Get Mystery Box with random crypto!

ረቡዕ ምሽት! ሚያዝያ 11/2015 ዓ.ም የEMS Mereja ዐበይት ዜናዎች 1፤ የተመድ ዋና ጸሃ | Zemedkun Bekele (ዘመዴ)

ረቡዕ ምሽት! ሚያዝያ 11/2015 ዓ.ም የEMS Mereja ዐበይት ዜናዎች

1፤ የተመድ ዋና ጸሃፊ አንቴኒዮ ጉተሬዝ ባለፈው የካቲት ወደ ኢትዮጵያ በሄዱ ጊዜ ትግራይን እንዳይጎበኙ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ደመቀ ቀደም ብለው በጻፉላቸው ደብዳቤ እንደተከለከሉ ዋሽንግተን ፖስት ከአሜሪካ መንግሥት ካፈተለኩት ሚስጢራዊ የስለላ መረጃዎች ተመልክቻለሁ ሲል አስነብቧል። መንግሥት ጉተሬዝ ትግራይን እንዲጎበኙ ባለመፍቀዱ፣ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ይቅርታ እንደጠየቋቸው ጉተሬዝ ለተመድ ባለሥልጣናት ስለመናገራቸው ዘገባው ጠቅሷል። ጉተሬዝ የጉብኝት እቅዳቸውን መከልከላቸውን እንዳወቁ፣ ቅሬታቸውን በተመድ ለኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ለመግለጽ ፈልገው እንደነበር ተገልጧል።

2፤ የብሄራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምኅረቱ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብር ከዓለም ገንዘብ ድርጅትና ዓለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ ውጭም ቢኾን ይቀጥላል ሲሉ በአሜሪካው ሀርቫርድ ዪኒቨርሰቲ ባደረጉት ንግግር ላይ መግለጣቸውን ሪፖርተር አስነብቧል።
አሜሪካ የሚገኘው የመንግሥት ልዑካን ቡድን በከፍተኛ የዕዳ ጫና፣ የኑሮ ውድነት፣ ያልተመጣጠነ የውጭ ምንዛሬና የውጭ ብድር ዙሪያ ከሁለቱ ተቋማት ጋር እየተነጋገረ ስለመኾኑ ማሞ መጥቀሳቸውን ዘገባው አመልክቷል። ማሻሻያዎቹ በመንግሥት አገር በቀል የኢኮኖሚ መርሃ ግብር ማዕቀፍ እንደሚከናወኑ ማሞ እንደገለጡ ያመለከተው ዘገባው፣ ኾኖም ማሻሻያዎቹን በተሟላ አኳኋን ለመተግበር የውጭ ድጋፍ ያስፈልገናል ማለታቸውን ጠቅሷል። ማሞ ይህን የተናገሩት፣ እሳቸውና ገንዘብ ሚንስትር አሕመድ ሽዴ የመሩት ልዐካን ቡድን በዓለም ባንክና የዓለም ገንዘብ ድርጅት ስብሰባ ላይ ባለፈው ሳምንት ከተካፈለ በኋላ ነው።

3፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ዛሬ የግጭት ቀጠና ኾኖ በከረመው ምሥራቅ ወለጋ ዞን በነቀምት ከተማ ጉብኝት ማድረጋቸውን የጠቅላይ ሚንስትር ጽሕፈት ቤት በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባሰራጨው መረጃ አስታውቋል። ዐቢይ በነቀምት ቆይታቸው፣ ከከተማዋ ነዋሪዎች ጋር መወያየታቸው የተገለጠ ቢኾንም፣ ስለ ጉብኝቱ ዓላማና ስለ ውይይቱ ጽሕፈት ቤቱ ዝርዝር መረጃ አልሰጠም። ከዐቢይ ጋር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሠ ጫፎ እና የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ በጉብኝቱ ላይ ተሳትፈዋል ተብሏል።

4፤ በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የክልሉ ትምህርት ቢሮ በመጭው ሚያዝያ 23 የመማር ማስተማር ሥራ ይጀምራሉ ማለቱን የክልሉ ቴሌቪዥን ዘግቧል። በዕለቱ ትምህርት የሚጀምሩት፣ በክልሉ የሚገኙ ከ1ኛ እስከ 12ኛ ክፍሎች የሚያስተምሩ ትምህርት ቤቶች በሙሉ እንደኾኑ ዘገባው አመልክቷል።

5፤ ጀኔራል ሞሐመድ ደጋሎ የሚመሩት የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሠራዊት ዛሬ ከምሽቱ 12:00 ሰዓት ጀምሮ የሚጸና የ24 ሰዓት ተኩስ አቁም ለማድረግ ዝግጁ መኾኑን ከቀትር በኋላ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ጀኔራል አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን የሚመሩት የሱዳን ጦር ሠራዊት ግን፣ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ ስለ ተኩስ አቁም ጥሪው ምላሽ እንዳልሰጠ ታውቋል። ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች የ24 ሰዓት ተኩስ አቁም ለማድረግ ትናንት በተናጥል የደረሱበት ውሳኔ ተግባራዊ ሳይኾን ቀርቷል። ፈጥኖ ደራሽ ሠራዊቱ ሙሉ ተኩስ አቁም ለማድረግ ዝግጁ መኾኑንም በትዊተር ገጹ ገልጧል።

6፤ ኢጋድ ለሱዳኑ ግጭት ሰላማዊ መፍትሄ ለማፈላለግ የሰየማቸው የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ፣ የጅቡቲው ፕሬዝዳንት እስማዔል ጌሌ እና የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ዛሬ ካርቱም ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል። ዛሬ አምስተኛ ቀኑን በያዘው የሱዳን ጦር ሠራዊትና ፈጥኖ ደራሽ ሠራዊት ግጭት 270 ሰዎች እንደተገደሉና ከ2 ሺህ 500 በላይ ሰዎች እንደቆሰሉ የውጭ ዜና ምንጮች የዓለም ጤና ፕሮግራምን ጠቅሰው ዘግበዋል። በርካታ የካርቱም ነዋሪዎች ግጭቱን በመሸሽ፣ ከተማዋን ለቀው እየወጡ መኾኑን ዘገባዎች አመልክተዋል። ዛሬ በካርቱም የከባድ መሳሪያ ውጊያ እየተካሄደ ያለው፣ በዋናነት በጦር ሠራዊቱ ጠቅላይ መምሪያና አውሮፕላን ማረፊያው ውስጥ እንደኾነ ተገልጧል።

7፤ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 54 ብር ከ0679 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 55 ብር ከ1493 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ በድረገጹ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 64 ብር ከ2123 ሳንቲም እና መሸጫው 65 ብር ከ4974 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ59 ብር ከ3449 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ60 ብር ከ5318 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል። #ሼር በማድረግ ተባበሩን


ወሳኝ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ቻናሉን ይቀላቀሉ

                                   @emsmereja
ለማስታወቂያ ስራና ለመረጃ ጥቆማዎች @infoetrobot ይህን ይጠቀሙ