Get Mystery Box with random crypto!

በሐመር ወረዳ 65 ከመቶ የሚሆነው የበልግ ሰብል በተከሰተ የዝናብ እጥረት ከጥቅም ውጭ መሆኑ ተነገ | ዳጉ-ጆርናል/Dagu-Journal

በሐመር ወረዳ 65 ከመቶ የሚሆነው የበልግ ሰብል በተከሰተ የዝናብ እጥረት ከጥቅም ውጭ መሆኑ ተነገረ

በሐመር ወረዳ ምርት ለመስጠት ደርሶ የነበረ የበልግ ሰብል በተከሰተ የዝናብ እጥረት 65 ከመቶ የሚሆነው ሰብል በፀሐይ ተቃጥሎ ከጥቅም ውጭ እንደሆነ ተነግሯል ።በወረዳው ከአራት ዓመታት በላይ ዝናብ ሳይጥል መቆየቱ የሚታወስ ሲሆን ከወራት በፊት ዝናብ መጣሉን ተከትሎ ከ7200 ሄክታር መሬት በላይ በበልግ ሰብል መሸፈኑ ተገልጿል ።

ከዚህ ውስጥ በተከሰተው የዝናብ እጥረት በበልግ በሁሉም የሰብል አይነቶች ከተሸፈነው መሬት ውስጥ 65 ከመቶ የሚሆነው ሰብል ምርት እንደማይሰጥ የሐመር ወረዳ ኮሚኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሀላፊ አ/ቶ አወቀ ንጋቱ ለብስራት ራዲዮ ተናግረዋል ።

በፀሐይ የተቃጠለው ሰብል ምንም አይነት ምርት እንደማይሰጥ በእርሻ ዘርፍ በተደረገ የዳሰሳ ጥናት መረጋገጡን ገልጸዋል ። በዚህ ምክንያት አርሶ አደሮች ሰብሉን ለእንስሳት መኖ እንዲውል ማድረጋቸው ተነግሯል ።

በወረዳው ከፊል አርሶ አደር እና አርብቶ አደር የማህበረሰብ ክፍል የሚገኝ ሲሆን ለተከታታይ ዓመታት በሰው እና በእንስሳቱ ላይ ድርቅ መፈራረቁን ተናግረዋል ። በዚህ ዓመት በተገኘው ዝናብ ሰፊ ስራ ቢሰራም በተከሰተው የዝናብ እጥረት ምክንያት ምርት ሊሰጡ የተቃረቡ ሰብሎች በፀሐይ መቃጠላቸው የማህበረሰቡን ቅስም መስበሩን አ/ቶ አወቀ ጨምረው ተናግረዋል ።

በአበረ ስሜነህ
#ዳጉ_ጆርናል