Get Mystery Box with random crypto!

ሞራሉ በቀላሉ የማይሰበር ሕዝብ ስነልቦናው ከፍ ያለ ነው! (The psychology of the ma | ፍልስፍና ለላቀ አስተሳሰብ Philosophy

ሞራሉ በቀላሉ የማይሰበር ሕዝብ ስነልቦናው ከፍ ያለ ነው!
(The psychology of the masses always matters)
(እ.ብ.ይ)

ሐገር በየትኛውም ጊዜ የእርስበርስ እልቂትና የጦርነት አደጋ ሊያጋጥማት ይችላል፡፡ አደጋው በራሷ ልጆች አልያም በውጪ ጠላቶቿ ሊከሰት ይችላል፡፡ ስጋት የነበረ፣ ያለና ወደፊትም የሚኖር ነው፡፡ አይደለም በሐገር ደረጃ በግለሰብ ደረጃም ትላልቅ ስጋቶች አሉ፡፡ ማንም ከደቂቃ በኋላ ስላለው ጤናው፣ ሰላሙና ደህንነቱ ማወቅ አይችልም፡፡ አንዳንድ ሁኔታዎች ከምንጠብቀውና ከምንገምተው በላይ ሆነው ከቁጥጥራችን ውጪ ሊወጡ ይችላሉ፡፡ ስጋትን መተንተን፣ ሊፈጠሩ የሚችሉ ያልታሰቡ ክስተቶችን ማሰብ ነገሮቹ ሲፈጠሩና ከተፈጠሩ በኋላ ለሚኖረው መፍትሄ ወሳኝ ነገሮች ናቸው፡፡ በጥሩም ይሁን በመጥፎ በሕይወታችን ላይ የሚፈጠሩ አዳዲስ ክስተቶች ይዘውት የሚመጡት መልካም አጋጣሚዎችና አደጋዎች መኖራቸው አያጠያይቅም፡፡ የሚሊየን ዶላሮች ሎተሪ የደረሰው ሰው የአዕምሮ ዝግጁነት ከሌለው ዕድሉ አይሆኑ የሕይወት ፈተና ውስጥ ሊሰነቅረው ይችላል፡፡ መከራ አንድም በደስታ ጊዜ፤ አንድም በሃዘን ጊዜ ሊፈጠር ይችላል፡፡ ይሄን ክስተት የሚቀበል የአዕምሮ ዕውቀትና የስሜት ብስለት ከሌለ ወድቆ መቅረትን ያመጣል፡፡ ሐገር ችግሮቿን ተሻግራ፤ መከራዎቿን አልፋ ጸንታ ልትቆም የምትችለው የሕዝቧ ስነልቦና ጠንካራ ሲሆን ነው፡፡ የህዝብ ስነልቦናው መነሻው የግለሰብ ስነልቦና ነው፡፡ በስሜት ብስለት (Emotional intelligence) ያልሰለጠነ ዜጋ ራሱንም ሆነ ሐገሩን ከሚመጣበት መከራ ሊያድን አይችልም፡፡ አስደንጋጭ ክስተት ሲፈጠር አሁናዊ አደጋውንና የሚቀጥለው መዘዙን በእንዴት ያለ መፍትሄ ማስቀረት እንደሚቻል የአዕምሮ ዝግጁነት ከሌለ ከጠፋው በላይ ሌላ ጥፋት ይከተላል፡፡

