Get Mystery Box with random crypto!

+++ ዛሬም በፊታችን የቆመ የወርቅ ምስል አለ +++ እውነተኛ ክብርን ማግኘት ትፈልጋለህን? ክብ | ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ

+++ ዛሬም በፊታችን የቆመ የወርቅ ምስል አለ +++

እውነተኛ ክብርን ማግኘት ትፈልጋለህን? ክብርን ናቅ፤ ያን ጊዜም ትከብራለህ፡፡ ለምን እንደ ናቡከደነፆር ታስባለህ? እርሱ ክብርን መጨመር በፈለገ ጊዜ ከዕንጨትና ከድንጋይ የራሱን ምስል ሐውልት አቁሞአልና፤ ሕይወት በሌለው በዚህ ግዑዝ ነገር ሕይወት ላለው ለእርሱ ክብር የሚጨምርለት መስሎት ነበርና፡፡ [ነገር ግን ክብር ሳይኾን ውርደት አገኘው፡፡] እንግዲህ የስንፍናውን መጠን አለፍነት ታያለህን? እከብርበታለሁ ብሎ ባቆመው ነገር እንዴት የገዛ ራሱን እንደ ዘለፈበት ትመለከታለህን? በራሱና በገዛ ነፍሱ ንጽህና ሳይኾን ሕይወት በሌለው ነገር ላይ መደገፉ፣ በዚያ ረዳትነትም ክብርን ማግኘት ፈልጎ ሐውልቱን ማቆሙ፥ ከዚህ በላይ ምን ሞኝነት አለ? ራሱን ለማክበር ብሎ የገዛ ሕይወቱን እንደ ማስተካከል፥ በዕንጨት ላይ ዕንጨት እንደ መጨመር ያለ ምን ሞኝነት አለ? ይህ ማለት “አንድ ሰው ፈሊጥ ያውቃል የሚባለው ሰው በመኾኑ ሳይኾን የቤቱ ምንጣፍ ያማረ ስለ ኾነ፣ የቤቱ ደረጃም የተወደደ ስለ ኾነ ነው” እንደ ማለት ይቈጠራል፡፡ በእኛ ዘንድ በእኛ ዘመን ናቡከደነፆርን የሚመስሉ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ እርሱ ሐውልት እንዳቆመ አንዳንዶችም ስለ ለበሱት ልብስ፣ ስለ ገነቡት ቤት፣ ስላላቸው ፈረስ፣ ገንዘብ ስላደረጉት ሠረገላ፣ ወይም ስለ ቤታቸው አሠራር ክብር የሚያገኙ ይመስላቸዋል፡፡ ከሰውነት አፍአ ወጥተው ይህን በመሰለ መጠን አለፍ ዕብደት ይያዛሉ፡፡ የራሳቸውን ሕይወት እንደ ማስተካከል ቁሳዊ ነገርን በመሰብሰብ ክብርን ይፈልጋሉ፡፡

ቅዱሳንና የእግዚአብሔር አገልጋዮች የኾኑት [ሠለስቱ ደቂቅ] ግን ክብርን ያገኙት እነርሱ ራሳቸው ኖረው ባሳዩት ሕይወት ነው እንጂ [ናቡከደነፆር ክብር አገኝባቸዋለሁ ባላቸው] በእነዚህ ነገሮች አይደለም፡፡ ለራሳቸው ብቻ ሳይኾን ለሌሎችም ብርሃን ኾነው እውነተኛ ክብርን ያገኙት በዚህ መንገድ ነበር፡፡ ምርኮኞች፣ ባሪያዎች፣ ወጣቶች፣ ከሀገራቸው ርቀው የሚኖሩ ለሀገሩ ባዕዳንና ሀብታቸውን ኹሉ የተቀሙ የነበሩ ቢኾኑም ከማረካቸው፣ ከጌታቸው፣ በሀገሩም ይኖር ከነበረው ከናቡከደነፆር ይልቅ ንዑዳን ክቡራን የኾኑት እነርሱ ነበሩና፡፡ ናቡከደነፆር ከሐውልቱም፣ ከንግሥናውም፣ ከአለቆች ብዛትም፣ ከሠራዊቱ ብዛትም፣ ከወርቁ ብዛትም፣ ወይም ከሌላው ነገር ጓጉቶለት የነበረውን ክብር ማግኘትም ኾነ ከእነዚህ የተነሣ ታላቅ መኾን አልተቻለውም፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ እነዚህ ኹሉ ያልነበሩአቸው ሦስቱ ወጣቶች ራሳቸውን በመግዛታቸው ብቻ ይህን ኹሉ ክብር አገኙ፡፡ በራሱ ላይ የደፋው ዘውድ፣ የተጎናጸፈውም ሐምራዊ መጎናጸፍያ፥ ይህን የመሰለ ምንም ከሌላቸው ይልቅ እርሱ ራሱ እጅግ ሕሱር እንደ ኾነ ለናቡከደነፆር አሳዩት፡፡ ፀሐይ ከዕንቊ ይልቅ ደምቃ አሸብርቃ እንደምትታይ፥ እነርሱም ንጉሡ ካገኘው ክብር ይልቅ እነርሱ ያገኙት ክብር እጅግ እንዲሻል አስረዱት፡፡

