Get Mystery Box with random crypto!

የሳምንቱ አንኳር ዜናዎች  እሁድ ሰኔ 11 ቀን 2015 (EMS Mereja) 1) በኦሮሚያ ክ | Zemedkun Bekele (ዘመዴ)

የሳምንቱ አንኳር ዜናዎች 

እሁድ ሰኔ 11 ቀን 2015 (EMS Mereja)

1) በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ባቱ (ዝዋይ) ከተማ እሁድ ሰኔ 4/2015 ዕለት ከሌሊቱ አምስት ሰዓት አካባቢ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ብሎ የሚጠራውና በመንግሥት ኦነግ ሸኔ ተብሎ በአሸባሪነት በተፈረጀው ታጣቂ ቡድን መካከል በተደረገ ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ የአራት ሰዎች ሕይወት ማለፉን የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡

ከሟቾቹ መካከል አንዲት ሴትን ጨምሮ ሦስቱ የመንግሥት የጸጥታ አካላት መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን፤ አንዱ ደግሞ ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን አባል ነው ተብሏል። ለተከታታይ ኹለት ሰዓታት በላይ ሲደረግ ነበር የተባለው የተኩስ ልውውጥ፤ ዓላማው እስረኛ ለማስፈታት እንደሆነ ተገልጿል።

እስር ቤቱ በተለምዶ ሀይቅ ዳር ወይም የቀድሞ ጤና ጣቢያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ እንደሚገኝ እና ታጣቂዎቹ ከዚህ ቀደምም በእስር ቤቱ የታሰረባቸውን አባል ለማስፈታት ጥረት ሲያደረጉ የሰዎች ሕይወት ማለፉን ነዋሪዎቹ አውስተዋል።

2) ከሶማሊያ ግጭት በመሸሽ ወደ ኢትዮጵያ ከገቡ ስደተኞች ውስጥ 70 በመቶ ገደማ የሚሆኑት መጠለያ ባለማግኘታቸው ሜዳ ላይ እንደሚያድሩ ተገልጿል። ይህ የሆነው በገንዘብ እጥረት መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ ለስደተኞች ያስፈልጋል ከተባለው 116 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ የተገኘው ኹለት በመቶ ብቻ መሆኑ ተጠቅሷል። ይህን ተከትሎም ለስደተኞች ከሚያስፈልገው መጠለያ 30 በመቶ ብቻ በመሟላቱ ሌሎቹ በአንድ ቦታ ተጨናንቀው በዛፎች ሥርና ሜዳ ላይ እንደሚኖሩ ተመላክቷል። ከሶማሊያ ወደ ኢትዮጵያ ከገቡ ከ100 ሺሕ በላይ ስደተኞች መካከል፤ 20 ሺሕ ያህሉ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ዶሎ ዞን ቦኦ ወረዳ ሚርቃን ቀበሌ በሚገኝ መጠለያ ጣቢያ እንዲገቡ መደረጋቸው ነው የተገለጸው። 

3) ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ባለፉት አስር ወራት 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ለአዲስ ማለዳ ገልጿል።

በዚህም ከሃምሌ 01/2014 እስከ መጋቢት 30/2015 ድረስ ከአገር ዉስጥ ቦንድና ስጦታ 897 ሚሊዮን በላይ መሰብሰብ መቻሉ የተገለጸ ሲሆን፤ ከዲያስፖራ ቦንድና ስጦታ ከ13 ሚሊዮን በላይ እንዲሁም ከአጭር የሞባይል መልእክት አገልግሎት ከ110 ሚሊዮን ብር በላይ እና በኢትዮጵያ ኤሌትሪክ ኃይል የስጦታ አካውንት ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ እንደተሰበሰብ ተጠቁሟል።

4) በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ኮንሶ ዞን የተከሰተው ድርቅ ባስከተለው ሰብዓዊ ቀውስ ምክንያት ከ190 ሺሕ በላይ ሰዎች አስቸኳይ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው የዞኑ አደጋ ስጋትና መከላከል መምሪያ ለአዲስ ማለዳ ገልጿል።

የኮንሶ ዞን አደጋ ስጋት እና መከላከል መምሪያ ኃላፊ ገደኖ ካዋይታ፤ በዞኑ አሁንም 190 ሺሕ 822 ሰዎች አስቸኳይ ድጋፍ የሚፈልጉ መሆናቸውን ነው የተናገሩት። ኃላፊው አክለውም፤ ለተከታታይ አራት የመኸር ዘመን ተቋራጦ የነበረው ዝናብ በዘንድሮ የበልግ ዘመን መዝነቡን ተከትሎ ቀድሞ ከተለያዩ አካላት ሲደረግ የነበረው ሰብዓዊ ድጋፍ መቀዛቀዙን ተናግረዋል፡፡

5) በበጀት መቋረጥ ምክንያት በጣና ሀይቅ ላይ የተከሰተውን የእንቦጭ አረም የማስወገዱ ሥራ ከአምስት ወራት በፊት መቆሙን የጣና ሐይቅና ሌሎች ዉሃ አካላት ጥበቃና ልማት ኤጀንሲ ለአዲስ ማለዳ ገለጸ።

በዚህም ከባለፈው የካቲት ወር ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ምንም አይነት የእንቦጭ አረም የማስወገድ ሥራ እየተሰራ አለመሆኑን የኤጀንሲው ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶክተር አያሌው ወንዴ ተናግረዋል። በዘንድሮው በጀት ዓመት ሙሉ ለሙሉ የእንቦጭ አረምን ለማስወገድ ታቅዶ እንደነበር የገለጹት ኃላፊው፤ አረሙን ለማስወገድ ለገቡት ማሽኖች የነዳጅ ወጪ እንዲሁም ለኤክስካቫተር ኪራይ ወጪ መሸፈን ባለመቻሉ ሥራው ተቋርጧል ነው ያሉት።

