ትኩረት ልንሰጠው የሚገባ ነጥብ ነው! መቼም ፈቅደንም ሆነ ተገደን "በአማራ ፖለቲካ ውስጥ አለንበት!" እስካልን ድረስ ፤ ቃላቶቻችን ጥይት ሆነው የመግደልም ሆነ መድሀኒት ሆነው የመፈወስ ኃይል እንዳላቸው መገንዘብ በእጅጉ ያስፈልገናል፡፡ ፖለቲካዊ ተግባቦት/Political Communication ከስሜት በዘለለ ፥ ፖለቲካዊ አላማንና ግብን ከማሳካት አኳያ ካልተቀነበበ የሚወልደው አደጋና ኪሳራም የትየለሌ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ በሳይበሩና በሚዲያዎች አካባቢ ፖለቲካዊ ሀሳቦቻችንን የምናቀርብና ለተግባቦታዊ ስርአቱ ቅርብ የሆንን ሰዎች ፥ በዚህ ረገድ የመጣንበትን ገምግመን ራሳችንን ልናርም ፣ ልናበቃና ልንነቃ ይገባል ባይ ነኝ፡፡ አንዳንድ ወገኖቻችን በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ፥ ሁኔታና ጊዜው ስለፈቀደላቸው ብቻ ፥ በተለያዩ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በፅሁፍ ፣ በድምፅና በተንቀሳቃሽ ምስል የሚያሰራጯቸው አደገኛ ንግግሮች ፥ ተፅዕኗቸው እነሱ ጋር ባይደርስ እንኳ ሌላ ቦታ ገጀራ ፥ ጥይት ፣ እሳት ፣ መከራና ግፍ ሆነው ፥ "እንታገልለታለን" በምንለው ህዝብ ላይ እንደበረዶ ይዘንባሉ፡፡ የምንታገላቸው ፅንፈኛ የፖለቲካ ሀይሎች (ቡድኖች) እነዚያን ሀላፊነት የጎደላቸውና የአማራ ህዝብ መሠረታዊ የትግል ግብና አላማ ያልሆኑ የግለሰቦች ሀሳብና ንግግሮች እያስተጋቡም " እነሱኮ አላማቸው ይኸ ነው!" ሲሉ እንደህዝብ አቋም ወስደው ከፍተኛ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ያደርጋሉ ፥ ይቀሰቅሳሉ ፥ ለህዝባችን ተጨማሪ ጠላት ለመፍጠር ይተጋሉ፡፡ በተለይ ደግሞ የምንታገለው "የጥላቻ ጡጦ ጠብተው ያደጉና በህዝብ ስልጣን ላይ ያሉ የፖለቲካ ሀይሎችን" እንጂ ህዝብን እንደህዝብ ፈርጀን አለመሆኑን ማጤንና ማስረዳት ያሻል፡፡ ሹምምንቱንና ፖለቲከኛውን እንዳሻን መተቸት ፥ መዝለፍ መቃወም መብታችን ነው፡፡ ሆኖም እነሱ ሴራ ደርተው ለስንፍናቸውና ለወንጀላቸው መደበቂያ የሚያደርጉትን የወጡበት ፥ ማህበረሰብ ወይም ግለሰባዊ አምልኮዎች (ሀይማኖቶች ) በተመለከተ በጅምላ ለሴራ የሚመነዘር ፖለቲካዊ ንግግር ማድረግ ፥ ፈፅሞ ጎጂና በገዛ ወገኖቻችን ላይ ተጨማሪ መከራ የሚያዘንብ መሆኑን በሚገባ በመረዳት ተጠንቅቀን መጓዝ ይኖርብናል፡፡ ይኸው ነው! 5.0K viewsedited 13:18