Get Mystery Box with random crypto!

አንድ በጣም ትልቅ ቆሻሻ የጫነ ጋሪ የሚገፋ ሰው ወደ ቤትህ መጥቶ 'እባክህ በርህን ክፈትልኝና ይህ | ዘማሪ ዲ/ን ፍፁም ከበደ

አንድ በጣም ትልቅ ቆሻሻ የጫነ ጋሪ የሚገፋ ሰው ወደ ቤትህ መጥቶ "እባክህ በርህን ክፈትልኝና ይህን ቆሻሻ አንተ ቤት ላራግፈው?" ቢልህ፣ "ውይ የሚጥልበት ቢያጣ ነው። ባይቸገር ወደ እኔ አይመጣም ነበር" ብለህ ደጅህን ከፍተህ ታስገባዋለህ? በፍጹም፤ እንደውም "እንዴት ብታስበኝ ነው? ምነው ስታየው ቤት አልመሰለህም? እንዴት ሰው በሚኖርበት ቤት ቆሻሻ ካልደፋሁ ትላለህ? ስትል ለጠብ ትጋበዛለህ። መደፈርህ እያንገበገበህ "እምቢ!" ብለህ ትቆጣለህ። በእርግጥም ያስቆጣል።

ግን ሌላ የሚከፋ ሽታ ያለው ቆሻሻን ጭኖ ለመጣ ባላጋራ እኮ በፈቃድህ የከፈትከው ቤት አለ። የምን ቤት? ልብህ ነዋ፤ ማን ይኖርበታል አልኸኝ? እግዚአብሔር ነዋ። አንተ ለመኖሪያ ቤትህ ጽዳት የምትጠነቀቀውን ያህል የያዕቆብ አምላክ ለሚያርፍበት ኅሊናህ ተጠንቅቀህ ታውቃለህ? ሰይጣን ጭኖ የሚያመጣውን የኃጢአት ቆሻሻ ሁሉ እሺ ብለህ ወደ ልብህ በማስገባት የፈጣሪህን መቅደስ ለምን ታቆሽሻለህ? ንጹሑ እግዚአብሔር የሚያድርበትን ቤት ሊያቆሽሽ በመጣ ሰይጣን ላይ እንዴት አልተቆጣህም? ድፍረቱ ለምን አላብከነከነህም?

እግዚአብሔር አንተ ልትኖርበት ከምትፈልገው ንጹሕ ቤት የበለጠ ጽዱ መቅደስ የማይፈልግ ይመስልሃል?

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
አዲስ አበባ