Get Mystery Box with random crypto!

የተዘነጉት በጎጃም የሚገኙት ተፈናቃዮች በጥቃቶችና በጦርነት ተፈናቅለው አማራ ክልል የተጠለሉ ተ | Zemedkun Bekele (ዘመዴ)

የተዘነጉት በጎጃም የሚገኙት ተፈናቃዮች
በጥቃቶችና በጦርነት ተፈናቅለው አማራ ክልል የተጠለሉ ተፈናቃዮች ጤና በየጊዜው እያሽቆለቆለ ነው ተብሏል
በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ የተፈናቀሉ 300 ሽህ የሚደርሱ ዜጎች ተጠልለው ይገኛሉ፡፡ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በተለይም ከወለጋ፣ ከመተከልና ከወልቃይት የተፈናቀሉ ዜጎች ድረሱን እያሉ ናቸው፡፡
በዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች ተበትነውና ከማህበረሰቡ ጋር ተጠግተው አዲሱን መደበኛ ህይወታቸውን የሚመሩት ተፈናቃዮቹ ዛሬና ነገ እያሳሰባቸው ነው፡፡
ኦነግ ሸኔ በምስራቅ ወለጋ ዞን 50 ተፈናቃዮችን መግደሉን ኢሰመኮ ገለጸ
ተፈናቃይ እና ከስደት ተመላሽ ኢትዮጵያዊያንን ለመርዳት 111 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ተባለ
ተፈናቃዮቹ የእለት ጉርስ ማግኘትና የነገ እጣ ፈንታቸው እያስጨነቃቸው መሆኑን ለአል ዐይን ተናግረዋል፡፡ የበጎ አድራጊዎችንና የመንግስትን እጅ ከመጠበቅ ጀምሮ ህይወታቸውን ለማቃናት የጉልበት ስራ እየሰራን ነው ብለዋል፡፡
ተፈናቃዮቹ በእርሻ ስራ ተሰማርተው የነበሩ ሲሆኑ፤ የአፈሩ ሽታና የእህል ጎተራ ናፍቋቸዋል፡፡ ያሉበትን ሁኔታ ሲገልጹም ህይወት በዚህ መንገድ መቀጠል የለባትም ሲሉ ድጋፍን አጥብቀው ሽተዋል፡፡ 
በ40ዎቹ እድሜ አጋማሽ የሚገኙት ደመላሽ አዱኛ ከኦሮሚያ ክልል ወለጋ ጊዳ አያና ወረዳ ተፈናቅለው ምዕራብ ጎጃም ከተበተኑ አያሌ ተፈናቃዮች አንዱ ናቸው፡፡ ለደህንነታቸው ሰግተው ሩብ ክ/ዘመን ከኖሩበት አካባቢ ስድስት ልጆቻቸውን ይዘው ከአካባቢው መፈናቀላቸውን የሚናገሩት ደመላሽ "ልጆቼን ለማዳን ሳይቀጣጠል ቅድሚያ ላኳቸው" ይላሉ፡፡ 
"ልጆቼን ከላኩ በኋላ ምንአልባት ይረጋጋ ከሆነ ብዬ እኔ ወደ ኋላ ቀረሁ፡፡ ነገሩ እየተባባሰ ሲመጣ በእግሬ አቋርጬ ጎጃም ገባሁ" በማለት የተፈናቀሉበትን ቅጽበት ያስረዳሉ፡፡
ሰብዓዊ ድጋፍ ተፈናቅለው ዓመት ከሆናቸው በኋላ በመንግስት 15 ኪሎ ስንዴ ማግኘት መጀመራቸውን ይናገራሉ፡፡ ይህኑ ድጋፍን አሁን ላይ ካገኙ አምስት ወራት ማለፉን የሚናገሩት ደመላሽ አዱኛ "እግዚአብሄር የከፈተውን ጉሮሮ ሳይዘጋው አያድርም" በማለት ኑሯቸውን ይገልጻሉ፡፡ 
ቤት ተከራይው እንደሚኖሩ የሚናገሩት ደመላሽ አዱኛ፤ ወሩ ሲደርስ ኪራይ ለመክፈል ጭንቅ ነው ይላሉ፡፡
"የምናደርገው ነገር ከሌለለ ያው ምንም አማራጭ የለም፡፡ ወደ ዛው ብትሄጂም አሁንም ሰው እየተገደለ ነው፡፡ ይህ ጊዜ ያልፍ ይሆን እያልን በጉጉት እየጠበቅን ነው" ይላሉ፡፡ 
በሰሜኑ ጦርነት ተፈናቅለው እንደመጡ የሚናገሩት ቦጋለ ፈንታ በእርሻ ስራ ይተዳደሩ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ እሳቸውንና አብዛኛው ተፈናቃይ በእሳቸው አጠራር "በስግሰጋ" ቤተሰብ ዘመድ እተሳሳበ ኑራቸውን በአካባቢው መመስረታቸውን ይገልጻሉ፡፡ ለረጅም ዓመታት ከኖሩበትና ቤተሰብ ካፈሩበት አካባቢ በ2013 ዓ.ም. በተቀሰቀሰው ጦርነት ከጀርባቸው የለበሷትን ልብስ እንደያዙ ሀብት ንብረታቸውን ጥለው እግሬ አውጭኝ ማለታቸውን ይናገራሉ፡፡
 "ጦርነቱ ሲነሳ ህብረተሰቡን ማሳደድ ተጀመረ፡፡ የብሄር ጸብ ተነሳ፡፡ አማራጩ መሸሽ ነው፡፡ ድንገት ነበር፡፡ ከሦስት እስከ አራት ቀን ጫካ ያደረ አለ፡፡ እየተሰባሰበ ከዚያም ከዚያም እያለ በአንድ ሳምንትም በሁለትም በወሩም የገባ አለ፡፡ እንደዚህ አድርገን ተሰደድን፡፡" ሲሉ ሁነቱን ይገልጻሉ፡፡
