Get Mystery Box with random crypto!

+++ ልሸፈንላችሁ? +++ ሙሴ ከሲና ተራራ ወርዶ ከሕዝቡ ጋር ሲገናኝ የፊቱን ማንጸባረቅ አይተ | ዘማሪ ዲ/ን ፍፁም ከበደ

+++ ልሸፈንላችሁ? +++

ሙሴ ከሲና ተራራ ወርዶ ከሕዝቡ ጋር ሲገናኝ የፊቱን ማንጸባረቅ አይተው "ተሸፈንልን" ያሉት ሕዝቡ ናቸው። እርሱ "ከእግዚአብሔር ጋር ስነጋገር ቆይቼ እኮ አሁን መውረዴ ነው? ምነው የፊቴ ብርሃን አስቸገራችሁ? ልሸፈንላችሁ እንዴ?" አላለም። እንዲያውም ቅዱስ መጽሐፍ "ሙሴም ከተራራው በወረደ ጊዜ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ስለ ተነጋገረ የፊቱ ቁርበት እንዳንጸባረቀ አላወቀም ነበር" ነው የሚለው።(ዘጸ 34፥29) ለቅዱሳን እግዚአብሔር በፊታቸው የሚሥለው የክብር ብርሃን እነርሱን ለሚመለከታቸው እንጂ ለራሳቸው አይታወቃቸውም። እውነተኞቹ ቅዱሳን  "ተሸፈኑልን" የሚባሉ እንጂ "ልሸፈንላችሁ" የሚሉ አይደሉም።

ጥቂት በጎ ሥራ ሠርተህ ጻድቅነትህን በግድ ለማሳየት አትሞክር። ሌሎች ተሸፈንልን ይበሉህ እንጂ፣ አንተ ራስህ "ልሸፈንላችሁ" እያልህ የዋሐንን አታስጨንቅ።

በአገራችን የሚታወቅ ተረት አለ። አንድ ጊዜ ትንኝ በሬ ቀንድ ላይ ቆመችና "ከብጄህ እንደ ሆነ ንገረኝና ልነሣልህ" አለችው። በሬውም "እንኳን ልትከብጅኝ መኖርሽንም አላወቅሁም" አላት።

"ጻድቃን እንደ ሆኑ በራሳቸው ለሚታመኑና ሌሎቹን ሁሉ በጣም ለሚንቁ ይህን ምሳሌ ነገራቸው"   ሉቃስ 18፥9

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
አዲስ አበባ

          ( ቃለ ሕይወት ያሰማልን:: የሚደንቅ ነው:: "ማብራቱ አይታወቀውም ነበር" የሚያሳዝነው እነሱ ቅድስናቸው እንደማይታወቃቸው እኛም ኃጢአታችን አይታወቀንም:: ልብስ ሲቆሽሽ አይታወቀውም አይደል?    "ዲያቆን ሔኖክ ኃይሌ" )