Get Mystery Box with random crypto!

ሰኞ ምሽት! ሰኔ 12/2015 ዓ.ም የEMS ዐበይት ዜናዎች 1፤ ምርጫ ቦርድ ዛሬ በደቡብ ክልል | Zemedkun Bekele (ዘመዴ)

ሰኞ ምሽት! ሰኔ 12/2015 ዓ.ም የEMS ዐበይት ዜናዎች

1፤ ምርጫ ቦርድ ዛሬ በደቡብ ክልል ወላይታ ዞን በድጋሚ ሲያካሂድ የዋለውን የክልልነት ሕዝበ ውሳኔ ድምጽ አሰጣጥ የሰዓት ገደብ ከምሽቱ 12 ሰዓት ወደ 1 ሰዓት ማራዘሙን አስታውቋል። የዞኑ ድምጽ ሰጭዎች ድምጽ ሲሰጡ የዋሉት፣ ወላይታ ዞን ባለፈው ጥር 29 ቀን ሕዝበ ውሳኔ ካካሄዱት ሌሎች አምስት ዞኖችና አምስት ልዩ ወረዳዎች ጋር በጋራ አንድ ራሱን ያቻለ ክልል እንዲያቋቁም "እደግፋለኹ" ወይም "አልደግፍም" በሚሉ አማራጮች ላይ ነው። ቦርዱ ዛሬ በዞኑ በድጋሚ ሕዝበ ውሳኔ ያካሄደው፣ ጥር 29 በዞኑ የተካሄደው ሕዝበ ውሳኔ "መጠነ ሰፊ የሕግ ጥሰት" ታይቶበታል በማለት ውጤቱን በመሰረዙ ነው። ሌሎች አምስት ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ግን ከደቡብ ክልል ተነጥለው ራሱን የቻለ አዲስ ክልል ለማቋቋም በአብላጫ ድምጽ መወሰናቸው ይታወሳል።

2፤ ምርጫ ቦርድ ዛሬ በደቡብ ክልል ወላይታ ዞን በድጋሚ ሲያካሂድ በዋለው የክልልነት ሕዝበ ውሳኔ ዙሪያ ምሽት 2:00 ሰዓት ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጥ አስታውቋል። ቦርዱ ከአዲስ አበባ 5 ሺህ 215 እንዲኹም ከወላይታ ዞን 3 ሺህ 845 የምርጫ አስፈጻሚዎችን ለሕዝበ ውሳኔው ማሠማራቱንና በዞኑ በጠቅላላው በ1 ሺህ 812 ጣቢያዎች ድምጽ ሰጪዎች ድምጽ ሲሰጡ እንደዋሉ በሌላ መግለጫው ገልጧል። ሦስት የአገር ውስጥ ሲቪክ ተቋማት 214 ታዛቢዎችን በዞኑ ማሠማራታቸውንም ቦርዱ ጠቅሷል። በርካታ ድምጽ ሰጪዎች ስድስት ወር ያልሞላው መታወቂያ ይዘው መገኘታቸውን የጠቀሰው ቦርዱ፣ መራጮቹ ሦስት የሰው ምስክሮችን አቅርበው ድምጽ እንዲሰጡ ተደርጓል ብሏል።

3፤ በአማራ ክልል ስር ራሱን "የወልቃይት ጠገዴ ዞን" በማለት ያዋቀረው አስተዳደር ምክትል ሊቀመንበር ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ከግጭት ማቆም ስምምነቱ በኋላ አስተዳደሩ ከወልቃይት ጠገዴ አካባቢ የትግራይ ተወላጆችን አላፈናቀለም በማለት ማስተባበላቸውን ቢቢሲ አማርኛ ዘግቧል። ከአካባቢው ለቀው የሚሄዱ የትግራይ ተወላጆች "በራሳቸው ፍቃድ ብቻ" ለቀው የሚሄዱ መኾናቸውን ደመቀ ጠቅሰው፣ በአካባቢው በርካታ የትግራይ ተወላጆች አኹንም እየኖሩ መኾኑን ማንም አካል በአካል መጥቶ ማረጋገጥ ይችላል ማለታቸውን ዘገባው አመልክቷል። ሂውማን ራይትስ ዎችና አምነስቲ ኢንተርናሽናል ኮሎኔል ደመቀ አኹንም የትግራይ ተወላጆችን ከአካባቢው በግዳጅ ያፈናቅላሉ በማለት በቅርቡ ላቀረቡባቸው ውንጀላ፣ ድርጅቶቹ በወልቃይት ጉዳይ ላይ "የሕወሃት ቃል አቀባይ እንጂ የመብት ተሟጋቾች" አልኾኑም በማለት መክሰሳቸውን ዘገባው ጨምሮ ጠቅሷል። የወልቃይት ጥያቄ ከሕዝበ ውሳኔ ይልቅ፣ ታሪክንና ሕግን መሠረት ያደረገ ሕጋዊ ምላሽ እንዲሰጠው እንደሚፈልጉ ደመቀ ተናግረዋል ተብሏል።

4፤ በኢትዮጵያ ለዘንድሮው የምርት ዘመን ከፍተኛ የአፈር ማዳበሪያ እጥረት በመከሰቱ በተለይ በአማራ ክልል አርሶ አደሮች የማዳበሪያ ጥያቄያቸውን በሰላማዊ ሰልፍ እስከማቅረብ ደርሰዋል። በአገሪቱ የአፈር ማዳበሪያ እጥረት መከሰቱን ያመነው ግብርና ሚንስቴር፣ ሰሞኑን ጅቡቲ ወደብ የደረሰ 7 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ወደ አገር ውስጥ እየተጓጓዘ መኾኑን መናገሩን መንግሥታዊ ዜና አውታሮች ዘግበዋል። ሰሞኑን ጅቡቲ የገባው የአፈር ማዳበሪያ፣ መንግሥት ዘንድሮው የምርት ዘመን ከውጭ ገበያ የገዛው 12 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ አካል እንደኾነ ዘገባዎቹ ጠቅሰዋል።

5፤ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 54 ብር ከ4852 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 55 ብር ከ5749 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ በድረገጹ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 66 ብር ከ6651 ሳንቲምና መሸጫው 67 ብር ከ9984 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ59 ከ6449 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ60 ብር ከ8378 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል።
መረጃ ህይወት ነው፣ ይህንንም መረጃ ለጓደኞቻችሁ#Share በማድረግ ተባበሩን


ወሳኝ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ቻናሉን ይቀላቀሉ


t.me/emsmereja
t.me/emsmereja
t.me/emsmereja