Get Mystery Box with random crypto!

ሴራሊዮን ከሰው አጥንት በሚቀመም የአደንዛዥ እፅ መስፋፋት ምክንያት አስቸኳይ ጊዜ አወጀች! የሴራ | YeneTube

ሴራሊዮን ከሰው አጥንት በሚቀመም የአደንዛዥ እፅ መስፋፋት ምክንያት አስቸኳይ ጊዜ አወጀች!

የሴራሊዮኑ ፕሬዚደንት በአገሪቷ በተንሰራፋው ‘ኩሽ’ እየተባለ በሚጠራው የአደንዛዥ እፅ ምክንያት ብሔራዊ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አወጁ።ኩሽ የተለያዩ ሱስ የሚያስይዙ ግብዓቶችን በመደባለቅ የሚሰራ እፅ ሲሆን ለዓመታት በአገሪቷ ተንሰራፍቶ ይገኛል።በዚህ አደንዛዥ እፅ ውስጥ ከሚጨመሩ ግብዓቶች መካከል አንዱ የተፈጨ የሰው አጥንት ነው።በዚህም ምክንያት ከመቃብር ውስጥ አፅም ለማውጣት የሚቆፍሩ ሱሰኞችን ለማስቆም የጸጥታ አካላት በመካነ መቃብር ሥፍራዎች የሚያደርጉትን ጥበቃዎች አጠክረው ቆይተዋል።

ፕሬዚደንት ጁሊየን ማዳ ባዮ አስተዳደራቸው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲያውጅ ያስገደደውን ይህንን እፅ “የሞት ወጥመድ” ሲሉ የገለጹት ሲሆን በአገሪቷ ላይም የህልውና ቀውስ ፈጥሯል ብለዋል።በኩሽ እፅ የናወዙና እግራቸው ያበጠ በአብዛኛው ወንድ ወጣቶችን በሴራሊዮን ጎዳናዎች ጥጋ ጥግ ላይ ተቀምጠው ማየት የተለመደ ነው።ቢቢሲ ያነጋገረው አንድ ወጣት ከተዘፈቀበት ሱስ ለመውጣት እንዳዳገተው ተናግሯል።እስካሁን በዚህ እፅ ምክንያት የምን ያህል ሰዎች ሕይወት እንደተቀጠፈ በይፋ የተገለጸ ቁጥር የለም።

ሆኖም አንድ ሐኪም ለቢቢሲ እንደተናገሩት በዋና መዲናዋ ፍሪታውን በቅርብ ወራት ውስጥ ኩሽ በተባለው እፅ ምክንያት ባጋጠማቸው ውስጣዊ የሰውነት አካል ጉዳት ሳቢያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወጣት ወንዶች ሞተዋል።አደንዛዥ እፁ በአዕምሮ ጤና ላይም ከፍተኛ ቀውስ አስከትሏል።በአገሪቷ ውስጥ ያለው ብቸኛው የሥነ አዕምሮ ሆስፒታል እንደገለጸው በአውሮፓውያኑ 2020 እና 2023 መካከል ባሉት ዓመታት ውስጥ ከእፁ ጋር በተገናኘ ወደ ሆስፒታሉ የሚገቡ ሰዎች ቁጥር በ4 ሺህ በመቶ ገደማ ጨምሮ ቁጥራቸው 1 ሺህ 865 ደርሶ ነበር።

ከዚህም በተጨማሪ ኩሽ የተባለውን እፅ የሚጠቀሙ ሰዎች በመበራከታቸው ምክንያት በፍሪታውን ከተማ የሚገኘው ዋና መካነ መቃብር አፅም ለማውጣት መቃብር የሚቆፍሩ ወጣት ወንዶችን ለመከላከል የፖሊስ ጥበቃ እንዲደረግለት ለመጠየቅ ተገዷል።ምክንያቱ ግልጽ ባይሆንም የኩሽን እፅ ለመስራት ጥቅም ላይ ከሚውሉ በርካታ ግብዓቶች መካከል የተፈጨ የሰው አጥንት አንዱ ነው።

Via BBC
@YeneTube @FikerAssefa