Get Mystery Box with random crypto!

ቅዳሜ ምሽት! ሚያዝያ 14/2015 ዓ.ም የEMS ዐበይት ዜናዎች 1፤ ዛሬ ከመቀሌ ወደ አዲስ አበ | Zemedkun Bekele (ዘመዴ)

ቅዳሜ ምሽት! ሚያዝያ 14/2015 ዓ.ም የEMS ዐበይት ዜናዎች

1፤ ዛሬ ከመቀሌ ወደ አዲስ አበባ የአውቶብስ መጓጓዣ አገልግሎት መጀመሩን ድምጸ ወያኔ ዘግቧል። ከኹለት ዓመታት በኋላ ዛሬ መንገደኞችን ማጓጓዝ የጀመረው፣ ሰላም ባስ የግል ትራንስፖርት ኩባንያ መኾኑን ዘገባው አመልክቷል። በዛሬው የመጀመሪያ ጉዞ 54 መንገደኞች ከመቀሌ ወደ አዲስ አበባ እንደተጓዙ ዜና ምንጩ ገልጧል።

2፤ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ድርጅት ሲሚንቶ ለማገበያየት ያዋጣው እንደኾነ ለመወሰን ጥናት እያደረገ መኾኑን ሪፖርተር አስነብቧል። ድርጅቱ ጥናቱን አጠናቆና ከመንግሥት አስፈቅዶ ግብይቱን ከጀመረ፣ በኢንዱስትሪ ጥሬ ዕቃ ግብይት ሲሚንቶ በድርጅቱ ታሪክ የመጀመሪያው ይኾናል። የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ድርጅት አንድን ምርት ለማገበያየት ፍቃድ የሚያገኘው ከንግድ ሚንስቴር ነው። የሲሚንቶ የአገር ውስጥ ምርትና ግብይት በአሁኑ ወቅት በበርካታ ችግሮች ተተብትቦ የተያዘ እንደዳኾነ በተደጋጋሚ ተነግሯል።

3፤ የሱዳን ጦር ሠራዊትና የፈጥኖ ደራሽ ሠራዊት የውጭ አገር ዜጎችን ከካርቱም ለማስወጣት አውሮፕላን ጣቢያውን በከፊል ለመክፈት መስማማታቸውን ዛሬ በየፊናቸው አስታውቀዋል። ይህንኑ ተከትሎ፣ የአሜሪካ፣ ብሪታኒያ፣ ፈረንሳይ እና ቻይና ዜጎችና ዲፕሎማቶች በወታደራዊ አውሮፕላን ከካርቱም እንዲወጡ ኹኔታዎችን ማመቻቸተን የአገሪቱ ጦር ሠራዊት ባወጣው መግለጫ ገልጧል። ሳዑዲ ዓረቢያ ዜጎቿን በሰሜናዊቷ ፖርት ሱዳን በኩል ዛሬ በማስወጣት የመጀመሪያዋ አገር ኾናለች።

4፤ የሱዳን ጦር ሠራዊትና ፈጥኖ ደራሽ ሠራዊት የሚያደርጉት ውጊያ ዛሬም መቀጠሉን የውጭ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች ከትናንት ጀምሮ ለኢድ አልፈጥር በዓል ተግባራዊ እንዲኾን በተናጥል የተስማሙበት የ72 ሰዓታት ተኩስ አቁም ተፈጻሚ ሳይኾን ቀርቷል። ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የፈጥኖ ደራሹ ሠራዊት ዋና አዛዥ ጀኔራል ሞሐመድ ደጋሎ ሙሉ ተኩስ አቁም ስለማድረግና በረድዔት ሠራተኞች ደኅንነት ዙሪያ ከተመድ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ጋር በስልክ እንደተነጋገሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ገልጸዋል።

5፤ የሱማሊያ መንግሥት የአፍሪካ ኅብረት ሰላም ተልዕኮ ከቀጣዩ የፈረንጆች ዓመት መጨረሻ በኋላ ቆይታው በድጋሚ እንዲራዘም ፍቃደኛ መኾኑን ዘ ኢስት አፍሪካን ዘግቧል። የፕሬዝዳንት ሐሰን ሞሐመድ መንግሥት የኅብረቱ ሰላም አስከባሪዎች ቆይታ ይራዘም የሚለውን ጥያቄውን ሰላም አስከባሪ ወታደሮችን ያዋጡ የቀጠናው አገሮችና ዓለማቀፉ ኅብረተሰብ እንዲቀበሉት ማግባባት መጀመሩን ዘገባው ጠቅሷል። አፍሪካ ኅብረት ቀደም ሲል ከሱማሊያ መንግሥት ጋር በደረሰው ስምምነት መሠረት፣ የኅብረቱን ሰላም አስከባሪ ወታደሮች ከመጭው ሰኔ ጀምሮ ደረጃ በደረጃ በመቀነስ በቀጣዩ የፈረንጆች ዓመት ታህሳስ ወር ሙሉ በሙሉ ከአገሪቱ እንዲወጡ ታቅዶ ነበር። #ሼር በማድረግ ተባበሩን


ወሳኝ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ቻናሉን ይቀላቀሉ

                                   @emsmereja