2022-04-24 08:44:59
ተነስቷል
"እንደ ተናገረ ተነሥቶአልና በዚህ የለም፤ የተኛበትን ስፍራ ኑና እዩ።"
የማቴዎስ ወንጌል 28 : 6
ሰው ከወደቀበት መሬት ይነሳል፤ ሰው ህመሙ አገግሞ ከአልጋ ይነሳል፤ ሰው ከተቀመጠበት ወንበር ይነሳል። መነሳትን ለእነዚህ ዓላማዎች ብቻ ይጠቀምበታል። ሰው ከእነዚህ ነገሮች ሁሉ ተነስቶ በእግሩ ቢቆም ማንም አይገረምም አይደነቅም። ኢየሱስ ብቻ ሞትን ድል አድርጎ ተነሳ።
ሰው ተገንዞ ከተቀበረበት፤ ነፍሱ ወጥታ ስጋው በድን ከሆነበት፤ አንረሳህም በልባችን ትኖራለህ ተብሎ ድንጋይ ከተገጠመበት ውስጥ ተነሳ ሲባል ተረት ፌዝ ይመስላል። ምክንያቱም ዓለም ሁሉ በአንድነት የሚያውቀው የሞትን ኃያልነት፣ የሞትን ብቸኛ ጀግንነት፣ የሞትን አስፈሪነት ነው። ዛሬ ግን የሞት ኃያልነት ታሪክ ሊሆን ኢየሱስ በዝግ መቃብር ከሞት ተነሳ።
ዛሬ ግን የዓለምን የዕለት ተዕለት እውቀት የሚሽር፤ የዓለምን የዘመናት የልምድ መመላለስ የሚለውጥ ክስተት ተፈጥሯል። እርሱም ሞትን ድል አድርጎ የተነሳ ሰው ተገኝቷል።
ስንቱን አልቅሳ መሸኘት ልምዷ የሆነው ዓለም የኢየሱስን መሞት ለመቀበል አልተቸገረችም። ምክንያቱም ኢየሱስ ለእርሷ ከድሀ መንደር የተገኘ አንድ ምስኪን ሰው ነው። ይህ ምስኪን ሰው በብዙ መከራ ተደብድቦ መሞቱ አይደንቃትም። ኢየሱስ ከሞት መነሳቱ ግን ደንቋታል፣ እጇን በአፏ አስጭኗታል።
መሬት የፈጠራትን ዋጠችው ጌታዋን ነውና አልቻለችም ተፋችው፤ ፃድቅ ነውና ሲዖል ጉልበቱ ተብረክርኮ መዝጊያው ተሰበረ። ሞት ያልያዘውን ምንም ሊይዘው አልቻለም።
አንዲት የስንዴ ቅንጣት መሬት ላይ ስትዘራ ሞታ ትበሰብሳለች ግን በዛው አትቀርም ሺህ የስንዴ ፍሬዎችን ይዛ ትነሳለች ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ሞቶ ቢቀበርም ድንጋይ ቢገጠምበትም በዛው አልቀረም ሞትን ድል አድርጎ እኛንም ይዞን ተነሳ። ለክብር፣ ለህይወት፣ ለሹመት ይዞን ተነሳ።
ከጉልበታሙ ሞት ኃይሉን ነጥቆ እኛ ደካሞቹን የትንሳኤውን ኃይል አለበሰን፤ የማስፈራቱን ሞገስ ከሞት ገፍፎ ጠላታችንን የምናስፈራበት መለኮታዊ ሞገሱን አለበሰን። ይህ ሁሉ ክብር በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ ያገኘነው ነው።
ለህይወት ተነስተን በሞት ሰፈር አንገኝም፤ ለክብር ተነስተን እግዚአብሔርን በማያከብር ስፍራ አንገኝም፤ ለፅድቅ ተነስተን ከኃጢአት ጋር አንወዳጅም፤ ላንጠፋ ተነስተን ከሚጠፉት ጋር አናብርም፤ ለዘላለም ህይወት ተነስተን ለጊዜያዊ ህይወት አንባክንም። ክብር ለትንሳኤው ጌታ ይሁን።
<< በፈቃዱ ሞተ፣ ሞትን ይገድለው ዘንድ ሞተ፣ የሞቱትን ያድናቸው ዘንድ ሞተ፣ የተቀበሩትን ያስነሳቸው ዘንድ ተቀበረ፣ ህያዋንንም ይጠብቃቸው ዘንድ፣ ያደፉትን ያነፃቸው ዘንድ፣ ኃጥአንንም ያፀድቃቸው ዘንድ፣ የተበተኑትንም ይሰበስባቸው ዘንድ፣ የበደሉትንም ወደ ክብር ያመጣቸው ዘንድ፣ ወደ ጌትነት ይመልሳቸው ዘንድ ከሞት ተነሳ >>
ከሞት የተነሳው ጌታ ከሞት አስነስቶናል!
1.6K viewsበርናባስ ነኝ, 05:44