“እንዴት አሳዩት?” ብለህ የጠየቅኸኝ እንደ ኾነም እንዲህ ብዬ እመልስልሃለሁ፡- አስቀድሜ እንደ ተናገርሁት እነዚህ ወጣቶች፣ ምርኮኞችና ባሪያዎች ዓለም ኹሉ ተሰብስቦ የንጉሡን በዓል ወደሚያደርግበት ሥፍራ ተከስሰው ተወሰዱ፡፡ ያን ጊዜ ንጉሡ እጅግ ተቈጣ፤ የፊቱም መልክ ተለወጠ፡፡ መኳንንትና ሹማምንት፣ የዲያብሎስ ትርኢትም ኹሉ በዙሪያቸው ቆሙ፡፡ መለከትና እምቢልታ በኹሉም አቅጣጫ ተነፋ፤ የዘፈኑ ድምፅም እስከ ሰማያት ድረስ ተሰማ፡፡ የእቶኑ እሳት ያለ ልክ ወደ ላይ ተንበለበለ፤ እስከ ደመናትም ደረሰ፡፡ ያን ጊዜ ኹሉም ፈራ፤ ተንቀጠቀጠም፡፡ ሦስቱ ወጣቶች ግን ምንም ምን ፍርሐት አይታይባቸውም ነበር፤ እነዚያ እነርሱን እንደ ናቁአቸው እነዚህም እሳቱን ንቀዉታልና፡፡ እሳቱን መናቅ ብቻም አይደለም፤ ጥብዓትንም አሳዩ እንጂ፡፡ ቅድም ሲነፉአቸው ከነበሩት መለከቶችና እንቢልቶች በላይ ጽሩይ ኾኖ የሚሰማ ድምፅም አሰሙ፡፡ “ንጉሥ ሆይ! ይህን ዕወቅ” አሉ (ዳን.3፡18)፡፡ እንዲህ ማለታቸው ንጉሡን መስደብ ሽተው አልነበረም፡፡ ሌላ ቃልም ሊናገሩት ፈልገው አልነበረም፤ ሃይማኖታቸውን ብቻ ሊያሳውቁት ነው እንጂ፡፡ ስለዚህም ምክንያት ንግግራቸውን አላስረዘሙም፤ በአጭር አነጋገር፡- “የምናመልከው አምላካችን ከሚነድደው ከእሳቱ እቶን ያድነን ዘንድ ይችላል” አሉት እንጂ (ዳን.3፡17)፡፡ “ይህን ኹሉ ሰው ሰብስበህ የምታሳየን ለምንድን ነው? የእቶኑን እሳት የምታቀጣጥለውስ ለምንድን ነው? እኮ፥ ሰይፍህን የምትስለው ለምንድን ነው? ከሠራዊትህ ውስጥ ኃያላኑን መርጠህ የምታዘውስ ለምንድን ነው? ይህን ዕወቅ፡- አምላካችን እግዚአብሔር ከእነዚህ ኹሉ በላይና ኃይለኛ ነው፡፡”

