Get Mystery Box with random crypto!

ማክሰኞ ማለዳ! ሚያዝያ 10/2015 ዓ.ም የEMS Mereja ዐበይት ዜናዎች 1፤ የትግራይ ክልል | Zemedkun Bekele (ዘመዴ)

ማክሰኞ ማለዳ! ሚያዝያ 10/2015 ዓ.ም የEMS Mereja ዐበይት ዜናዎች

1፤ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ከጠላት ጋር መተባበርን ጨምሮ ሕወሃት በጦርነቱ ወቅት ባወጣቸው 30 ክልከላዎች የታሠሩ ግለሰቦችን ለመፍታት መወሰኑን ቪኦኤ ዘግቧል። ውሳኔው ምርመራ ላይ የሚገኙ፣ በክስ ሂደት ያሉና በፍርድ ቤት ውሳኔ የታሠሩ ግለሰቦችን እንደሚመለከት ቢሮው መናገሩን የገለጠው ዘገባው፣ ሰው የገደሉ፣ ጾታዊ ጥቃት ያደረሱ ወይም ከኤርትራ ጋር የተባበሩ ግን ውሳኔው አይመለከታቸውም መባሉን ዘገባው ጠቅሷል። በውሳኔው መሠረት የሚፈተት እስረኞች ብዛት ስንት እንደኾነ ግን ቢሮው አልተገለጠም ተብሏል። የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር እስረኞችን ለመፍታት የወሰነው የሰላም ስምምነት ከተፈረመ በኋላ በእስር ላይ መቆየታቸው አስፈላጊ ስላልኾነ መኾኑን ቢሮው መግለጡን ዘገባው ጨምሮ አመልክቷል።

2፤ የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን በሱማሌ ክልል በኩል በኮንትሮባንድ ወደ ውጭ የሚወጣውን የጫት ምርት ለማስቆም ክልሉ ሊተባበረኝ አልፈቀደም ማለቱን ሪፖርተር አስነብቧል። በክልሉ በኩል ጫት ወደ ውጭ የሚወጣው፣ "ለአገር ውፍጆታ ነው" በሚል ሽፋን መኾኑን ኮሚሽኑ መግለጡንና፣ ጫት በሕጋዊ መንገድ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ለሚደረገው ጥረት ጭምር የክልሉ ጸጥታ ኃይሎች ተባባሪ እንዳልኾኑ መናገሩን ዘገባው አመልክቷል። በክልሉ ሲቲ ዞን ውስጥ የጫት ኮንትሮባንድ ነጋዴዎች ከታጠቁ ሚሊሻዎች ድጋፍ እንደሚያገኙ ኮሚሽኑ መግለጡንም ዘገባው አስነብቧል።

3፤ ተመድ በሱዳን ጦር ሠራዊትና በፈጥኖ ደራሽ ሠራዊቱ መካከል በቀጠለው ግጭት ከ180 በላይ ሰዎች መገደላቸውንና ከ1800 በላይ ሰዎች መቁሰላቸውን አስታውቋል። አሜሪካ የሱዳኑ ግጭት ባስቸኳይ እንዲቆም ከጀኔራል ቡርሃንና ከጀኔራል ሞሐመድ ደጋሎ ጋር ግንኙነት እያደረገች መኾኗን አስታውቃለች። የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በበኩሉ፣ ግጭቱ ሱዳናዊያን ብቻ የሚፈቱት የውስጥ ጉዳይ ነው ሲል ትናንት ማምሻውን አስታውቋል። ሚንስቴሩ፣ የሱዳን ጦር ሠራዊት ወታደራዊ ጠቅላይ መምሪያውን፣ ቤተ መንግሥቱን፣ የካርቱም አውሮፕላን ማረፊያንና ብሄራዊ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ጣቢያውን "አማጺ" ሲል ከፈረጀው ፈጥኖ ደራሽ ሠራዊት ማስለቀቁን የገለጠ ሲሆን፣ የጀኔራል ደጋሎ ኃይሎች ግን ያስተባብላሉ።

4፤ የሱዳን ጦር ሠራዊት ዋና አዛዥ ጀኔራል ቡርሃን ጀኔሬል ሞሐመድ ደጋሎ የሚመሩት ፈጥኖ ደራሽ ሠራዊት የከፈተው ጥቃት "የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ" እና "በአገሪቱ ላይ የተቃጣ ጥቃት" ነው ሲሉ መናገራቸውን ለሲ ኤን ኤን ዘግቧል። ጀኔራል ቡርሃን፣ ፈጥኖ ደራሽ ሠራዊቱ በጦር ሠራዊቱ ጠቅላይ መምሪያ ላይ ጥቃት የፈጰመው፣ እሳቸውን ለመግደል መኾኑን መናገራቸውን ዘገባው አመልክቷል። የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሠራዊት በበኩሉ፣ ባሁኑ ወቅት ተኩስ አቁም ለማድረግ ዝግጁ አለመኾኑን መናገሩን ብሉምበርግ ዘግቧል።

5፤ ብሪታኒያ "ሕገወጥ" ያለቻቸውን ጥገኝነት ጠያቂዎች ሩዋንዳ ውስጥ ለማስፈር ሁለቱ አገሮች የደረሱበትን ስምምነት ማሻሻላቸውን ዘ ኢስት አፍሪካን ጋዜጣ ዘግቧል። በስምምነቱ ላይ አዲስ በተጨመረው አንቀጽ መሠረት፣ ብሪታኒያ ጥገኝነት ያልጠየቁ ስደተኞችንና ፍልሰተኞችን ጭምር ወደ ሩዋንዳ እንደምትልክ ዘገባው ጠቅሷል። ማሻሻያው፣ ሩዋንዳ ጥገኝነት ያልጠየቁ ስደተኞችን ከተቀበለች በኋላ ወደ አገራቸው እንድትልካቸው መብት እንደሚሰጣት ዘገባው ጠቅሷል። የብሪታኒያ ፍርድ ቤት ጥገኝነት ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ የመላኩ ውሳኔ ሕጋዊ ነው በማለት መወሰኑ ይታወሳል። #ሼር በማድረግ ተባበሩን


ወሳኝ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ቻናሉን ይቀላቀሉ

                                   @emsmereja
ለማስታወቂያ ስራና ለመረጃ ጥቆማዎች @infoetrobot ይህን ይጠቀሙ