Get Mystery Box with random crypto!

ቅዳሜ ምሽት! ሰኔ 10/2015 ዓ.ም የEMS ዐበይት ዜናዎች 1፤ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳ | Zemedkun Bekele (ዘመዴ)

ቅዳሜ ምሽት! ሰኔ 10/2015 ዓ.ም የEMS ዐበይት ዜናዎች

1፤ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ለኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በጻፈው ደብዳቤ በጦርነቱ ለተጎዱ የክልሉ ኢንቨስትመንቶች የካሳ ክፍያ፣ የዕዳና የታክስ ስረዛ እንዲደረግላቸው መጠየቁን ሪፖርተር ዘግቧል። ኮሚሽኑ የጥያቄዎቹን አፈጻጸም የሚገመግም የጋራ ኮሚቴ እንዲቋቋም ጭምር ጠይቋል ተብሏል። ኮሚሽኑ የውጭ ኢንቨስትመንት ኩባንያዎች በክልሉ ሙዓለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ፌደራል መንግሥቱ እንዲጋብዝ መጠየቁንም ዜና ምንጩ አመልክቷል። የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው፣ የክልሉ ኢንቨስትመንት ኩባንያዎች ብድር እንዲሰረዝላቸው ወይም የዕዳ መክፈያ ጊዜ እንዲራዘምላቸው ብሄራዊ ባንክን መጠየቃቸውን በዘገባው ተመልክቷል።

2፤ ምርጫ ቦርድ በቀጣዩ ሰኞ በደቡብ ክልል ወላይታ ዞን በድጋሚ የክልልነት ሕዝበ ውሳኔ ያካሂዳል። በዞኑ የሚንቀሳቀሱት ተቃዋሚዎቹ የዎላይታ ብሄራዊ ንቅናቄ እና የዎላይታ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ግንባር ግን ቦርዱ ለሚያካሂደው የክልልነት ሕዝበ ውሳኔ እውቅና አንሰጥም ማለታቸውን ዶይቸቨለ ዘግቧል። ሁለቱ ፓርቲዎች ሕዝበ ውሳኔውን የተቃወሙት፣ ሕዝበ ውሳኔው የዎላይታን ሕዝብ ራሱን የቻለ ክልል የመመስረት መብት የነፈገና ሕገ መንግሥታዊ ጥሰት ያለበት ሂደት ነው በማለት እንደኾነ ዘገባው አመልክቷል። ሁለቱ ፓርቲዎች ፌደሬሽን ምክር ቤት የዞኑን ሕዝብ ሕጋመንግሥታዊ መብት ጥሷል በማለት ቀደም ሲል በፍርድ ቤት ክስ መስርተዋል። የሰኞው ሕዝበ ውሳኔ፣ ጥር ላይ ወላይታን ጨምሮ ስድስት ዞኖችና አምስት ልዩ ወረዳዎች ያካሄዱት ሕዝበ ውሳኔ አካል ነው። ቦርዱ በወቅቱ የወላይታ ዞን ሕዝበ ውሳኔ ላይ የሕግ ጥሰት አግኝቼበታለኹ በማለት በድጋሚ እንዲካሄድ መወሰኑ ይታወሳል።

3፤ የሱማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሞሐመድ የተመድ ጸጥታው ምክር ቤት በአገራቸው ላይ የጣለውን የጦር መሳሪያ ማዕቀብ ሙሉ በሙሉ እንዲያነሳ በአካል እንዲጠይቁ በተያዘው ወር የምክር ቤቱ ሰብሳቢ የኾነችው ወዳጃቸው የተባበሩት ዓረብ ኢምሬቶች ጋብዛቸዋለች። ፕሬዝዳንቱ የጦር መሳሪያ ማዕቀቡ እንዲነሳ ለጸጥታው ምክር ቤት በሚያደርጉት ንግግር የሚጠይቁት፣ ምክር ቤት በሱማሊያ ወቅታዊ ጸጥታ ላይ በተያዘው ወር በሚያዘጋጀው ልዩ ስብሰባ ላይ እንደኾነ የሱማሊያ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ጸጥታው ምክር ቤት በአገሪቱ ላይ የጦር መሳሪያ ማዕቀብ የጣለው ከ30 ዓመት በፊት ቢኾንም፣ በተለያዩ ጊዜያት ማዕቀቡን በከፊል አንስቷል።