እንግሊዛውያን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ዋዜማ ላይ ስጋት ወጥሯቸው፣ ፍርሃት ወርሯቸው ጭንቀት በጭንቀት ሆነው እንደነበር ታሪክ ይናገራል፡፡ በዚህ አስፈሪ ጊዜ አዶልፍ ሂትለር በእንግሊዛውያን ላይ የቦንብ ናዳ ለመልቀቅ የመጨረሻ ውሳኔ ላይ መድረሱ የለንደንን ነዋሪዎች አንቅልፍ ነስቶ ነበር፡፡ ትንሹም ትልቁም ካሁን አሁን የቦንብ ናዳ ረገፈብን በሚል በፍርሃት ቆፈን ተይዞ የለንደንን ሰማይ በየደቂቃው በሰቀቀን ይመለከት ነበር፡፡ በፈረንጆቹ ጥቅምት 19 ቀን 1939 ዓ.ም. ሂትለር ለጦር ጄኔራሎቹ በለንደን ሰማይ ላይ እንዴት ጥቃት እንደሚፈጽሙ እቅዱን አብራራ፡፡ እ.ኤ.አ. መስከረም 7 ቀን 1940 ዓ.ም. ሶስት መቶ አርባ ስምንት የጀርመን ቦንብ ጣይ አይሮፕላኖች ለንደን ሰማይ ላይ ተራወጡ፡፡ ያ ቀን ለእንግሊዛውያኑ ጥቁር ቀን (Black Satureday) ነበር፡፡ በዚህ ቀን የተጀመረው ጥቃት ለተከታታይ ዘጠኝ ወራት ቀጠለ፡፡ በዚህም ከ80 ሺ በላይ የሚቆጠሩ ንጹሃን ዜጎች በጥቃቱ ሕይወታቸውን አጡ፡፡ በሚሊየን የሚቆጠሩ የለንደን ታሪካዊ ህንጻዎች ፈራረሱ፡፡ ለንደን እንዳልነበረች ሆነች፡፡

ከሁሉ የሚገርመው ይሄን አደጋ እንዴት ነበር እንግሊዛውያኑ ተቀብለው ያስተናገዱት የሚለው ነበር፡፡ እንግሊዛውያኑ ያ ሁሉ ጥቃት ሲፈፀምባቸው ትራፊኩ ስራውን ከመስራት አልታቀበም፤ ህጻናቱ በሰላሙ ጊዜ የሚጫወቱትን ጨዋታቸውን አላቋረጡም፣ ሰራተኛው ከስራው ገበታው አልተስተጓጎለም፡፡ ባለሱቆቹ ከምንጊዜውም በላይ ሱቃቸው በር ላይ ‹‹መስኮቶቻችን በጥቃቱ ቢደቅቁም መንፈሳችን ግን አልደቀቀም፡፡ ደንበኞቻችን ይግቡና የሚፈልጉትን ይሸምቱ! (Our windows are gone. But our spirits are excellent. Come in and try them)›› የሚል ማስታወቂያ ለጥፈው ደንበኞቻቸውን ይጠባበቁ ነበር፡፡ ሂትለር በጊዜው የእንግሊዝን የደህንነት መረጃና የጦር ሚስጥር ቢያውቅም የእንግሊዛውያኑን የመንፈስ ጥንካሬ ግን አያውቅም ነበር፡፡ ዊኒስተል ቸርችል በዚህ ጥቃት ከሶስት እስከ አራት ሚሊየን የሚጠጉ ዜጎቹ ጦርነቱን በመሸሽ ሐገራቸውን ለቀው ይሰደዳሉ ብሎ ቢገምትም የሆነው ግን በተቃራኒው ነበር፡፡

እንግሊዛውያኑ በጥቃቱ ዘመዶቻቸውን በማጣታቸው ሐዘን ቢሰማቸውም፤ ንብረታቸው በመውደሙ ቢበሳጩም ስሜታቸውን የሚያስጨንቅ፣ አዕምሯቸውን የሚረብሽ ምንም ዓይነት የመንፈስ ጠባሳ (Trauma) አልነበረባቸውም፡፡ እንደውም በሰላሙ ጊዜ የነበሩ ወንጀሎች በዚህ ክፉ ጊዜ ቀንሰው ነበር፡፡ የአልኮል ጠጪዎች ከሸመታ ቤት ጠፍተዋል፡፡ ደሃም ይሁን ሃብታም እርስበራሳቸው ይረዳዱ ነበር፡፡ የተጎዱ ቤተሰቦችን በመርዳትና በመጎብኘት ያፅናኑ ነበር፡፡ ፖለቲካ ከሞራላቸው አላነጣባቸውም፤ የካድሬ ጩኸት እርስበራሳቸው አልለያያቸውም፡፡ ይሄ ክፉ ጊዜ ሰው-ነታቸውን አስታወሰ እንጂ ሰብዓዊነታቸውን አልቀማቸውም፡፡ ባንክ ለመዝረፍ የሮጠ የለም፡፡ እስር ቤቶችን ሰብሬ በህግ ጥላ ስር ያሉ እስረኞችን አስለቅቃለሁ ያለ ጉልበተኛ የለም፡፡ ይሄን የቀውጢ ሰዓት ተጠቅሞ ሱቆችን ሰባብሮ እቃዎችን ለመስረቅ ያሰበ ማንም አልነበረም፡፡ በጦርነቱ ምክንያት ኢኮኖሚያቸው እንዳይጎዳ ራሳቸውን ለአደጋ አጋልጠውም ቢሆን ስራቸውን ከመስራት ያቆማቸው አንዳች ሃይል አልነበረም፡፡