እግዚአብሔር በእሳቱ እቶን ተቃጥለው እንዲሞቱ ሊፈቅድ እንደሚችል ባሰቡ ጊዜም፥ የተናገሩት ነገር ሐሰት እንደ ኾነ አስቦ ንጉሡ እንዳይሳለቅባቸው ጨምረው፡- “ንጉሥ ሆይ ! እርሱ ባያድነን እንኳን አማልክትህን እንዳናመልክ ላቆምኸውም ምስል እንዳንሰግድለት ዕወቅ” አሉት (ዳን.3፡18)፡፡ “ባያድነን እንኳን ከእኛ ኃጢአት የተነሣ ነው” ብለዉት ቢኾን ኖሮ ንጉሡ ባላመናቸው ነበር፡፡ በእሳቱ እቶን ውስጥ ኾነው ግን “ባመጣህብን መከራ ኹሉ አንተ ጻድቅ ነህ፤ በእውነተኛ ፍርድህ ስለ ኃጢአታችን ይህን ኹሉ መከራ አምጥተህብናልና” እያሉ ስለ ኃጢአታቸው ወደ እግዚአብሔር ደጋግመው ይጸልዩ ነበር (መዝ.ሠለ.ደቂ. ቊ.4)፡፡ በንጉሡ ፊት ግን ስለ ኃጢአታቸው ከመናገር ዝም አሉ፡፡ ዝም ማለታቸው ብቻም ሳይኾን ቢሞቱም እንኳን ሃይማኖታቸውንም እንደማይለውጡ ቁርጥ ውሳኔያቸውን ነገሩት፡፡
ያደረጉትን ኹሉ ሲያደርጉም “ከእሳቱ እቶን ያድነናል፤ ከፍልሰታችን ወደ ሀገራችን ይመልሰናል፤ ከባርነታችን አርነት ያወጣናል፤ የቀደመ ባለጠግነታችንም ይሰጠናል” ብለው ሳይኾን እንዲሁ ለአምላካቸው ካላቸው ፍቅር የተነሣ ብቻ ነበርና፡፡ አዎን ! ሀገራቸውን፣ ነጻነታቸውንና ሀብታቸውን አጥተዋል፡፡ በቤተ መንግሥት ስለ ነበራቸው ክብር አትንገረኝ፡፡ ቅዱሳንና ጻድቃን ስለ ነበሩ በባዕድ ሀገር እልፍ ጊዜ ይህ ኹሉ ከሚኖራቸው ይልቅ በሀገራቸው ኾነው ነዳያን መኾንንና የቤተ መቅደሱን በረከት መቀበልን ይመርጣሉና ምንም አልነበራቸውም፡፡ “ከአእላፍ ይልቅ በአደባባዮችህ አንዲት ቀን ትሻላለች፤ በኃጥኣን ድንኳኖች ከመቀመጥ ይልቅ፥ በእግዚአብሔር ቤት እጣል ዘንድ መረጥሁ” ይላልና (መዝ. 83፡10)፡፡ ስለዚህ በባቢሎን ነገሥታት ከሚኾኑ ይልቅ በሀገራቸው የተጣሉ የተናቁ ሰዎች ይኾኑ ዘንድ እልፍ ጊዜ እንደሚመርጡ በዚህ የታወቀ የተረዳ ነው፡፡ “ስለ ኃጢአታችን በሀገሩ ኹሉ ዛሬ የጐሰቆልን ኾን” በማለታቸውም ይታወቃል (መዝ.ሠለ.ደቂ. ቊ.13)፡፡ እነርሱ ራሳቸው ታላቅ የኾነ ክብርን አግኝተው የነበሩ ቢኾኑም እንኳን፥ የሌላውን ሰው መከራ እያዩ ግን እጅግ ያዝኑ ነበርና፡፡ የቅዱሳን ሰዎች ልዩ ጠባያቸው እንደዚህ ነውና፡- ከወንድማቸው ደኅንነት በላይ ለእነርሱ ክብርም ቢኾን፣ ሹመትም ቢኾን፣ ወይም ይህን የመሰለ ሌላም ቢኾን ኢምንት ነውና፡፡ ለምሳሌ በእሳቱ እቶን ውስጥ ኾነው እንኳን ለወገናቸው እንደ ምን ያለ ምልጃ ያቀርቡ እንደ ነበሩ ተመልከት፡፡ እኛ ግን በደኅናውም ጊዜ እንኳን ስለ ወንድማችን አናስብም፡፡ የከለዳውያን ጠንቋዮች ንጉሡ ስላለመው ሕልም ጠይቆአቸው መመለስ ባለመቻላቸው ሊገድላቸው ትእዛዝ አውጥቶ ነበር፡፡ እነዚህ ወጣቶች ግን “የባልንጀራቸውን እንጂ የራሳቸውን ጥቅም ሳይመለከቱ” የባቢሎን ጠቢባን እንዳይሞቱ በማሰብ ስለ ሕልሙ ይነግራቸው ዘንድ ከሰማይ አምላክ ምሕረት ይለምኑ ነበር (ዳን.2፡17-18፣