Get Mystery Box with random crypto!

...የዛሬው የሠላም ድስኩር ፤ ለነገው ጦርነት የመክፈቻ ምዕራፍ ነው! በተለይ በተለይ የኢትዮጵያ | ዘሪሁን ገሠሠ

...የዛሬው የሠላም ድስኩር ፤ ለነገው ጦርነት የመክፈቻ ምዕራፍ ነው!

በተለይ በተለይ የኢትዮጵያ ፖለቲካ "አክተር" የሚባሉት ሀይሎች የተወከሉባቸው የኦሮሞ ፣ የአማራና የትግራይ ህዝቦች ፤ ወደራሳቸው በመመልከት ፤ የሴራ ፖለቲከኞችን መደበቂያ ዋሻ ለማሳጣትና የተሻሉ መሪዎችን ከአብራካቸው ለማውጣት ብሎም የሀገሪቱን ነገ ለመወሰን ፥ ከዚህ ካለንበት ወቅት የበለጠ የመማሪያ እድል የለም!

..አስከሬን በቅጡ አልተሰበሰበም ፤ ሌላው ቀርቶ መርዶ እንኳ በቅጡ በክብር አልተረዳም ፥ እልፍ የትግራይ ፣ የአማራ ፣ የኦሮሞ ፣ የአፋር ፥ ... እናቶች ልጆቻቸውን ዛሬም "በር በር" እያዩ እየጠበቁ ነው ፤ ....!

ህዝብ ያልቃል ፤ የሴራ ፖለቲከኛው ጥቅሙን ተደራድሮ ይታረቃል! ዞሮ ደግሞ "ክተት ፣ አንክት" ባለበት አንደበቱ ስለሰላም አስፈላጊነት እየሰበከህ ልብህን ያደርቃል!

ህዝብ ፍዝ ተመልካች በሆነበት ሀገር የፖለቲካ ጨዋታው ህግ ይህ ነው!

አብረሀቸው እንደቤተሰብ ከኖርካቸው የአማራ ፥ የትግሬ ፥ ...ወዘተ ጎረቤቶችህ ጋር ሁሉ ሆድና ጀርባ አድርጎህ ፤ " ጁንታና የቀን ጅብ ብለህ ጥራቸው!" ብሎ የቀሰቀሰህና ያዘመተህ የሴራ ፖለቲካ ሊቅ ፥ ዛሬ ስለሰላም ሲዘምር ፥ ዛሬ ስለጦርነት አስከፊነት ሲሰብክህ ፤ ከአንድ ሚሊየን በላይ ሰው ቀርቶ ችግኝ ያስጨፈጨፈ አይመስልም!

ህዝብ "ለምን? ከዚያስ?" ብሎ መጠየቅ ካልጀመረ ፤ ለሴራና ለጥላቻ ፖለቲከኞች መደበቂያ ዋሻ ከመሆን ካልተቆጠበ ብሎም "በቃ!" ብሎ የትውልዱን የተሻለ ነገና ሀገር ለመፈለግ ካልተነሳ ፤ የዛሬው የሰላምና ፌሽታ ድግስ የነገው ሌላ የእልቂት ድግስ አቀባበል መሆኑን አስረግጨ እነግርሃለሁ!