Get Mystery Box with random crypto!

+++ 'ጌታ ሆይ አሰናብትልን' +++ ጌታ ሠላሳ ዓመት በምድረ በዳ የኖረ የዮሐንስ መጥምቅን ሞ | ዘማሪ ዲ/ን ፍፁም ከበደ

+++ "ጌታ ሆይ አሰናብትልን" +++

ጌታ ሠላሳ ዓመት በምድረ በዳ የኖረ የዮሐንስ መጥምቅን ሞት በሰማ ጊዜ በታንኳ ወደ ምድረ በዳ ፈቀቅ ብሎ ሄደ። ብቸኛ ሆኖ ኖሮ የሞተውን ሰው ኃዘን ብቻውን ሆኖ ሊወጣ ወደ በረሃ ተሳፈረ። ነገር ግን የእርሱን መሄድ የሰሙት ሕዝቡ ብቻውን እንዲሆን አልተውትም። እርሱ በታንኳ ቢሄድ እነርሱ በእግር ተከትለውት መጡ። ጌታችንም ጠባቂ እንደ ሌለው መንጋ የሆኑትን ሕዝብ በፊቱ ባየ ጊዜ አዘነላቸው። እስኪመሽም ድረስ አስተማራቸው፤ ድውዮቻቸውንም ፈወሰ።

ታዲያ በዚህ መካከል የአገልግሎቱ አስተባባሪ የነበሩት ሐዋርያትን አንድ ነገር አሳሰባቸው፤ "ይህ ሁሉ ሕዝብ ምን ሊበላ ነው?" የሚለው የምግብ ጉዳይ። ይህን ጥያቄያቸውን ይዘው ወደ መድኃኒታችን መጡና "ቦታው ምድረ በዳ ነው አሁንም ሰዓቱ አልፎአል፤ ወደ መንደሮች ሄደው ለራሳቸው ምግብ እንዲገዙ ሕዝቡን አሰናብት" አሉት።(ማቴ 14፥15) ጌታችንም "አይይ ይህን የመሰለ ቃለ እግዚአብሔር ሲመገቡ አምሽተው እናንተ ስለ ምግብ ትጨነቃላችሁ? ባይበላስ?" ብሎ አላሳፈራቸውም። እርሱ የነፍስም የሥጋም ፈጣሪ ነው። በእለተ ማግሰኞ ለምግበ ሥጋ የሚሆኑ አዝርእትና ፍራፍሬን የፈጠረ አምላክ እንዴት የሰውን ረሃብ ቸል ይላል? ስለዚህም ለሐዋርያቱ "እናንተ የሚበሉትን ስጡአቸው እንጂ ሊሄዱ አያስፈልግም" አላቸው።(ማቴ 14፥16) ደቀ መዛሙርቱም ያለን ጥቂት ነው። ከሁለት ዓሣና ከአምስት እንጀራ በቀር ምንም የለንም አሉ።

ከሐዋርያቱ ጥያቄ እንደምንረዳው የምግብ ጭንቀታቸውን ያባባሰው አንደኛ ቦታው ምድረ በዳ መሆኑ፣ ሁለተኛ ደግሞ ሰዓቱ ማለፉ (መምሸቱ) ነው። ሙት ሲያስነሣ፣ ድውይ ሲፈውስ ያዩትን መምህራቸውን ምንም እንደ ቀደሙ አባቶቻቸው "እግዚአብሔር በምድረ በዳ ማዕድን ያሰናዳ ዘንድ ይችላልን?" ብለው ባያሙትም፣ በምድረ በዳ ሕዝቡን ይመግባል ብለው ግን አላመኑበትም ነበር።(መዝ 78፥19) አብሯቸው ያለው ጊዜ እና ቦታ የማይወስነው የብርሃኑን ጊዜ ቀን፣ የጨለማውን ጊዜ ደግሞ ማታ ብሎ ስም ያወጣላቸው በሰዓታት ላይ የሰለጠነ አምላክ መሆኑን አላስተዋሉም ነበር። 

ክርስቶስ ሐዋርያቱን "እናንተ የሚበሉትን ስጧቸው" ብሎ ሲያዝዝ ደቀ መዛሙርቱ ጥቂት ብቻ እንዳላቸው ሳያውቅ ቀርቶ አይደለም። ነገር ግን ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ እንደሚነግረን እምነታቸውን ሊፈትን ነበር። በእርግጥም ፈተናቸው እንደ ጠበቀውም ዓይነት እምነት አላገኘባቸውም። "ያለን ጥቂት ነው" አሉት። ሐዋርያቱ ምን ያህል ቢይዙ ነበር አምስት ሺህ ሰው (ሴቶችና ሕፃናት ሳይቆጠሩ) መመገብ የሚችሉት? መቼም ቢሆን ለአምስት ገበያ ሕዝብ የሚሆን ምግብ ተሸክመው አይዞሩም። ስለዚህ አሁን ካላቸው አምስት እንጀራ እና ሁለት ዓሣ የሚበልጥ ምግብ ቢኖራቸው እንኳን ሕዝቡን ለማጥገብ የእግዚአብሔር በረከት ግድ ያስፈልግ ነበር። እነርሱ ያሰቡት በእጃቸው ያለውን ጥቂት ነገር እንጂ አብሯቸው ያለውን በብዙም በጥቂትም መሥራት የሚችለውን አምላክ አልነበረም። እርሱን ማሰብ ቢያስቀድሙ ኖሮ በጥቂቱ ነገር  አይጨነቁም በብዙውም ነገር አይኮሩም ነበር።

እኛስ እጃችን ላይ ያለውን ጥቂት ነገር ብቻ አይተን "አሰናብትልን" ያልንበት ጊዜ የለም? የምእመናኑ ጥያቄ እና የእኛ ዝግጅት አልመጣጠን ሲለን ጥቂቱን ነገር ማብዛት ወደሚችል አምላክ ቀርቦ ከመጠየቅ ይልቅ ስንት ጊዜ "ጌታ ሆይ አሰናብትልን?" እያል ከነገሩ ለመሸሽ ሞከርን? በትዳር ጉዳይ ምክር ፈልጌ ነበር? "ጌታ ሆይ አሰናብትልን?"፣ ልጆቼን እንዴት ላሳድግ? -"ጌታ ሆይ አሰናብትልን?"፣ ኑሮዬን መምራት ቸግሮኛል -"ጌታ ሆይ አሰናብትልን?"፣ ከሱስ እንዴት ልላቀቅ -"ጌታ ሆይ አሰናብትልን?"...

እግዚአብሔር ከሰው ብዙ አይፈልግም። እጅህ ላይ ያለው ጥቂት ነገር ይበቃዋል። ለአምስት ሺህ ሕዝብ አምስት እንጀራን፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩትን ሕዝብ ባሕረ ኤርትራን ለማሻገር አንድ የሙሴን በትር፣ አንድ ሺ ፍልስጥኤማውያንን ለመግደል አንድ የአህያ መንጋጋ ተጠቅሞ ድንቅ ሥራውን አሳይቶናል። ጥቂቱን ነገር ሲጠይቅህ እርሱን ለማቅረብ ወደ ኋላ አትበል። እርሱ ማብዛት፣ ማበርከት፣ ለብዙ ሕዝብ፣ ለብዙ ጉባኤ ማድረግን ያውቅበታል።

በዲያቆን አቤል ካሳሁን


https://t.me/akanim1wasen2