Get Mystery Box with random crypto!

በጥንቱ ዘመን ሰማዕትነት ከዓላውያን ነገሥታት ጋር ነበር። ዓላውያን ነገሥታት ክርስቲያኖችን ያሳድዷ | ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ

በጥንቱ ዘመን ሰማዕትነት ከዓላውያን ነገሥታት ጋር ነበር። ዓላውያን ነገሥታት ክርስቲያኖችን ያሳድዷቸዋል። ክርስቲያኖቹም ጨርቄን ማቄን ሳይሉ ይሰደዳሉ። ስለ ሀብት ንብረታቸው፣ ስለ ምድራዊ ክብራቸው፣ ስለ ሚስቶቻቸው፣ ስለ ልጆቻቸው፣ ስለ ምድራዊት ኑሯቸው አይጨነቁም። ዋናው ጭንቀታቸው ነፍሳቸው ከአምላኳ፣ ከወዳጇ፣ ከሞተላት አፍቃሪዋ ርቃ እንዳትሰደድ ነበር። ታዲያ ለዚህ ብለው የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ግማሾቻቸው ዱር ለዱር፣ ግማሾቻቸው ተራራ ለተራራ፣ ግማሾቻቸው ዋሻ ለዋሻ ፣ ግማሾቻቸው ፍርክታ ለፍርክታ ተቅበዘበዙ። ብዙ የብዙም ብዙ መከራ ተቀበሉ። ነፍሳቸውን ለማትረፍ ብለው ራሳቸውን በየመቃብሩ፣ በየበረሃው ይደብቁ ነበር። በጣም የሚያስደንቀኝ ግን ይህን ያደረጉ በጣም ብዙ እናቶች መኖራቸው ነው።

ልጆቼ! የእኛ ሰማዕትነት ግን እንዲህ አይደለም። የእኛ ሰማዕትነትና ውጊያ በላያችን ላይ ካሉ ነገሥታት ጋር ነው። የእኛ ሰማዕትነት ከምኞቶቻችን ጋር ነው። የእኛ ሰማዕትነት ከስግብግብነት፣ ከእንቅልፍ፣ ከዋዛ ፈዛዛ፣ ከስንፍና፣ ከውሸት፣ ከሐሜት ጋር ነው። የእኛ ሰማዕትነት በጠዋት ተነሥቶ ኳስ ለመጫወት ሳይኾን ለጸሎት፣ ለስግደት ወደ ቤተክርስቲያን መሄድ ነው። የእኛ ሰማዕትነት ወንበራችን እስኪጎደጉድ ድረስ ፊልም ማየት ሳይኾን ቃለ እግዚአብሔር ማንበብ፣ መመልከት ነው።

ስለዚህ ልጆቼ! ከምኞታችን ጋር ተጋድሎ እንግጠም። ነፍሳችንን ከአምላኳ ጋር ከሚያጣሉ ደግሞም ለጊዜው ሳይኾን ለዘለዓለም ከሚለይዋት ፍላጎቶቻችን ጋር እንጋደል። ስለ ምድራዊ ሀብት፣ ስለ ምድራዊ ዝና፣ ስለ ጊዜአዊ ደስታ ብለን ነፍሳችንን ለዓላውያን ነገሥታት (ለምኞቶቻችን) ትንበረከክ ዘንድ አሳልፈን አንስጣት። ነፍሳችንን ከእነዚህ ነገሥታት መከራ እናድናት። እነዚህን ነገሥታት ድል አድርገን ከአምላኳ ጋር እናገናኛት። ከእንቅልፍ ጋር ተዋግተን ድልም አድርገን ጧት ለስግደት፣ ለጸሎት እናበርታት። የእኛ ዘመን ሰማዕትነት ይኼ ነው።

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
ምንጭ፦ "ሰማዕትነት አያምልጣችሁ"
ትርጉም፦ ገብረ እግዚአብሔር ኪደ