ሊንድማን የተባለ የቸርችል የቅርብ ጓደኛ በጦርነቱ ሳቢያ በጣም በተጎዱ በበርሚንግሃምና ኸል (Bermingham and Hull cities) በተባሉ ሁለት ከተሞች እንግሊዛውያኑ የመንፈስ ስብራትና የአዕምሮ መረበሽ እንደደረሰባቸውና እንዳልደረሰባቸው ለማወቅ ሁለት የጥናት ቡድኖችን ወደከተሞቹ ላከ፡፡ አጥኒዎቹም ይዘዉት የመጡት የጥናት ግኝቶች (Findings) ግን ብዙዎችን ያስደነቀ ነበር፡፡ በጥናቱ ወረቀት የፊት ገፅ ላይ በትላልቅ ፊደላት የተፃፈው ፡-

‹‹There is no evidence of breakdown of morale (የሞራል ስብራት እንዳለ የሚያረጋግጥ ምንም ማስረጃ የለም)‹‹ የሚል ነበር፡፡

አዎ ሐገርን ከአደጋ በኋላ ቀና የሚያደርገው ገንዘብ ብቻ አይደለም፡፡ ሐገርን ወደፊት እንዲቀጥል የሚያደርገው የህዝቡ ፅናትና የስነልቦና ጥንካሬ ነው፡፡ እንግሊዛውያኑ የሂትለርንና የቸርችልን ፖለቲካዊ እሰጣ ግባ ችላ ብለው ለሐገራቸው የቆሙት መንፈሳቸው ጠንካራ ስለነበረ ነው፡፡ የመጣባቸውን ጥፋት ተጋፍጠው ሞራላቸውን ሳያስነኩ ሀገራቸውንም ራሳቸውንም ጠብቀው ለቀጣዩ ትውልድ አስረክበዋል፡፡ ሞቱን ተቀብለው፤ አካል ጉዳቱን ችለው ሐገራቸው ኢኮኖሚዋ እንዳይወድቅ የበኩላቸውን ሚና ተጫውተዋል፡፡ በዚህም ለሌላው የዓለም ህዝብ ምሳሌ ሆነው ሲዘከሩ ይኖራሉ፡፡

ሐገርን በፅኑ መሰረት ላይ የሚያቆመው ጠንካራ ስነልቦና ያለው ህዝብ ነው! መንፈሱ ከፍ ያለ ሕዝብ ሐገሩ ላይ የተደቀነውን ፈተና ያልፋል፤ ከፊቱ የተጋረጠውን አደጋ ይሻገራል!

አዎ! አጥፊዎች ሆይ... ‹‹ንብረቶቻችንን ልታወድሙ ትችላላችሁ፤ መንፈሳችንን ግን ማድቀቅ አትችሉም፡፡ አካላችንን ትጎዱት ይሆናል ስነልቦናችንን ለመድፈር ግን አቅም የላችሁም!››

ቸር ጊዜ!

ኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊነት መንፈስ ለዘላለም ይኑሩ!

_____
እሸቱ ብሩ ይትባረክ
(እ.ብ.ይ.)

@Zephilosophy
@Zephilosophy