Get Mystery Box with random crypto!

'ለወፎች ክንፍ የተሰጣቸው' ለወፎች ክንፍ የተሰጣቸው በወጥመድ እንዳይያዙ ነው። ሰዎችም የ | ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ

"ለወፎች ክንፍ የተሰጣቸው"

ለወፎች ክንፍ የተሰጣቸው በወጥመድ እንዳይያዙ ነው። ሰዎችም የማሰቡ ኃይልን የተሰጣቸው ኃጢአትን እንዲያስወግዱ ነው። እንግዲህ እንዲህ የማሰብ ኃይል ተሰጥቶን ሳለ ይባስ ብለን ከምድር አራዊት በታች የማናስተውል ከኾንን ሊደረግልን የሚችል ምህረት ወይም ይቅርታ እንደምን ያለ ምሕረት እንደምንስ ያለ ይቅርታ ነው?

በወጥመድ ተይዛ የነበረች ወፍ ድንገት ከወጥመዱ ብታመልጥ፤ ወደ ወጥመድ ገብቶ የነበረ አጋዘን ወጥመዱን በጣጥሶ ቢሄድ ከእንግዲህ ወዲህ በተመሳሳይ ወጥመድ እነዚህን መያዝ ከባድ ነው። የሕይወት ተሞክሮ ለሁለቱም ጥንቃቄን አስተምሯቸዋልና። እኛ ግን ምንም እንኳ በተመሳሳይ ወጥመድ ብንያዝም ተመልሰን ወደዚያ ወጥመድ እንወድቃለን፣ ምንም እንኳን በለባዊነት የከበርን ብንኾንም አእምሮ እንደሌላቸው እንሰሳት እንኳን ቀድመን አናስብም፤ አንጠነቀቅም!

ሴትን በማየት እልፍ ጉዳቶችን ተቀብለን ወደ ቤታችን የተመለስነው፤ በዝሙት ተመኝተንም ስናበቃ ለአያሌ ቀናት ያዘንነው ስንቴ ነው? ነገር ግን ከዚያ በኋላም ቢሆን በዚሁ ጉዳይ ላይ ጠንቃቆች አልኾንም፤ አንዱን ቁስል ሳናገግም ወደዚያ ክፉ ጠባይ እንወድቃለን፣ በተመሳሳይ መንገድ እንያዛለን፤ እጅግ ጥቂት ለኾነች የደስታ ሽርፍራፊ ብለንም ረጅምና ተደጋጋሚ ሥቃይን እንቀበላለን።

ዘውትር "በወጥመዶች መካከል እንደምትኼድ በገደልም መካከል እንደምትመላለስ ዕወቅ" የሚለውን ኃይለ ቃል ደጋግመን ለራሳችን ብንነግረው ግን ከእነዚህ ጉዳቶች ኹሉ እንጠበቃለን (ሲራ 9:13)

~ በእንተ ሐውልታት