Get Mystery Box with random crypto!

ረቡዕ ማለዳ! ሚያዝያ 11/2015 ዓ.ም የEMS Mereja ዐበይት ዜናዎች 1፤ በሱዳን የኢትዮጵ | Zemedkun Bekele (ዘመዴ)

ረቡዕ ማለዳ! ሚያዝያ 11/2015 ዓ.ም የEMS Mereja ዐበይት ዜናዎች

1፤ በሱዳን የኢትዮጵያ ኢምባሲ በሱዳን ጦር ሠራዊትና በፈጥኖ ደራሽ ሠራዊት ውጊያ ከተገደሉት ሰላማዊ ሰዎች መካከል ኢትዮጵያዊያን እንደሚገኙበት መረጃዎች ደርሰውኛል ሲል በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባሰራጨው መረጃ አስታውቋል። ኾኖም ኢምባሲው እስከ ትናንት ባገኘው መረጃ ስንት ኢትዮጵያዊያን በግጭቱ ሕይወታቸውን እንዳጡ አልገለጠም። ዶይቸቨለ ግን፣ ካርቱም ውስጥ አራት ወይም አምስት ኢትዮጵያዊያን በከባድ መሳሪያ ፍንጣሪ እንደተገደሉ ከዓይን ምስክሮች መስማቱን ጠቅሶ ዘግቧል።

2፤ የሩሲያው የግል ወታደራዊ ኩባንያ ዋግነር ግሩፕ ሱዳን ውስጥ ቅጥረኛ ተዋጊዎቼን እንዳላሠማራ መናገሩን የውጭ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ኩባንያው ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በሱዳን ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ የለኝም ማለቱን ዘገባዎቹ ጠቅሰዋል። ከሩሲያ መንግሥት ጋር ግንኙነት እንዳለው የሚነገርለት ወታደራዊ ኩባንያው፣ በተለይ ከሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሠራዊት አዛዥ ጀኔራል ሞሐመድ ደጋሎ ጋር በቅርብ እንደሚሠራ ሲነገር ቆይቷል።

3፤ የሱዳን ጦር ሠራዊት እና ፈጥኖ ደራሽ ሠራዊት የ24 ሰዓት ተኩስ አቁም ለማድረግ ትናንት ምሽት የደረሱበት የ24 ሰዓት ተኩስ አቁም ስምምነት ሙሉ በሙሉ እንዳልተከበረ የተለያዩ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ተኩስ አቁሙ ትናንት ምሽት ከ12:00 ሰዓት ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚኾን ተጠብቆ ነበር። የተመድ የዕርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮ ሃላፊ ማርቲን ግሪፊትስ፣ በግጭቱ በረድዔት ሠራተኞች ላይ የጾታ ጥቃት እየተፈጸመ ስለመኾኑ መናገራቸውን ዘገባዎች አመልክተዋል። ከሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች ማን ወታደራዊ የበላይነት እንደያዘ እስከ ትናንት ድረስ አልታወቀም።

4፤ ቦይንግ ኩባንያ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖቹን በከፍተኛ መጠን ለማምረት የያዘውን ዕቅድ እንደሚገፋበት መግለጡን ብሉምበርግ ዘግቧል። ኩባንያው ይህን አቋሙን የገለጠው፣ የታዘዛቸውን 737 ማክስ አውሮፕላኖች የኋለኛው ክፍል ተገጣጣሚዎች ላይ እክል እንዳጋጠመውና አዲስ አውሮፕላኖችን በታቀደው ጊዜ ለደንበኞቹ ለማስረከብ ከፍተኛ የጊዜ መዘግየት እንደሚያጋጥመው በተናገረ ማግስት ነው። ኩባንያው፣ የመገጣጠሚያ እክል ባለባቸው ባለፉት አራት ዓመታት በተመረቱ ከ550 እስከ 800 የሚገመቱ አውሮፕላኖች ላይ እንደገና ፍተሻ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጧል።

5፤ ጃፓን በሒሮሺማ ከተማ ከቀጣዩ ግንቦት 11 እስከ 13 በምታስተናግደው የቡድን-7 የበለጸጉ አገሮች ጉባኤ ላይ ደቡብ አፍሪካን ሳትጋብዝ ቀርታለች። ጃፓን በደቡብ አፍሪካ ፋንታ አፍሪካ ኅብረትን እንደጋበዘችና የኅብረቱ የወቅቱ ሊቀመንበር የኮሞሮሱ ፕሬዝዳንት አዛሊ አሱማኒ ኅብረቱን ወክለው እንደሚገኙ "ኒውስ 24" ዘግቧል። ደቡብ አፍሪካ በቡድን-7 ስብሰባ ላይ ለበርካታ ዓመታት ስትጋበዝ ነበር። ደቡብ አፍሪካ በዩክሬኑ ጦርነት ድጋፏን ለሩሲያ ሰጥታለች የሚል ውግዘት ከምዕራባዊያን አገራት ሲቀርብባት መቆየቱ ይታወሳል። #ሼር በማድረግ ተባበሩን


ወሳኝ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ቻናሉን ይቀላቀሉ

                                   @emsmereja
ለማስታወቂያ ስራና ለመረጃ ጥቆማዎች @infoetrobot ይህን ይጠቀሙ