Get Mystery Box with random crypto!

እንዴት እንጸልይ*?? የብዙዎች ጥያቄ መልስ ???? አንድ ሰው ለጸሎት ሲነሳ ዝም ብሎ እን | ዘማሪ ዲ/ን ፍፁም ከበደ

እንዴት እንጸልይ*??

የብዙዎች ጥያቄ መልስ ????

አንድ ሰው ለጸሎት ሲነሳ ዝም ብሎ እንደ ውሃ ደራሽ መሆን የለበትም፡፡ ለምን?እንዴት? መቼ? እጸልያለሁ የሚሉት ጥያቄዎች ሊመለሱ ይገባል። ስለ ጸሎት በምናስብበት ማናቸውም ጊዜ ልናስተወላቸው የሚያስፈልጉን ሁለት መሠረታዊ ነጥቦች አሉ፡- በእምነት መጸለይና በጥልቀት/በማስተዋል መጸለይ፡፡
እስኪ ሰፋ አድርገን እንመልከታቸው።

1. በእምነት መጸለይ
እግዚአብሔር አምላካችን ስለሚያስብልንና ስለሚወደን ልመናችንን እንደሚሰማንና የሚረባንን ነገር እንደሚያደርግልን፣ የተሻለውንም ነገር እንደሚሰጠን ልናምን ያስፈልገናል፡፡ ‘‘አምናችኹም በጸሎት የምትለምኑትን ዅሉ ትቀበላላችኹ፡፡’’ ማቴ 21፣22 ተብለናልና አምላካችን እግዚአብሔር የሚያስፈልገንን ሁሉ ሳንለምነው እንደሚሰጠንም እናምናለን፡፡ ‘‘ሳትለምኑት አባታችሁ የሚያስፈልጋችሁን ያውቃልና’’ ተብሎ እንደተጻፈ እግዚአብሔር አምላካችን እንኳን በለመንነው ነገር ይቅርና ባለመንነው በጎ ነገርም ላይ እርሱ ጻድቅና የታመነ ነው፡፡ (ማቴ 6፣8)፡፡ እስከ ሞት የወደደን እርሱ ደግሞ ሊሰጠን የማይወደውና የሚከለክለን ነገር እንደሌለ እናምናለን፡፡‘‘ለገዛ ልጁ ያልራራለት ነገር ግን ስለ ሁላችን አሳልፎ የሰጠው ያው ከእርሱ ጋር ደግሞ ሁሉን ነገር እንዲያው እንዴት አይሰጠንም?’’ ሮሜ 8፣32፡፡

በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ሞት የወደደንና የታረቀን አባታችን እግዚአብሔር የበጎ ነገር ሁሉ ምንጭ፣ የመልካምነት ሁሉ መዝገብ፣ የቸርነት ሁሉ መገኛ ነውና የምንለምነውን ሁሉ ከእርሱ እንደምንቀበል አውቀን እንጸልያለን፡፡‘‘ለምኑ፥ ይሰጣችኹማል፤ ፈልጉ፥ ታገኙማላችኹ፤ መዝጊያን አንኳኩ፥ ይከፈትላችኹማል። የሚለምነው ዅሉ ይቀበላልና፥ የሚፈልገውም ያገኛል፥ መዝጊያንም ለሚያንኳኳ ይከፈትለታል። ወይስ ከእናንተ፥ ልጁ እንጀራ ቢለምነው፥ ድንጋይን የሚሰጠው ከእናንተ ማን ሰው ነው? ዓሣስ ቢለምነው እባብን ይሰጠዋልን? እንኪያስ እናንተ ክፉዎች ስትኾኑ ለልጆቻችኹ መልካም ስጦታ መስጠትን ካወቃችኹ፥ በሰማያት ያለው አባታችኹ ለሚለምኑት እንዴት አብልጦ መልካም ነገርን ይሰጣቸው?’’ (ማቴ 7፣7-11)፡፡


እግዚአብሔር አምላካችን ለፍጥረቱ ሁሉ መጋቢ፣ የሚያዝንና የሚራራ ስለሆነ የምንለምነውን ሁሉ እንደሚሰጠንና እንደሚያደርግልን አምነን እንጸልያለን፤ ይህ እምነት እንኳን ባይኖረን ‘‘አለማመኔን እርዳው’’ ብለን ልንጸልይ ያስፈልገናል፡፡ እግዚአብሔር አምላካችንም የእምነት ሰዎች ሊያደርገንና በፊቱ የእምነት ሰዎች ሆነን እናድግ ዘንድ ሊያግዘን ይቻለዋል፡፡(ማር 9፣24)፡፡

