Get Mystery Box with random crypto!

ሐሙስ ምሽት! ሚያዝያ 12/2015 ዓ.ም የEMS ዐበይት ዜናዎች 1፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ በ | Zemedkun Bekele (ዘመዴ)

ሐሙስ ምሽት! ሚያዝያ 12/2015 ዓ.ም የEMS ዐበይት ዜናዎች

1፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ በኢትዮጵያ እና ሱዳን መካከል "ግጭት መቀስቀስ የሚፈልጉ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ" አዲስ ባወጡት መግለጫ አስጠንቅቀዋል። ዐቢይ አንዳንድ አካላት የኢትዮጵያና ሱዳን ግንኙነትንና በወንድማማችነት ላይ የተመሠረተ ጉርብትና ለማበላሸት፣ "ኢትዮጵያ ወታደሮቿን ሱዳን ውስጥ አስገብታለች በማለት ሐሰተኛ መረጄ እያሠራጩ ነው" በማለት ከሰዋል። የኢትዮጵያና ሱዳን የድንበር ውዝግብ በንግግር ይፈታል ያሉት ዐቢይ፣ "ኢትዮጵያ የሱዳንን ወቅታዊ ነባራዊ ሁኔታ ለውዝግቡ መጠቀሚያ ልታደርገው አትፈልግም" ብለዋል። አንዳንድ ወገኖች ኢትዮጵያ በአስቸጋሪ ኹኔታ ውስጥ በነበረችበት ወቅት "ሉዓላዊነቷን በመጣስና መሬቷን በኃይል በመቆጣጠር የፈጸሙትን ድርጊት ኢትዮጵያ በሱዳን ላይ እንደማትፈጽም ዐቢይ ገልጸዋል።

2፤ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የጦር ጉዳተኞች ምክር ቤት ማቋቋሙን አስታውቋል። የክልሉ አስተዳደር ምክር ቤቱን ያቋቋመው፣ የጦር ጉዳተኞችንና በጦርነቱ ተዋጊዎች የሞቱባቸውን ቤተሰቦች ለመርዳት እንደኾነ የክልሉ ቴሌቪዥን ዘግቧል። የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ፣ አስተዳደሩ ለጦር ጉዳተኞች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ካምፕ ውስጥ የሚገኙ የጦር ጉዳተኞች ባለፈው ወር በመቀሌ ከተማ በሰላማዊ ሰልፍ ችግራቸውን በገለጹበት ወቅት ቃል መግባታቸው ይታወሳል።

3፤ በካርቱም የኢትዮጵያ ኢምባሲ በሱዳን የሚኖሩ ኢትዮጵያዊን ዜጎችን ደኅንነት ለማስጠበቅ ጥረት እያደረገ መኾኑን ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር መግለጡን የመንግሥት ዜና አውታሮች ዘግበዋል። መንግሥት በሱዳን የሚኖሩ ዜጎችን ደኅንነት ለመከታተል እንዲያመቸው፣ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማትና የሱዳን አጎራባች ከኾኑ ክልላዊ መንግሥታት የተውጣጣ ግብረ ኃይል ማቋቋሙን ሚንስቴሩ ይፋ ማድረጉንም ዘገባዎቹ አመልክተዋል። በሱዳን የኢትዮጵያ ኢምባሲ በበኩሉ፣ በግጭቱ የተገደሉ ኢትዮጵያዊያን ስለመኖራቸው መረጃ እንደደረሰው ገልጦ ነበር።

4፤ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሠራዊት አዛዥ ጀኔራል ሞሐመድ ደጋሎ ከአገሪቱ ጦር ሠራዊት ዋና አዛዥ ጀኔራል ቡርሃን ጋር ለድርድር አልቀመጥም ማለታቸውን አልጀዚራ ዘግቧል። ግጭቱን የጀመሩት ጀኔራል ቡርሃን ናቸው ያሉት ጀኔራል ደጋሎ፣ ወደፊትም ከባላንጣቸው ጋር ድርድር እንደማይኖር መግለጻቸውን ዘገባው ጠቅሷል። የሱዳን ጦር ሠራዊትም፣ ከፈጥኖ ደራሽ ሠራዊቱ ጋር የሚደረግን ድርድር ውድቅ አድርጓል። ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ጥሪ ብናደርግም የጦር ሠራዊቱ አዛዦች ግን ተኩስ አቁም አይፈልጉም ያሉት ጀኔራል ደጋሎ፣ ነገ ለሚከበረው ኢድ አልፈጥር በዓል ተኩስ አቁም ቢደረግ ተቃውሞ የለንም ማለታቸው ተገልጧል። ጀኔራል ደጋሎ ሠራዊታቸው ከሩሲያው የግል ወታደራዊ ኩባንያ "ዋግነር" ድጋፍ ያገኛል መባሉን አስተባብለዋል።

5፤ የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር በሱዳን ጦር ሠራዊትና በፈጥኖ ደራሹ ሠራዊት ላይ ማዕቀብ ለመጣል እያሰላሰለ መኾኑን ፎሬን ፖሊሲ መጽሄት ዘግቧል። ዛሬ ስድስተኛ ቀኑን በያዘው የሁለቱ ወገኖች ውጊያ ዛሬ ስድስተኛ ቀኑን የያዘ ሲሆን፣ የዓለም ጤና ድርጅት በግጭቱ 330 ሰዎች መገደላቸውንና 3 ሺህ 200 ሰዎች መቁሰላቸውን አስታውቋል። በሺዎች የሚቆጠሩ የካርቱም ነዋሪዎች ውጊያውን በመሸሽ ከተማዋን ለቀው እየወጡ እንደኾነ ተነግሯል።

6፤ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 54 ብር ከ0852 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 55 ብር ከ1669 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ በድረገጹ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 64 ብር ከ0425 ሳንቲም እና መሸጫው 65 ብር ከ3234 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ59 ብር ከ1043 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ60 ብር ከ2864 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል። #ሼር በማድረግ ተባበሩን


ወሳኝ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ቻናሉን ይቀላቀሉ

                                   @emsmereja
ለማስታወቂያ ስራና ለመረጃ ጥቆማዎች @infoetrobot ይህን ይጠቀሙ