Get Mystery Box with random crypto!

በሶማሌ ክልል በባህላዊ የምርጫ ሥነ ሥርዓት ላይ በፀጥታ ኃይሎች የተፈጸመውን ግድያ ኢሰመኮ ኮነነ! | ዳጉ-ጆርናል/Dagu-Journal

በሶማሌ ክልል በባህላዊ የምርጫ ሥነ ሥርዓት ላይ በፀጥታ ኃይሎች የተፈጸመውን ግድያ ኢሰመኮ ኮነነ!

በሶማሌ ክልል ቦምባስ ከተማ በባህላዊ ሥነ ሥርዓት የጎሳ መሪ ለመምረጥ በተሰበሰቡ ሰዎች ላይ በፀጥታ ኃይሎችና በታጠቁ ግለሰቦች በተፈጸሙ ጥቃቶች የ11 ሰዎች ህይወት መጥፋቱን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ኮነነ።በሶማሌ ክልል ከሚገኙት የሶማሌ ጎሳዎች መካከል የሆኑት የአኪሾ ጎሳ አባላት መጋቢት 11 እና 12 ቀን 2014 ዓ.ም. የጎሳ መሪያቸውን ለመምረጥ በተሰበሰቡበት ዕለት ከግድያ በተጨማሪ 33 ሰዎች ላይ ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱን ማረጋገጡን ኢሰመኮ ዛሬ ግንቦት 04/2014 ዓ.ም. ባወጣው የምርመራ ሪፖርቱ አስታውቋል።

ኢሰመኮ በስፍራው ተገኝቶ ባደረገውም ምርመራ የክልሉ መንግሥት የፀጥታ አካላት ከመጠን ያለፈ የኃይል አጠቃቀም ለሞትና ለአካል ጉዳት ምክንያት ሆኗል ብሏል።ኢሰመኮ በሁለቱ ቀናት ስለተፈጸሙ ግድያዎችና የአካል ጉዳቶች የደረሰውን ጥቆማ ተከትሎ በቦታው በመገኘት የዓይን ምስክሮችን፣ ተጎጂዎችን፣ የተጎጂ ቤተሰቦችን፣ የአገር ሽማግሌዎችን ማናገሩን አስታውቋል።

በተጨማሪም ከሆስፒታል ምንጮች መረጃ በማሰባሰብ እንዲሁም ፈቃደኛ የሆኑ የክልሉ ኃላፊዎችን በማነጋገር የምርመራውን ሪፖርት አጠናቅሯል።በተጨማሪም ቦምባስ ከተማ የሚገኝ የጥቃቱ ሰለባዎች የተቀበሩበትን መካነ መቃብር መጎብኘቱን ገልጾ በዚህም በመጀመሪያው ቀን የተገደሉ ሰዎች የተቀበሩበትን የጅምላ መቃብር እንዲሁም በሁለተኛው ቀን የተገደለች ሴት ተቀብራበታለች የተባለ መካነ መቃብር መመልከቱንም በዚሁ የምርመራ ሪፖርቱ አካቷል።

#ዳጉ_ጆርናል