Get Mystery Box with random crypto!

ሐሙስ ምሽት! ግንቦት 10/2015 ዓ.ም የEMS ዐበይት ዜናዎች 1፤ የፌደራልና ክልል መንግሥታት | Zemedkun Bekele (ዘመዴ)

ሐሙስ ምሽት! ግንቦት 10/2015 ዓ.ም የEMS ዐበይት ዜናዎች

1፤ የፌደራልና ክልል መንግሥታት ከፍተኛ የበጀት እጥረት እንደገጠማቸው ዋዜማ ከምንጮቿ ሰምታለች። መንግሥት በርካታ የግዥ ጨረታዎችን የሰረዘ ሲኾን፣ አንዳንድ ክልሎች ደሞ ለመንግሥት ሠራተኞች ለወራት ደመወዝ አልከፈሉም። በካሳ ክፍያና ከግንባታ ግብዓቶች ዋጋ መናር ሳቢያ፣ 40 መንግሥታዊ ፕሮጀክቶች በእንጥልጥል ላይ እንደኾኑ የፌደራል መንገዶች አስተዳደር ምንጮች ለዋዜማ ተናግረዋል። መንግሥት ለበጀት ዓመቱ ካጸደቀው 786 ቢሊዮን ብር ውስጥ፣ በርካታ ባለበጀት መስሪያ ቤቶች የተመደበላቸው የበጀት ድጎማ ሙሉ በሙሉ አልተለቀቀላቸውም። የዘንድሮው በጀት ሲጸድቅ፣ በብድርና በበጀት ድጋፍ የሚሞላ የ300 ቢሊዮን ብር ጉድለት ነበረበት።

2፤ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ በባሕርዳር ከተማ ክልል ዓቀፍ ኮንፈረንስ መጀመሩን የክልሉ ቴሌቪዥን ዘግቧል። በኮንፈረንሱ ላይ ከ1 ሺህ 400 በላይ ከፍተኛና መካከለኛ የፓርቲና የመንግሥት አመራሮች እንደሚሳተፉ ዘገባው አመልክቷል። የኮንፈረንሱ ዓላማ፣ በክልሉ ወቅታዊ ፈተናዎችና ችግሮች ዙሪያ በመወያየት የፓርቲውንና የክላሉን መንግሥት ጥንካሬ ማጎልበት እንደኾነና በመድረኩ ላይ ጠንካራ የውስጠ ፓርቲ ዲሞክራሲያዊ ትግል ይካሄዳል ተብሎ እንደሚጠበቅ ፓርቲው መናገሩን ዘገባው ጠቅሷል።

3፤ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የተመሠረተበትን 60ኛ ዓመት ከግንቦት 17 ጀምሮ በተለያዩ መርሃ ግብሮች አዲስ አበባ ውስጥ ለአንድ ዓመት ያህል እንደሚከበር የውጭ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ መለስ ዓለም ዛሬ በሰጡት መግለጫ መናገራቸውን የአገር ውስጥ ዜና አውታሮች ዘግበዋል። መርሃ ግብሮቹ፣ ፓን አፍሪካኒዝምን በማጠናከር እና አፍሪካ ኅብረት እኤአ በ2063 ዓ፣ም ለማሳካት የያዛቸውን ግቦች በማውሳት ላይ የሚያተኩሩ እንደሚኾኑ ቃል አቀባዩ መግለጣቸውን ዘገባዎቹ ጠቅሰዋል። የኅብረቱ አባል አገራት በዓሉን በየራሳቸው መንገድ እንደሚያከብሩት ተናግረዋል ተብሏል።

4፤ የ"ንቃት ኢትዮጵያ" ዩትዩብ ጣቢያ ባለቤት መስከረም አበራና ሌሎች አምስት ተከሳሾች ዛሬ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በተሰጣቸው ቀጠሮ መሠረት እንደቀረቡ የአገር ውስጥ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። መርማሪ ፖሊስ በባለፈው ቀጠሮ፣ በተጠርጣሪዎቹ ላይ "በአማራ ክልል ሁከትና ብጥብጥ መፍጠር" የሚለውን የምርመራ መዝገቡን ቀይሮ "የሽብር ወንጀል" መዝገብ በመክፈት፣ የ14 ቀናት ተጨማሪ ቀጠሮ እንደተሰጠው ይታወሳል። መርማሪ ፖሊስ የጀመረውን ምርመራ ለማጠናቀቅ ተጨማሪ 14 ቀናት እንዲሰጠው ዛሬም በድጋሚ መጠየቁንና፣ የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆችም የደንበኞቻቸው የዋስትና መብት እንዲከበር መጠየቃቸውን ዘገባዎቹ ጠቅሰዋል። ችሎቱ፣ የሁለቱን ወገኖች ክርክር መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት ነገ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል ተብሏል።

5፤ በኢትዮጵያ የአውሮፓ ኅብረት አምባሳደር ሮላንድ ኮቢያ የሚመሩት ልዑካን ቡድን ዛሬ በትግራይ ክልል በሰሜኑ ጦርነት ሳቢያ ከሁለት ዓመት በላይ የመማር ማስተማር ሥራውን ካቋረጠው የአዲግራት ዩኒቨርሲቲ አመራሮች ጋር መወያየቱን የክልሉ ቴሌቪዥን ዘግቧል። የአዲግራት ዩኒቨርስቲ አመራሮች በጦርነቱ ወቅት በዩኒቨርስቲው ላይ የደረሰውን ውድመትና ሌሎች ጉዳቶች የያዘ ዝርዝር ሰነድ ለኅብረቱ ልዑካን ቡድን ማስረከባቸውን ዘገባው አመልክቷል። አዲግራት ዩኒቨርሲቲ፣ በትግራይ ክልል ከሚገኙ አራት የፌደራል ዩኒቨርሲቲዎች መካከል አንዱ ነው፡ የአውሮፓ ኅብረት ልዑካን ቡድን ከአዲግራት ቀጥሎ፣ በሽሬ ከተማና አካባቢዋ በሚገኙ መሠረተ ልማቶች ላይ ጦርነቱ ያደረሰውን ጉዳት ይጎበኛል ተብሏል።

6፤ ትምህርት ሚንስቴር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች መውጫ ፈተና ከሐምሌ 3 እስከ ሐምሌ 13 ድረስ በሁሉም የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መፈተኛ ማዕከላት ውስጥ እንደሚሰጥ አስታውቋል። ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መውጫ የተዘጋጀውን ፈተና የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ጭ እንደሚወስዱት ሚንስቴሩ ገልጧል። ሚንስቴሩ ለሁሉም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመራቂ ተማሪዎች የመውጫ ፈተና የሚሰጠው፣ ሁሉም ተመራቂዎች በተመረቁበት የትምህርት መስክ በሥራ ዓለም ለመሠማራት የሚያበቃቸውን የእውቀትና ክህሎት ደረጃ ማሟላት አለማሟላታቸውን ለማረጋገጥ ነው።

7፤ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 54 ብር ከ0576 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 55 ብር ከ1388 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ በድረገጹ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 64 ብር ከ0924 ሳንቲምና መሸጫው 65 ብር ከ3742 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ59 ብር ከ3174 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ60 ብር ከ6037 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል። #ሼር በማድረግ ተባበሩን


ወሳኝ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ቻናሉን ይቀላቀሉ

                                  
@emsmereja