Get Mystery Box with random crypto!

ዓርብ ምሽት! ግንቦት 11/2015 ዓ.ም የEMS ዐበይት ዜናዎች 1፤ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ላ | Zemedkun Bekele (ዘመዴ)

ዓርብ ምሽት! ግንቦት 11/2015 ዓ.ም የEMS ዐበይት ዜናዎች

1፤ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ላቀደው ብሄራዊ ምክክር አጀንዳ ሊኾኑ የሚችሉ ጉዳዮችን ከዛሬ ጀምሮ ከኅብረተሰቡ መቀበል መጀመሩን ዛሬ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል። ኮሚሽኑ በቀጣዩ ሳምንት በሲዳማ፣ ጋምቤላ፣ ሐረሬና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎችና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በአገራዊ ምክክሩ ሂደት የሚሳተፉ ግለሰቦችን መለየት እንደሚጀምር በመግለጫው አመልክቷል። ኅብረተሰቡ የአገራዊ ምክክሩ ተሳታፊዎችን የሚመርጠው በወረዳ ደረጃ መኾኑን ኮሚሽኑ ገልጧል።

2፤ ገቢዎች ሚንስቴር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያሻሻለውን የኤክሳይስ ታክስ አዋጅ ዝርዝር ዛሬ ይፋ አድርጓል። አዋጁን ማሻሻል ያስፈለገው፣ በአንዳንድ ምርቶች ላይ የተጣሉ ተደራራቢ ኤክሳይስ ታክሶችን ለማንሳት፣ ከአንዳንድ ምርቶች ላይ ኤክሳይስ ታክሱን ሙሉ በሙሉ ለማንሳትና የቴሌኮምንኬሽን አገልግሎቶችን ኤክሳይስ ታክስ ለማስከፈል እንደኾነ ሚንስቴሩ ገልጧል። የተሻሻለው አዋጅ፣ በሞባይል ኢንተርኔትና የሞባይል ድምጽና የጽሁፍ መልዕክቶች ላይ የ5 በመቶ ኤክሳይስ ታክስ የጣለ ሲኾን፣ ባንጻሩ በኪሮዚን፣ ቤንዚንና ናፍጣ ላይ የተጣለውን የ30 በመቶ ኤክሳይስ ታክስ ወደ 15 በመቶ ዝቅ እንዳደረገው ተገልጧል።

3፤ በየመን በረሃ ላይ ሞተው በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የአስከሬናቸው ምስሎች ሲሰራጩ የሰነበቱት ፍልሰተኞች ኢትዮጵያዊያን እንደኾኑ መረጋገጡን ቢቢሲ አማርኛ ዘግቧል። ፍልሰተኞቹ ሕይወታቸው ያለፈው በሕገወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች አማካኝነት ከየመን ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ በእግር በመጓዝ ላይ ሳሉ መኾኑን የዓይን ምስክር ፍልሰተኞች መናገራቸውን ዘገባው ጠቅሷል። 20 ያህል የሚኾኑት ወንድና ሴት ኢትዮጵያዊያን ፍልሰተኞች ሕይወታቸው ያለፈው፣ በድካም፣ ርሃብና ውሃ ጥም መኾኑን የዓይን ምስክሮቹ መናገራቸውን ዜና ምንጩ አመልክቷል። ዓለማቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት፣ ኢትዮጵያዊያን፣ ኤርትራዊያንና ሱማሊያዊያን ፍልሰተኞች በፑንትላንድ፣ ሱማሌላንድና ጅቡቲ በኩል ወደ የመን የሚሻገሩበት መስመር በርካቶችን ለሞት፣ ለአስገድዶ መደፈርና ድብደባ እያጋለጣቸው የሚገኝ እጅግ አደገኛ መስመር መኾኑን በተደጋጋሚ ይገልጣል።

4፤ የኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን መንግሥታት ሀለቱን አገራት የሚያገናኝ የመንገድ ግንባታ ስምምነት ዛሬ ጁባ ውስጥ መፈራረማቸውን የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር አስታውቋል። መንገዱ ከተገነባ፣ የሁለቱን አገራት ኢኮኖሚያዊ ትስስርና የጋራ የድንበር ጸጥታ ይበልጥ እንደሚያጠናክረው በስምምነቱ ፊርማ ስነ ሥርዓት ላይ ተገልጧል። የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቱ፣ ምዕራብ ኢትዮጵያን ከሰሜን ምሥራቅ የደቡብ ሱዳን ግዛቶች ጋር የሚያገናኝ ነው።

5፤ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት መርማሪ ፖሊስ በሽብር ወንጀል በተጠረጠሩ ስድስት ተጠርጣሪዎች ላይ ምርመራውን አጠናቆ እንዲያቀርብ የ7 ቀናት ጊዜ መስጠቱን የአገር ውስጥ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ችሎቱ ውሳኔውን የሰጠው፣ የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆችና መርማሪ ፖሊስ ትናንት ያቀረቡትን መከራከሪያ ከመረመረ በኋላ ነው። ከተጠርጣሪዎቹ መካከል፣ የ"ንቃት ኢትዮጵያ" ዩትዩብ ጣቢያ ባለቤት መስከረም አበራ ትገኝበታለች። መርማሪ ፖሊስ፣ በቀደሙት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜያት ከባንኮች የተጠርጣሪዎችን የገንዘብ ዝውውር ሰነዶች ማሰባሰቡን፣ የተጠርጣሪዎቹን የተከሳሽነት ቃላቸውን መቀበሉን፣ በተጠርጣሪዎቹ መኖሪያ ቤት ብርበራ ማካሄዱንና ሌሎች ክንውኖችን መጥቀሱን ዘገባዎቹ ጠቅሰዋል።

6፤ የሱማሊያ ደኅንነት ከሞቃዲሾ ወደብና አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ ለአልሸባብ ሊላኩ የነበሩ ከፍተኛ መጠን ያላቸው ጦር መሳሪያዎችና ተቀጣጣይ ፈንጂዎች መያዙን የአገሪቱ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። በሕገወጥ መንገድ ከገባው ጦር መሳሪያ ጋር በተያያዘ 10 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር እንደዋሉ የሱማሊያ ባለስልጣናት መናገራቸውን ዘገባዎቹ ጠቅሰዋል። ጦር መሳሪያዎቹና ተቀጣጣይ ፈንጂዎች ከየት አገር እንደገቡና በቁጥጥር ስር የዋሉትን ግለሰቦች ማንነት ባለሥልጣናቱ እንዳልጠቀሱ ተገልጧል። የተመድ ጸጥታው ምክር ቤት ከ30 ዓመት በፊት በሱማሊያ ላይ የጣለውን የጦር መሳሪያ ማዕቀብ እስካኹን አላነሳም።

7፤ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 54 ብር ከ2545 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 55 ብር ከ3398 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ በድረገጹ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 64 ብር ከ3987 ሳንቲምና መሸጫው 65 ብር ከ6867 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ58 ብር ከ6222 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ59 ብር ከ7946 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል። #ሼር በማድረግ ተባበሩን


ወሳኝ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ቻናሉን ይቀላቀሉ

                                  
@emsmereja