Get Mystery Box with random crypto!

ማክሰኞ ምሽት! ሚያዝያ 17/2015 ዓ.ም የEMS ዐበይት ዜናዎች 1፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤ | Zemedkun Bekele (ዘመዴ)

ማክሰኞ ምሽት! ሚያዝያ 17/2015 ዓ.ም የEMS ዐበይት ዜናዎች

1፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው ስብሰባ የተሻሻለውን የመከላከያ ሠራዊት አዋጅ በስድስት ድምጸ ተዓቅቦ አጽድቋል። መንግሥት አዘጋጅቶ ያቀረበው የተሻሻለ ረቂቅ አዋጅ፣ ኅብረ ብሄራዊ ተዋጽዖውን የጠበቀ ዘመናዊ የአገር መከላከያ ሠራዊት ለመገንባት ማነቆ ኾነዋል የተባሉ የሕግ ማዕቀፎችን ለማሻሻል ያስችላል ተብሏል። ተሻሽሎ የጸደቀው አዋጅ፣ የሠራዊቱ አባላት የጡረታ መውጫ የእድሜ ጣሪያን አወሳሰን፣ የ12ኛ ክፍል ወይም የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ተማሪዎች በፍቃዳቸው ለኹለት ዓመት ብሄራዊ አገልግሎት የሚሰጡበትን አግባብ፣ የአገር ሕልውና ከባድ አደጋ ላይ በሚወድቅበት ጊዜ ከሠራዊቱ የተገለሉ የቀድሞ አባላትን መልሶ መቅጠር የሚቻልበትና ሌሎች የሠራዊቱ መብትና ጥቅማ ጥቅሞችን እንዳካተተ ተገልጧል።

2፤ በሱዳን የኢትዮጵያ ኢምባሲ በሱዳኑ ውጊያ ቢያንስ ስምንት ኢትዮጵያዊያን እንደተገደሉና ሌሎች አራት ኢትዮጵያዊያን የመቁሰል ጉዳት እንደደረሰባቸው መናገሩን ቢቢሲ አማርኛ ዘግቧል። ኢትዮጵያዊያኑ ለሞት እና ለመቁሰል አደጋ የተዳረጉት፣ በተባራሪ ጥይት እና ከባድ መሳሪያ አረሮች ፍንጣሪ ሳቢያ መኾኑን ኢምባሲው መግለጡን ዘገባው አመልክቷል። ከአገሪቱ መውጣት የሚፈልጉ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ኢትዮጵያዊያን ዜጎች በአውቶብስ ወደ መተማ ለመሸኘት እየመዘገበ መኾኑን ኢምባሲው መግለጡን የጠቀሰው ዘገባው፣ የኢምባሲው ሠራተኞች ካርቱምን ለቀው ለኢትዮጵያ ቅርብ በኾነችው የሰሜን ሱዳኗ ገዳሪፍ ከተማ ሥራቸውን እያከናወኑ መኾኑን ጠቅሷል።

3፤ በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር ዛሬ መቀሌ መግባታቸውን የትግራይ ክልል ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ከልዩ መልዕክተኛ ሐመር ጋር በኢትዮጵያ የአሜሪካ ዋና ጉዳይ አስፈጻሚ ትሬሲ ጃኮብሰን አብረው መቀሌ ይገኛሉ ተብሏል። ሐመር ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ባለሥልጣናት ጋር ይወያያሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ዘገባው አመልክቷል። ሐመር፣ ባለፈው ኅዳር የሕወሃት የሰላም ተደራዳሪዎችን በአሜሪካ ወታደራዊ አውሮፕላን አሳፍረው ወደ ፕሪቶሪያ መውሰዳቸው ይታወሳል።