ሐዋርያትም በአንድ ወቅት መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ‘‘እምነት ጨምርልን’’ ብለውት ነበር፡፡ ሉቃ 17፣5፡፡ እርሱም በለመኑት ነገር ሁሉ ላይ የታመነ ነውና ሐዋርያቱን በእምነት አሳድጓቸዋል፣ አጠንክሯቸዋልም፡፡ እምነት በጸሎት ሕይወታችን ውስጥ ከእግዚአብሔር ኃይልን የምንቀበልበት ታላቅ መንፈሳዊነት ነው፡፡ የቱንም ያህል እግዚአብሔር እንደረሳን ቢሰማንና የዘገየ ቢመስለንም እርሱ ሁሉን የሚያደርግበት የራሱ ጊዜ አለውና በእምነት ጸንተን እንጸልያለን፣ በእምነታችንም ወስጥ ደግሞ የእርሱን ጊዜ በትዕግስት እንጠብቃለን፡፡ ጻድቅ ኢዮብ እንዴት እንደተፈተነ እናውቃለን፤ ሆኖም ግን እግዚአብሔርን ባለማመን፣ ተስፋ በመቁረጥና የእግዚአብሔርን ጊዜ ባለመጠበቅ አልደከመም፡፡ በብዙ መከራው ውስጥ እግዚአብሔርን በመጠበቁ ከፊተኛው ይልቅ የኋለኛውን እግዚአብሔር ለኢዮብ ሊባርክለት ወዷል፡፡

2. በጥልቀትና በማስተዋል እንጸልይ፡፡

ለጸሎት በእግዚአብሔር ፊት በምንቆምበት ጊዜ ሁሉ ከውስጣችን የምናወጣው ማናቸውም ቃልና የምናደርገው ማንኛውም ዓይነት እንቅስቃሴ በማወቅና በማስተዋል መሆን አለበት፡፡ ከልብ ፈንቅሎ የሚወጣ፣ ከመንፈሳዊነት ጥግ የሚመነጭ ጥልቅ ስሜት ያልተለየው፣ እውነተኛ መንፈሳዊ መሻትን የሚገልጽ እውነት እንዲኖረን ያስፈልጋል፡፡ ይህም ሲባል ጸሎታችን ኃጢአታችንን በመናዘዝና ጥፋታችንን በማመን የተደረገ (መዝ 50/ ምሳ 28፣13)፣ እግዚአብሔርን ተስፋ በማድረግና በመጠበቅ ውስጥ የሆነ (አንተ የመድኃኒቴ አምላክ ነህና በእውነትህ ምራኝ፥ አስተምረኝም ቀኑን ሁሉ አንተን ተስፋ አድርጌአለሁ መዝ 25፣5/ ሮሜ 8፣24-25)፣ በፍቅር የምንፈጽመው (1ኛ ቆሮ 13) ሊሆን ይገባል፡፡ ያለፍቅር የሚሆን ማናቸውም በጎ ነገር ሁሉ ከንቱ መሆኑ ተጽፏል፡፡ 1ኛ ዮሐ 3፣10 ላይም ወንድሙን የማይወድ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም ተብሎ ተጽፏልና ጸሎታችን ጠላቶቻችንን በመውደድ፣ ለሌሎች በማዘንና በመራራት ውስጥ ሆነን የምንጸልየው ሊሆን ይገባል። በመጽናት (ኤፌ 6፣18 በጸሎትና በልመናም ሁሉ ዘወትር በመንፈስ ጸልዩ፤ በዚህም አሳብ ስለ ቅዱሳን ሁሉ እየለመናችሁ በመጽናት ሁሉ ትጉ) እንደተባለ እግዚአብሔርን በመጽናት የምንጠብቅበትና የምንታገስበትም እንዲሆን ያስፈልገናል፡፡



ዲያቆን ወሰን የለው በሐሩ

https://t.me/ZDfitsumkebede
https://t.me/ZDfitsumkebede