በሀይቁ ላይ የተከሰተውን ከአረም ለማጥፋት በጀት የሚመድበውም በዋናነት በአማራ ክልል እና በፌደራል መንግሥታት መሆኑን አመላክተዋል።

6) በሰሜን ኢትዮጵያ በፌደራል መንግሥት እና በሕወሓት መካከል በተካሄደው ጦርነት በኹለቱም ወገኖች የታሰሩት ተዋጊዎች የት እንዳሉ እስካሁን እንደማይታወቅ ተገለጸ።

ከተኩስ አቁም ስምምነት ጀምሮ እስካሁን ድረስ በጦርነቱ ወቅት ስለታሰሩት በሺዎች የሚቆጠሩ የጦርነት ተሳታፊዎች እና ስለተማረኩት ተዋጊዎች እጣ ፈንታ ከፌደራል መንግሥትና ከሕወሓት በኩል የተሰጠ ምላሽ አለመኖሩ ቅሬታን መፍጠሩ ተገልጿል፡፡ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የሕግ አማካሪ ፍስሃ ተክሌ፤ በእስር ላይ የሚገኙ የፌደራል መንግሥቱ እና የሕወሓት ወታደሮች እንዲሁም በየአካባቢው በጦርነቱ ተሳትፋችዋል ተብለው ያለክስ የታሰሩ የሚሊሻ አባላት የት እንዳሉ አይታወቅም ማለታቸውን አልጀዚራ ዘግቧል።

7) በኢትዮጵያ 4.8 ሚሊዮን ሕጻናት በተመጣጣኝ ምግብ እጥረት የተነሳ የመቀንጨር አደጋ አጋጥሟቸዋል ተባለ።

የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለስልጣን (ኢጋድ) የአየር ንብረት ትንበያ እና መተግበሪያ ማዕከል፤ የምግብ ቀውሶችን አስመልክቶ ያጠናው ጥናት "ዓለም አቀፍ ሪፖርት 2023" ይፋ ተደርጓል። ጥናቱ በኢጋድ አባል አገራት ላይ ያተኮረ ሲሆን፤ በዚህም በ2022 በኢትዮጵያ 4.8 ሚሊዮን ሕጻናት በተመጣጣኝ ምግብ እጥረት የተነሳ ቀንጭረው እንደነበር ተመላክቷል። ይህም ቁጥር ኢትዮጵያን በምስራቅ አፍሪካ በሕጻናት መቀንጨር ቀዳሚ አገር እንደሚያደርጋትም ተነግሯል።

8) ከትግራይ ክልል እንዳይወጡ የታገዱ ነዋሪዎች የትራንስፖርት አገልግሎት ለማግኘት ጉቦ እየከፈሉ መሆኑን ገለጹ፡፡  በትግራይ ክልል ከ15 እስከ 60 ዕድሜ ያላቸው ሰዎች ከክልሉ በአየርና የየብስ ትራንስፖርት ወደ አዲስ አበባ መሄድ እንዳይችሉ ክልከላ ከመደረጉ ጋር ተያይዞ፤ ለትራንስፖርት ሰጭ ተቋማት ሠራተኞች ጉቦ እየከፈሉ እንደሚወጡ ተናግረዋል።

ነዋሪዎቹ ከትግራይ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በዋናነት ወደ አዲስ አበባ ለመጓዝ የአውሮፕላንም ሆነ የመኪና ትኬት ለማግኘት፤ ለአየር መንገድ ሠራተኞች እና ጥበቃዎች እንዲሁም ለአውቶብስ ሠራተኞች ጎቦ በመክፈል ትኬት እንደሚያገኙ ነው ለአዲስ ማለዳ የገለጹት። ከጦርነቱ ማብቃት በኋላ የትግራይ ክልል ወጣቶች በአውሮፕላንም ይሁን በመኪና ከክልሉ እንዳይወጡ እየተደረገ ነውም ብለዋል።

9) በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን በተከሰተው ድርቅ ለተጎዱ ዜጎች ሲቀርብ የነበረው ሰብዓዊ ድጋፍ መሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ መቋረጡን የቦረና ዞን ቡሳ ጎኖፋ መምሪያ ለአዲስ ማለዳ ገልጿል። 

የመምሪያው ኃላፊ ሊበን ሳራ፤ የድርቁ አስከፊነት በተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች ከተሰማ በኋላ፣ ሲደረግ የነበረው ሰብዓዊ ድጋፍ መልካም እንደነበረ የገለጹ ሲሆን፤ ነገር ግን ለአምስት ተከታታይ የዝናብ ወቅቶች ተቋርጦ የነበረው ዝናብ፣ መዝነብ ከጀመረ በኋላ ሲደረግ የነበረው ድጋፍ መቋረጡን አስረድተዋል፡፡

አሁን ላይ መጠነኛ ድጋፍ እያደረገ ያለው “ጆፕ” የተሰኘ መንግሥታዊ ያልሆን ግብረ ሰናይ ድርጅት ብቻ መሆኑን ገልጸው፤ በሌሎች አካላት ሲደረግ የነበረው ሰብዓዊ ድጋፍ ግን ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ መቆሙን ተናግረዋል፡፡
መረጃ ህይወት ነው፣ ይህንንም መረጃ ለጓደኞቻችሁ#Share በማድረግ ተባበሩን


ወሳኝ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ቻናሉን ይቀላቀሉ
http://t.me/emsmereja