4፤ የአሜሪካው ፔንታጎን ትናንት ሌሊት በአንድ የአልሸባብ አመራሮች ስብሰባ ላይ በፈጸመው የድሮን ጥቃት በርካቶች መገደላቸውን የሱማሊያ መንግሥታዊ ዜና አውታሮች ዘግበዋል። የድሮን ጥቃቱ የተፈጸመው፣ ከኪሲማዩ ወደብ ወጣ ብሎ በጁባላንድ ራስ ገዝ በታችኛው ጁባ ግዛት እንደኾነ ዘገባዎቹ ገልጠዋል። አልሸባብ የፔንታጎን የድሮን ጥቃት ዒላማ የኾነው፣ በአፍሪካ የአሜሪካ ወታደራዊ ዕዝ (አፍሪኮም) ዋና አዛዥ ከሞቃዲሾና ከጁባላንድ ራስ ገዝ ባለሥልጣናት ጋር በአካል ተወያይተው በተመለሱና የሱማሊያ ጦር ከኢትዮጵያ፣ ኬንያና ጅቡቲ ጦር ጋር ጁባላንድ በሚንቀሳቀሰው አልሸባብ ላይ የተቀናጀ ዘመቻ ለማድረግ በዝግጅት ላይ ባሉበት ወቅት ላይ ነው።

5፤ አንድ የሱዳን ጦር ሠራዊት ከፍተኛ አዛዥ የባርቱም ነዋሪዎች የፈጥኖ ደራሹ ኃይሎች ከመሸጉባቸው ሠፈሮች እንዲወጡ መጠየቃቸውን ሱዳን ትሪቡን ዘግቧል። የጦሩ ከፍተኛ አዛዥና የሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ኣባል የኾኑት ጀኔራሉ ይህን ትዕዛዝ ያስተላለፉት፣ ጦር ሠራዊቱ በየሠፈሩና መኖሪያ ቤቶች የመሸጉትን የፈጥኖ ደራሽ ሠራዊት ኃይሎች በምድር ውጊያ ሊገጥም በመኾኑ እንደኾነ መግለጣቸውን ዘገባው ጠቅሷል። ጦር ሠራዊቱ እስካሁን ካርቱም ላይ ሲዋጋ የቆየው፣ በዋናነት በአውሮፕላና ድብደባና በከባድ መሳሪያ ነው። ጀኔራሉ፣ ውጊያው በአኹኑ ወቅት ከወታደሮች አልፎ ሲቪሉን ሕዝብና የፖለቲካ ኃይሎችን ጭምር ያካተተ ኾኗል ማለታቸውን ዘገባው ጠቅሷል።

6፤ የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሴሪል ራማፎዛ የመሩት ለሩሲያና ዩክሬን ግጭት ሰላማዊ መፍትሄ አፈላላጊ የአፍሪካ መሪዎች ልዑካን ቡድን ዛሬ በሩሲያዋ ፒተርስበርግ ከተማ ገብቷል። ልዐካን ቡድኑ ወደ ሩሲያ ያቀናው፣ ከዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ዘለንስኪ ጋር ከተወያየ በኋላ ነው። የአፍሪካዊያኑ የመሪዎች ልዐካን ቡድን በሩሲያ ቆይታው፣ ግጭቱን በንግግር መፍታት በሚቻልበት ኹኔታ ዙሪያ ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ይወያያል። ልዑካን ቡድኑ፣ የሴኔጋል፣ የዲሞክራሲያዊት ኮንጎ፣ የኮሞሮስ፣ የዛምቢያና የግብጽ መሪዎችን ያካተተ ነው።
መረጃ ህይወት ነው፣ ይህንንም መረጃ ለጓደኞቻችሁ#Share በማድረግ ተባበሩን


ወሳኝ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ቻናሉን ይቀላቀሉ


t.me/emsmereja
t.me/emsmereja
t.me/emsmereja