Get Mystery Box with random crypto!

ሰኞ ማለዳ! ሚያዝያ 16/2015 ዓ.ም የEMS ዐበይት ዜናዎች 1፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ መንግ | Zemedkun Bekele (ዘመዴ)

ሰኞ ማለዳ! ሚያዝያ 16/2015 ዓ.ም የEMS ዐበይት ዜናዎች

1፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ መንግሥታቸው ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጋር ነገ የሰላም ድርድር ሊጀምር መኾኑን ትናንት የሰሜኑ ጦርነት እንዲቆም አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት እውቅና ለመስጠት በተዘጋጀው ልዩ ስነ ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር አስታውቀዋል። ዐቢይ፣ ከቡድኑ ጋር የሰላም ድርድር የሚደረገው በታንዛኒያ አስተናጋጅነት መኾኑን በንግግራቸው ላይ ጠቅሰዋል። መንግሥት ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጋር ድርድር ለመጀመር ባለፈው መጋቢት ላይ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት የሚመሩት ኮሚቴ ማቋቋሙን አስታውቆ ነበር።

2፤ አማጺው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ከመንግሥት ጋር የሰላም ድርድር ሊጀምር ነው ስለመባሉ ትናንት ማምሻውን ባወጣው መግለጫ አረጋግጧል ። ቡድኑ፣ ለሰላም ድርድሩ ያቀረብኳቸው "ቅድመ ሁኔታዎች በመንግሥት ዘንድ ተቀባይነት አግኝተዋል" ብሏል።

3፤ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ደመቀ በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመርን ትናንት በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው ማነጋገራቸውን ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በትዊተር ገጹ ባሰራጨው መረጃ አስታውቋል። በውይይቱ ላይ፣ ደመቀ በኢትዮጵያ መንግሥትና ሕወሃት መካከል በተደረሰው የሰላም ስምምነት አፈጻጸም ዙሪያ ለሐመር ማብራሪያ እንደሰጧቸው ሚንስቴሩ ገልጧል። ደመቀ፣ ኢትዮጵያ በጦርነቱ ማግስት እያካሄደች ላለችው የመልሶ ግንባታና ማቋቋም እንቅስቃሴ አሜሪካ ተጨባጭ ድጋፍ እንድታደርግ መጠየቃቸውን ሚንስቴሩ ጨምሮ አመልክቷል።

4፤ የአዲስ አበባ መምህራን ማኅበር የከተማዋ አስተዳደር ለ29 ሺህ 500 አባላቱ የመኖሪያ ቤት ችግር መፍትሄ እንዲሰጥ ለከንቲባ አዳነች አቤቤ በጻፈው ደብዳቤ መጠየቁን ሪፖርተር አስነብቧል። ከንቲባ አዳነች በከተማዋ አስተዳደር ስር የሚገኙ መምህራን በማኅበር ተደራጅተው ቤት እንዲገነቡ ከኹለት ዓመት በፊት ያሳለፉት ውሳኔ እስካሁን ተግባራዊ እንዳልሆነ ማኅበሩ መግለጡን ዘገባው ጠቅሷል። ማኅበሩ መምህራን ለከፍተኛ የኑሮ ውድነት እንደተጋለጡ ጠቅሶ፣ የከተማዋ አስተዳደር ከችግሩ ጋር የሚመጣጠን የገንዘብ ድጎማ እንዲያደርግ መጠየቁንም ዜና ምንጩ አመልክቷል።

5፤ የሱዳን ጦር ሠራዊትና ፈጥኖ ደራሽ ሠራዊት በካርቱም እና ሌሎች ግዛቶች የሚያካሂዱት ውጊያ ቀጥሏል። አሜሪካ እና ብሪታኒያ ትናንት ዲፕሎማቶቻቸውን ከካርቱም በአውሮፕላን አስወጥተዋል። አሜሪካ ዲፕሎማቶቿን ስታስወጣ፣ ኢትዮጵያ እና ጅቡቲ ትብብር እንዳደረጉላት ገልጻለች። ሌሎች በርካታ የአውሮፓ አገራትም ዜጎቻቸውንና ዲፕሎማቶቻቸውን በማስወጣት ሂደት ላይ እንደኾኑ ዓለማቀፍ የዜና ምንጮች ዘግበዋል። #ሼር በማድረግ ተባበሩን


ወሳኝ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ቻናሉን ይቀላቀሉ

                                   @emsmereja