4፤ ትናንት በታንዛኒያ ጉብኝት ያደረጉት ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ደመቀ ዛሬ በኮሞሮስ ይፋዊ ጉብኝት በማድረግ ላይ ናቸው። ደመቀ ዛሬ ከኮሞሮስ ፕሬዝዳንት አዛሊ አሱማኒ ጋር ተገናኝተው፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ከሕወሃት ጋር በደረሰበት የሰላም ስምምነት አፈጻጸም ዙሪያ ለፕሬዝዳንቱ ገለጻ እንዳደረጉላቸው ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር አስታውቋል። ፕሬዝዳንት አዛሊ፣ በአፍሪካ ኅብረት አስተባባሪነት በሕዳሴ ግድብ ውዝግብ ላይ ተቋርጦ የቆየው የሦስትዮሽ ድርድር እንዲቀጥል ጥረት አደርጋለሁ በማለት ለደመቀ እንዳረጋገጡላቸው ተገልጧል። ፕሬዝዳንት አዛሊ የወቅቱ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር ናቸው።

5፤ አውሮፓ ኅብረት በኢትዮጵያ መንግሥት እና ሕወሃት መካከል የተፈረመው የሰላም ስምምነት ዘላቂ አፈጻጸምን መሠረት በማድረግ ከመንግሥት ጋር ያቋረጠውን ግንኙነት ደረጃ በደረጃ እንደገና ወደነበረበት ለመመለስ ጥረት እንደሚያደርግ ትናንት ባወጣው መግለጫ በድጋሚ አስታውቋል። ኾኖም ኅብረቱ፣ በሰሜኑ ጦርነት ኹሉም ተፋላሚ ወገኖች የፈጸሟቸው ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና በሰላማዊ ሰዎችና ስደተኞች ላይ የተፈጸሙ የጦር ወንጀሎች በገለልተኛ መርማሪ አካል አማካኝነት ግልጽና ገለልተኛ ምርመራ የማድረግ ጉዳይ ጊዜ የማይሰጠው እጅግ አስፈላጊ ነገር መኾኑን በመግለጫው አመልክቷል። ኅብረቱ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ባሁኑ ወቅት እየታዩ ያሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ ውጥረቶችና ግጭቶች እንዳሳሰቡት ገልጦ፣ በአገሪቱ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለማስፈንችግሮቹ በፖለቲካዊ እና ዲሞክራሲያዊ አግባብ በንግግር ብቻ እንዲፈቱ ጥሪ አድርጓል። ኅብረቱ በሰሜኑ ጦርነት ሳቢያ ለኢትዮጵያ የሚሰጠውን የበጀት ድጋፍ ያቋረጠው፣ ከኹለት ዓመት ከመንፈቅ በፊት ነበር።

6፤ የሱዳን ጦር ሠራዊትና ፈጥኖ ደራሽ ሠራዊት በአሜሪካ አደራዳሪነት ከትናንት እኩለ ሌሊት ጀምሮ የደረሱበት የ72 ሰዓታት የተኩስ አቁም ስምምነት ካርቱም ውስጥ ከሞላ ጎደል ተግባራዊ እየኾነ መኾኑን ዓለማቀፍ የዜና ምንጮች ዘግበዋል። በኦምዱሩማንና ሌሎች ከተሞች ግን ውጊያው እንደቀጠለ መኾኑን ዘገባዎቹ አመልክተዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የጦር ሠራዊቱ ዋና አዛዥ ጀኔራል አል ቡርሃን እና የፈጥኖ ደራሹ ሠራዊት ዋና አዛዥ ጀኔራል ሞሐመድ ደጋሎ ሳዑዲ ዓረቢያ ውስጥ ተገናኝተው ፊት ለፊት እንዲነጋገሩ ጥረቶች እየተደረጉ መኾኑን የግብጽ ዜና ምንጮች ዘግበዋል።

7፤ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 54 ብር ከ1241 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 55 ብር ከ2066 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ በድረገጹ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 64 ብር ከ3057 ሳንቲም እና መሸጫው 65 ብር ከ5918 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ59 ብር ከ6015 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ60 ብር ከ7935 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል። #ሼር በማድረግ ተባበሩን


ወሳኝ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ቻናሉን ይቀላቀሉ

                                   @emsmereja