Get Mystery Box with random crypto!

የመስተንግዶ ባለሙያዎች የአለባበስ ኮድ መመሪያ ዝግጅት በመጠናቀቁ በቅርቡ ፀድቆ ተግባራዊ ይሆናል | YeneTube

የመስተንግዶ ባለሙያዎች የአለባበስ ኮድ መመሪያ ዝግጅት በመጠናቀቁ በቅርቡ ፀድቆ ተግባራዊ ይሆናል ተባለ፡፡

በሆቴሎች የሚሠሩ ሴት የመስተንግዶ ባለሙያዎች ከሀገሪቱ ባሕል ውጪ የሆነውን አለባበሳቸውን ለማስተካከል የሚያስችል የአለባበስ ኮድ መመሪያ ዝግጅቱ በመጠናቀቁ በቅርቡ ፀድቆ ተግባራዊ እንደሚደረግ የአዲስ አበባ ባሕል፣ ኪነ ጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ ገለጸ።

የአዲስ አበባ ባሕል፣ ኪነ ጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ሂሩት ካሣው (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በአንዳንድ ሆቴሎች የሴት መስተንግዶ ሠራተኞች አለባበስ ከሀገሪቱ ባሕል ወጣ ያለ ነው።

ይህን ለማስተካከል የሚረዳ የመስተንግዶ ባለሙያዎች የአለባበስ ኮድ መመሪያ ዝግጅቱ ተጠናቆ ለከንቲባ ጽሕፈት ቤት እንዲፀድቅ በመላኩ መመሪያው በከተማዋ ካቢኔ በቅርቡ ፀድቆ ተግባራዊ እንደሚደረግ ይጠበቃል ብለዋል።

ለቱሪስቶች መስተንግዶ ሲሰጥ የሀገራችንን ባሕልና እሴት በጠበቀ መልኩ መሆን አለበት ያሉት ኃላፊዋ፤ በሆቴሎች ያለው የመስተንግዶ ባለሙያዎች አለባበስ ሥነ-ሥርዓቱን የጠበቀ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል።

ሂሩት (ዶ/ር)እንዳመላከቱት፤ አሁን ላይ የመስተንግዶ ባለሙያዎች በተለይም ሴቶች በአንዳንድ ሆቴሎች አማካኝነት ሥነ-ሥርዓቱን ያልጠበቀ አለባበስ እንዲለብሱ ይገደዳሉ። ድርጊቱ ከሴት ልጅ መብት አኳያ ክብርን ያልጠበቀ እና አሳፋሪ ነው ብለዋል።

መመሪያው ፀድቆ ሥራ ላይ ሲውል በሆቴሎች የሚሠሩ የመስተንግዶ ባለሙያዎች ወጥ የሆነ ዓለማቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የአለባበስ ኮድ እንዲከተሉ ይደረጋል ያሉት ኃላፊዋ፤ ይህም የኢትዮጵያን ባሕልና ወግ ያልጠበቀ የአለባበስ ሥነ ሥርዓትን ለመቆጣጠር እንደሚያስችል አስረድተዋል።

አሁን ላይ በአንዳንድ ሆቴሎች የሚታየውን ከባሕል ያፈነገጠ የመስተንግዶ ባለሙያዎች አለባበስ መስተካከል እንዳለበት የከተማው ነዋሪዎች ጥያቄ እንደሚያቀርቡ ገልጸው፤ መመሪያው ሲፀድቅ የሁሉንም ጥያቄ እንደሚመልስ አብራርተዋል። ሕጉ ከፍተኛ የገንዘብ ቅጣትም ጭምር ያለው በመሆኑ መመሪያውን በሚተላለፉ ላይ ቅጣት እንደሚጣል ጠቁመዋል።

የአለባበስ መመሪያውን ለማውጣት ቢሮው ሁለት ዓመት ሲሠራ መቆየቱን ተናግረው፤ ሕጉ ከፀደቀ በኋላ ወደ ርምጃ እንደሚገባ አመላክተዋል። ሕጉ እስኪፀድቅ የቁጥጥር ሥራ የሚሠራ ሲሆን በሚደረገው ክትትልና ድጋፍም አሁን ላይ ለውጦች መኖራቸውን ተናግረዋል።

በቱሪዝም ዘርፉ ውድድር በዓለም አቀፍ ይዘት ያለው በመሆኑ ደረጃውን ያልጠበቀ መስተንግዶ የሚሰጥ ከሆነ ቱሪስቶች ተመልሰው እንደማይመጡ የሚገልጹት ሂሩት (ዶ/ር)፤ በሆቴሎች መልካም መስተንግዶ እንዲሰጥ ለማስቻል ቢሮው በየዓመቱ ሁለት ሺህ ለሚደርሱ በሥራ ላይ ላሉ መስተንግዶ ሰጪ ባለሙያዎች ሥልጠና እንደሚሰጥ አስታውቀዋል።

በከተማዋ ያሉ ዓለም አቀፍ ሆቴሎች የመስተንግዶ ባለሙያዎቻቸው አለባበስ ጥሩ መሆኑን ጠቅሰው፤ በመጠኑ ከሴት የመስተንግዶ ባለሙያዎች የፀጉር አያያዝ ሥነ-ሥርዓት ጋር በተያያዘ የማይፈቀዱ ነገሮች በአንዳንድ ሆቴሎች የሚታዩ በመሆኑ እንዲሻሻሉ ክትትል ይደረጋል ብለዋል።

Via EPA
@YeneTube @FikerAssefa