Get Mystery Box with random crypto!

ሰኞ ምሽት! ሚያዝያ 9/2015 ዓ.ም የEMS Mereja ዐበይት ዜናዎች 1፤ የኢትዮጵያ መገናኛ | Zemedkun Bekele (ዘመዴ)

ሰኞ ምሽት! ሚያዝያ 9/2015 ዓ.ም የEMS Mereja ዐበይት ዜናዎች

1፤ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ምክር ቤት በጋዜጠኞች ላይ የሚመሠረቱ ክሶች "በመገናኛ ብዙኀን አዋጅ ብቻ" እንዲታዩ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ጠይቋል። ምክር ቤቱ በታሠሩ ጋዜጠኞች ላይ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እየተፈቀደባቸው መታሠራቸው "ተቀባይነት የሌለው ነው" በማለት ድርጊቱን አውግዟል። ጋዜጠኞች በመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች "ከሕግ አግባብ ውጭ መያዛቸው፣ መታፈናቸውን" የጠቀሰው ምክር ቤቱ፣ የመገናኛ ብዙኀን ተቋማት "ያለ ፍርድ ቤት ማዘዣ ብርበራ" እንደሚፈጸምባቸው አመልክቷል።

2፤ የኢትዮጵያ መንግሥት በሳዑዲ ዓረቢያ በቤት ሠራተኛነት ቀጥረው የሚሠሩ ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 40 የሚኾኑ 500 ሺህ ሠራተኞችን እየመለመለ መኾኑን አልጀዚራ ዘግቧል። አማራ ክልል ብቻ 150 ሺህ አመልካቾችን እንዲመዘግብ በመንግሥት መታዘዙን መናገሩን ዘገባው አመልክቷል። ተቀጣሪ ሠራተኞች ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ በመንግሥት ወጪ እንደሚጓዙና ወርሃዊ ደመወዛቸው 1 ሺህ የሳዑዲ ሪያል ወይም 266 የአሜሪካ ዶላር እንደሚኾን ዘገባው አመልክቷል። መንግሥት አመልካቾች እንዲመዘገቡ በተለያዩ ከተሞች ጥሪ ሲያደርግ ሰንብቷል ተብሏል።

3፤ በሱዳን ጦር ሠራዊትና በፈጥኖ ደራሹ ሠራዊት መካከል ከቅዳሜ ጀምሮ በቀጠለው ግጭት በትንሹ 97 ሰላማዊ ሰዎችና 45 ወታደሮች መገደላቸውንና ከ940 በላይ ሰዎች መቁሰላቸውን የሱዳን ሐኪሞች ቡድን ማስታወቁን ሮይተርስ ዘግቧል። ዛሬ ካርቱም ውስጥ በጦር ሠራዊቱ ዋና ወታደራዊ ማዘዣ ጣቢያ አካባቢ ውጊያ ሲካሄድ መዋሉን የጠቀሰው ዘገባው፣ የሱዳን ጦር ሠራዊት ብሄራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያውን መልሶ መቆጣጠሩ አመልክቷል። የፈጥኖ ደራሹ ሠራዊት ዋና አዛዥ ጀኔራል ሞሐመድ ሐሚቲ፣ ዓለማቀፉ ኅብረተሰብ "እስላማዊ አክራሪ" እና "ወንጀለኛ" ባሏቸው በባላንጣቸው የጦር ሠራዊቱ ዋና አዛዥ ጀኔራል ቡርሃን ላይ ርምጃ እንዲወስድ በትዊተር መልዕክታቸው ጠይቀዋል።

4፤ ኢጋድ በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም ለተቀሰቀሰው ከባድ ግጭት ሰላማዊ መፍትሄ ለማፈላለግ ከፍተኛ የመሪዎች ልዑካን ቡድን ሊልክ እንደኾነ አስታውቋል። ኢጋድ ወደ ካርቱም የሚልከው፣ የደቡብ ሱዳኑን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪርን፣ የጅቡቲውን ኡመር ጌሌንና የኬንያውን ዊሊያም ሩቶን እንደኾነ ገልጧል። የኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱማሊያና ጅቡቲ መሪዎች ትናንት ባደረጉት የበይነ መረብ ውይይት፣ የአገሪቱ ጦር ሠራዊት እና ፈጥኖ ደራሽ ሠራዊት ግጭቱን ባስቸኳይ አቁመሙ ንግግር እንዲጀምሩና የሰብዓዊ ዕርዳታ ኮሪደሮችን እንዲከፍቱ ጥሪ አድርገዋል።
አፍሪካ ኅብረትም፣ የኮሚሽኑን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማኅተማን ወደ ካርቱም እንደሚልክ አስታውቋል።

5፤ 15 የሱማሊያ ዓለማቀፍ አጋሮች የሱማሌላንድ ራስ ገዝ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ በላስ አኖድ ከተማ ለቀጠለው ግጭት "ያለምንም ቅድመ ሁኔታ አስቸኳይ ተኩስ አቁም እንዲያውጁ በጋራ ባወጡት መግለጫ ጠይቀዋል። ዓለማቀፍ አጋሮች፣ የራስ ገዟ ወታደሮችና ተቃዋሚ የጎሳ ሚሊሻዎች በጋራ ስምምነት ወደሚደረስባቸው ቦታዎች ተዋጊዎቻቸውን እንዲያሸሹ ጥሪ አድርገዋል። ፕሬዝዳንት ቢሂ ግን፣ ወታደሮቻቸውን ከላስ አኖድ ከተማ እንዲያስወጡ የቀረበላቸውን ጥሪ እንዳልተቀበሉት የሱማሊያ ዜና ምንጮች ዘግበዋል።

6፤ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 54 ብር ከ0403 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 55 ብር ከ1211 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ በድረገጹ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 64 ብር ከ5364 ሳንቲም እና መሸጫው 65 ብር ከ8271 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ59 ብር ከ5308 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ60 ብር ከ7214 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል። #ሼር በማድረግ ተባበሩን


ወሳኝ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ቻናሉን ይቀላቀሉ

                                   @emsmereja
ለማስታወቂያ ስራና ለመረጃ ጥቆማዎች @infoetrobot ይህን ይጠቀሙ