Get Mystery Box with random crypto!

የሚፀልይ ሰው ትዕቢተኛ አይደለም!! ሁላችንም እንደምንረዳው ፀሎት ከእግዚአብሔር ጋር የምንነጋገ | Zaphnath-paaneah

የሚፀልይ ሰው ትዕቢተኛ አይደለም!!

ሁላችንም እንደምንረዳው ፀሎት ከእግዚአብሔር ጋር የምንነጋገርበትና ሸክማችንን በፊቱ አራግፈን አዲስ ሰው ሆነን የምንነሣበት አስደናቂ የመሰዊያ ስፍራችን ነው....ስለዚህ ድንቅ እውነት እግዚአብሔር ይባረክ!!

ሆኖም ግን ፀሎት ልመናችንን በእግዚአብሔር ፊት የምናቀርብበት መንገድ ብቻ አይደለም ይልቁንም እጅግ ብዙ ምስጢሮች አሉት....በነገራችን ላይ የፀሎት ምስጢሮች በግልፅ የሚገቡን በዋነኝነት ስንፀልይ ነው፤ ልክ መኪናን እስካልነዳን ድረስ ክፍል ውስጥ ቁጭ ብለን ብቻ በቃረምነው እውቀት መንዳት እንደማንችለው ማለት ነው!!

ፀሎት ራሣችንን ሁሉን ቻይ በሆነው አምላክ ፊት ህያው መስዋዕት አድርገን የምናቀርብበትና ራሳችንን በማዋርድና ለስሙ በመገዛት ትህትናን የምንማርበት መሰዊያ ነው፤ ነገር ግን ያልተቋረጠ የፀሎት ህይወት መሆኑን እዚህ ጋር ልብ ይሏል!!

“እንግዲህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ሰውነታችሁን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝና ሕያው ቅዱስም መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እለምናችኋለሁ፥ እርሱም ለአእምሮ የሚመች አገልግሎታችሁ ነው።”ሮሜ 12፥1

ሁልግዜ በእግዚአብሔር ፊት በፀሎት የመንበርከክ ልምድ ያለው ሰው አወቀም አላወቀም፣ ተረዳም አልተረዳም ባህሪው እንኳን ሳይቀር እየተቀረፀ ወደ ክርስቶስ ፍፁም ሙላት እያደገ መሄዱ እሙን ነው!!

ዕብራውያን 5
⁷ እርሱም በስጋው ወራት ከሞት ሊያድነው ወደሚችል ከብርቱ ጩኸትና ከእንባ ጋር ጸሎትንና ምልጃን አቀረበ፥ እግዚአብሔርንም ስለ መፍራቱ ተሰማለት፤
⁸ ምንም ልጅ ቢሆን፥ ከተቀበለው መከራ መታዘዝን ተማረ፤

በእግዚአብሔር ፊት በፀሎት መቆየት የለመደ ሰው ትህትና፣ ቅንነት፣ ታዛዥነትና መገዛትን ስለሚለማመድ ራሱን ለማዋረድ አይቸገርም፤ Already መንበርከክ ተምሯልና......በፀሎት ያልተገራ ልብና መንበርከክ ያልለመደ ጉልበት ያለው ሰው ግን ሁልግዜ በሰዎች ፊትም በትህትናና በቅንነት መመላለስ ትልቅ መከራ ይሆንበታል!!

ለዚህም ነው እውነትኛ የፀሎት ሰዎች ትሁታን የሆኑት....በምድር ላይ እንደ እርሱ ያለ ትሁት የለም የተባለለት ሙሴ እንኳን የፀሎት ህይወቱን ማየት ይቻላል....ስለዚህ በፀሎት በጌታ ፊት በመቆየት ያልተሠሩ ማንነቶቻችን እንዲሰሩ መፍቀድ አለብን....መንፈሳዊነት እንደ ሎሊፓፕ ጭንቅላታችንን ብቻ የምናሳድግበት ዝንባሌ ሳይሆን ከጌታ ጋር በመነካካት ጠረናችን በእርሱ አስደናቂ መዓዛ እስኪቀየር ድረስ ህልውናው ውስጥ ተውጥን የምንጠፋበት የህይወት ሥርዓት ነው!!

አቤት ግን በፀሎት ውስጥ የታጨቁት አስገራሚ ህይወት ለዋጭ ሚስጥሮች ብዛታቸው!!!!

@ZaphnathPaaneah1
@Yoni4Christ
https://t.me/+I4DSx0eJ2iI2MDg0