Get Mystery Box with random crypto!

የ“ኦነግ” ሸኔ ታጣቂዎች ከአዲስ አበባ 75 ኪሎ ሜትር እርቀት ላይ በምትገኝ ወረዳ አንድ ቀበሌ መ | Zemedkun Bekele (ዘመዴ)

የ“ኦነግ” ሸኔ ታጣቂዎች ከአዲስ አበባ 75 ኪሎ ሜትር እርቀት ላይ በምትገኝ ወረዳ አንድ ቀበሌ መቆጣጠራቸው ተገለጸ

ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራው እና በመንግሥት ኦነግ ሸኔ ተብሎ በአሸባሪነት የተፈረጀው ታጣቂ ቡድን አባላት በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ዋጫሌ ወረዳ፣ አርብ ሰኔ 9/2015 ተኩስ ከፍተው አንድ ቀበሌ መሉ በሙሉ መቆጣጠራቸውን አዲስ ማለዳ ከአካባቢው ነዋሪዎች ሰምታለች። 

በዚህም ታጣቂዎቹ በወረዳው ሥር ካሉ የገጠር ቀበሌዎች አንዷ የሆነችውን ጉምቢቹ ቀበሌ አርብ ዕለት ሙሉ ለሙሉ በቁጥጥራቸው ሥር ማድረጋቸውን የተገለጸ ሲሆን፤ የቀበሌው ነዋሪም በከፍተኛ ስጋት ውስጥ ናቸው ተብሏል።

በተጨማሪም በዕለቱ ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ገደማ ከአዲስ አበባ በስተሰሜን 75 ኪሎሜትር እርቀት ላይ ከምትገኘዋ የወረዳው ከተማ ሙከጡሪ በመግባት ኹለት ሰዎችን አፍነው ሲወስዱ አንድ ሰው ላይ ደግሞ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰው መሰወራቸው ተገልጿል።

በአካባቢውም ከሰላሳ ደቂቃ በላይ ከፍተኛ የተሰኩስ ድምጽ ይሰማ እንደነበር ነዋሪዎች ጨምረው ገልጸዋል።

የታጣቂ ቡድን አባላት በአካባቢው በተለይም ከአንድ ዓመት ወዲህ በስፋት እንደሚንቀሳቀሱና በፈለጉት ሰዓት በመምጣት ነዋሪዎችን አፍነው እንደሚወስዱ ነው የተገለጸው፡፡

ነዋሪዎቹን በተለያዩ ጊዜያት አፍነው ከወሰዱ በኋላም "ከ200 ሺሕ እስከ 1 ሚሊዮን ብር ክፈሉ" እያሉ እንደሚደራደሩ ነው የተገለጸው፡፡

ከአንድ ሳምንት በፊት የወረዳው የባህል እና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሌሊት ላይ በታጣቂዎች በመሳሪያ ተመትተው መገደላቸው የተጠቀሰ ሲሆን፤ የአካባቢው ነዋሪዎችም ከሚኖሩበት ቀዬ በየዕለቱ እንደሚፈናቀሉ ተመላክቷል።

በወረዳው የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በስፋት ያሉ ቢሆንም፤ ታጣቂ ቡድኑ በፈለገው ሰዓት እየገባ ሰላማዊ ሰዎችን አፍኖ እንደሚወስድም ነው የተገለጸው፡፡

አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ዙሪያ ከዋጫሌ ወረዳ ሰላም እና ጸጥታ ዘርፍ ጽህፈት ቤት ምላሽ ለማግኘት ተደጋጋሚ ሙከራ ብታደርግም ሳይሳካ ቀርቷል።
መረጃ ህይወት ነው፣ ይህንንም መረጃ ለጓደኞቻችሁ#Share በማድረግ ተባበሩን


ወሳኝ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ቻናሉን ይቀላቀሉ


t.me/emsmereja
t.me/emsmereja
t.me/emsmereja