በጎ አድራጊዎችና መንግስት በሚያቀርቡት እርዳታ፣ ከዘመድ ጋር በመጠጋት እንዲሁም የቀን ስራ (የጉልበት ስራ) በመስራት የእለት ጉርስ ለማግኘት እየታገሉ መሆኑን ቦጋለ ፈንታ ተናግረዋል።     
"ህይወት አይገፋ የለም መቼም እየተገፋች ነው፡፡ ቀን ይመሻል፤ ሌሊት ይጠባል፡፡ ምክንያቱም ሰው የሚኖረው ሲደላው ነው፡፡ ሰው መኖር የሚችለው ሲኖረው ነው፡፡ የመኖር ያለመኖር ላይ ነው ጥያቄው፡፡ ሰው ሲፈጠር አንድ ነው፡፡ የሚበላለጠውና የሚተናነሰው ነገር የለም፡፡ ከተወለደና ከአደገ በኋላ ነው ሰው የሚበላለጠው፡፡ ስሜ ቦጋለ ነው፡፡ አሁን ተፈናቃይ ተብዬ ስም ተሰይሚያለሁ፡፡ የተፈናቃይ ልጅ ተብላ ልጄ እስከምትጠራ ድረስ" በማለት ያሉበትን ሁኔታ ገልጸዋል    
እዚህ ግባ የሚባል እርዳታ እየደረሰን አይደለም የሚሉት ሌላው ተፈናቃይ መልካሙ ቁሜ "አሳሳቢ" የሚባል ሁኔታ ላይ ነን ይላሉ፡፡
"ስንዴውም ይህ ነው የሚባል አይደለም፡፡ በቂ አይደለም፡፡ ቋሚ አይደለም፡፡ እንዴውም እኛ ያለንበት ወረዳ ወደ ሌላ ወረዳ ሄዷል ተብሎ ገና አልገባልንም" በማለት ስለ ሰብዓዊ ድጋፉ ይናገራሉ፡፡
የአማራ ክል መንግስትም ግማሽ ሚሊዮን የሚበልጡ ተፈናቃዮች እንዳሉት ገልጾ፤ ሰብዓዊ አቅርቦት ለማድረግ እጅ ያጥረኛል ብሏል፡፡
የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና የቅድመ ማስጠንቀቂያ ምላሽ ዳይሬክተር ብርሀኑ ዘውዱ በአማራ ክልል ስድስት መቶ ስልሳ ሽህ ተፈናቃዮች እንዳሉ ለአል ዐይን ተናግረዋል፡፡ አብዛኞቹም ከኦሮሚያ ክልል የተፈናቀሉ መሆናቸውን የጠቀሱት ኃላፊው፤ ምዕራብ ጎጃምን ጨምሮ አብዛኛው ተፈናቃይ ባለባቸውን ዞኖች መንግስት እርዳታ እንደሚያቀርብ ገልጸዋል።   
ሰብዓዊ እርዳታው በቂ አለመሆኑን የሚያነሱት ኃላፊው፤ ይህም ከመንግስት አቅም ጋር የሚያያዝ ነው ብለዋል፡፡ እርዳታ በማጠሩ በየወሩ መሰጠት የነበረት እርዳታ ወራትን ከመሸገር አልፎ ዱካው የሚጠፋበት ጊዜ እንዳለም አልሸሸጉም፡፡ 
ክልሉ ለተፈናቃዮች እርዳታ ማቅረብ የአንድ ዞን ህዝብ መመገብ ማለት በመሆኑ ከብዶኛል ብሏል፡፡
ቀዳዳውን ለመሸፈን የክልሉን መጠባበቂያ በጀት እየተጠቀሙ መሆናቸውን የሚጠቁሙት ብርሀኑ ዘውዱ፤ "ማስታገሻ" እየሰጠን ነው ይላሉ፡፡
"ቢያንስ ሰው እንዳይሞት ነው እየሰጠን ያለነው፡፡ ጤናን ለመጠበቅ የሚያስፈለግ አቅርቦትን በተመለከተ ሰፊ ክፍተት ነው ያለው፡፡ በእናቶችና ህጻናት ያለው የስነ-ምግብ መጓደል [የተመጣጠነ ምግብ እጥረት] በየዓመቱ ከፍ እያለ ነው፡፡ ይሄ ማለት ባይሞቱም ጤናቸው ላይ ተጽዕኖ እያደረ ነው" ብለዋል፡፡
ተፈናቃዮቹ ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲቀርብላቸው እየወተወቱ ነው፡፡
ተፈናቃዮቹ ከእለት ጉርስ ባሻገርም በዘላቂነት የሚቋቋሙበትን ጊዜና ሁኔታ እየናፈቁ ናቸው፡፡ በሰሜኑ ጦርነቱ የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀያቸው ለመመለስ በመንግስት ተስፋ እንደተሰጣቸው ለአል ዐይን ተናግረዋል፡፡
የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን ተፈናቃዮን ማቋቋም ከክልሉ አቅም በላይ መሆኑን በማንሳት ኃላፊነቱ በፌደራል መንግስቱ ትከሻ ላይ ያረፈ መሆኑን ጠቁመሟል፡፡ መልዕክቱን #ሼር በማድረግ ተባበሩን


ወሳኝ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ቻናሉን ይቀላቀሉ

                                   @emsmereja
ለማስታወቂያ ስራና ለመረጃ ጥቆማዎች @infoetrobot ይህን ይጠቀሙ
አል አይን