Get Mystery Box with random crypto!

+ #ዝም_ብለን_የምንጠላው_ሰው + ከሩቅ የምናውቀው አንዳንድ ሰው የለም? ብዙም አናውቀውም:: | ይሄ ነው ሐበሻ!

+ #ዝም_ብለን_የምንጠላው_ሰው +

ከሩቅ የምናውቀው አንዳንድ ሰው የለም? ብዙም አናውቀውም:: ቀርበን አውርተነው አናውቅም:: ስናየው ግን እንዲሁ ደስ የማይለንና ያለ ምክንያት የምንጠላው ሰው የለም?

"እሱን ሰውዬ ጥሎብኝ አልወደውም"

"አይ እሱን ልጅ ቀልቤ ትከሻዬ አልወደደውም"

"እኔ እንጃ ለምን እንደሆነ ባላውቅም አልወዳትም:: ምክንያቴን አትጠይቀኝ ግን በቃ እንዲሁ አልወዳትም"

ምንም ምክንያት ሳይኖረን እንዲሁ #የምንጠላው ሰው አለ::

እግዚአብሔር ግን
"አንድያ ልጁን እስኪሠጥ ድረስ ዓለሙን #እንዲሁ_ወዶአል" (ዮሐ 3:16)

ጠላቶቹ ሳለን በልጁ ሞት አዳነን እንደሚል እርሱ እኛን ለመጥላት ብዙ ምክንያት ነበረው:: እርሱ ግን እንዲሁ #ወደደን:: ከእኛ ምንም ባያገኝም ስለ እኛ ያለው ፍቅር የእንዲሁ ፍቅር (unconditional love) ነበረ:: እርሱ #እንዲሁ_ወዶናል እኛ ግን እንዲሁ ሰው እንጠላለን::
ያለ ምክንያት #መውደድ ቢያቅተን እንኳን ያለ ምክንያት #መጥላታችን (unconditional hate) ቢቀር ምናለ?
የሚያሳዝነው ያለ ምክንያት የጠላናቸውን ሰዎች የበለጠ ለመጥላት በልባችን እስር ቤት ውስጥ በጥላቻ ሰንሰለት እናስራቸውና የበለጠ ለመጥላት ስለእነርሱ ክፉ ክፉ ማስረጃ ለመስማት እንተጋለን:: ጥሩ ነገራቸውን ለመስማት አንፈልግም:: ክፉ ስንሰማ ግን "እኮ እኔ እኮ ዝም ብሎ ትከሻዬ ይነግረኝ ነበር" ብለን በደስታ እንፈነድቃለን:: እንዲሁ የጠላነውን ሰው በምክንያት ለመጥላት በመቻላችን ደስ ይለናል::

እኛ ሰውን ለመጥላት ምክንያት የምንፈልገውን ያህል እንዲሁ የወደደን እግዚአብሔር ግን እኛን ለመማር ሰበብ ይፈልጋል:: #ትንሽ በጎነት ቅንጣት ቅንነት ሲያገኝ እጅግ ይደሰታል:: ባለቅኔው "እግዚአብሔር መንግሥቱን በርካሽ ዋጋ ሸጠው:: በቀዝቃዛ ውኃ በዘለላ ዕንባ እና ማረኝ በሚል የወንበዴ ጩኸት!" እንዳሉት እሱ እኛን ይቅር ለማለት የሚታይ በጎነት ቢያጣ ልባችን ውስጥ ገብቶ ትንሽ መጸጸት ካለ ይፈልጋል:: #እንዲሁ ወዶናልና እንዲሁ ሊተወን አይፈልግም::

"እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለ ጠጋ ስለሆነ
ከወደደን ከትልቅ #ፍቅሩ የተነሣ በበደላችን ሙታን እንኳን በሆንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ሕይወትን ሠጠን"
ኤፌ 2:4

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
@ይሄ ነው ሐበሻ!
https://t.me/yihenewhabesha