Get Mystery Box with random crypto!

የሎተሪ አሸናፊ ባለመቅረቡ ስምንት ሚሊዮን ብር ተመላሽ መደረጉ ተገለጸ እያንዳንዳቸው የአራት ሚሊ | YeneTube

የሎተሪ አሸናፊ ባለመቅረቡ ስምንት ሚሊዮን ብር ተመላሽ መደረጉ ተገለጸ

እያንዳንዳቸው የአራት ሚሊዮን ብር ዕጣ ያላቸው ሁለት የሎተሪ ቲኬቶች አሸናፊዎች ባለመቅረባቸው ስምንት ሚሊዮን ብር ዛሬ የካቲት 29/ 2016 ዓ.ም ተመላሽ መደረጉን የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር አስታወቀ።

እነዚህ ሁለት ዕጣዎች ብሔራዊ ሎተሪ ከሚያሳትማቸው ከፍተኛ ዕጣ የሆነው 20 ሚሊዮን ብር የሚያስገኘው የእንቁጣጣሽ ሎተሪ ቲኬቶች መሆናቸውን የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ኮሙኒኬሽን ዳይሬከተር አቶ ቴዎድሮስ ንዋን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

በእንቁጣጣሽ ሎተሪ ከቀረቡት አምስት ቲኬቶች ሶስቱ ቀርበው 12 ሚሊዮን ብር ሁለት አሸናፊዎች ቢረከቡም የቀሪዎቹ ሁለት ቲኬቶች አሸናፊዎች ባለመቅረባቸው ገንዘቡ ወደ ተቋሙ ገብቷል ብለዋል።

ጳጉሜ 2015 ዓ.ም የወጣው የእንቁጣጣሽ ሎተሪ የሁለቱ ቲኬቶች ወይም የስምንት ሚሊዮን ብር አሸናፊ በቀን ስራ የሚተዳደር አንድ ግለሰብ ሲሆን ዕጣው ከወጣ ከሶስት ወር በኋላም ወስዷል።

ሌላኛው አሸናፊ የቀን ሰራተኛው የሚሰራበት መኪና አሽከርካሪ የሆነ ግለሰብ ሲሆን መስከረም ወር መጨረሻ ላይ መጥቶ የአራት ሚሊዮን ብር ሽልማቱን ወስዷል።

በ2010 ዓ.ም የወጣው 20 ሚሊዮን ብር የሚያስገኘው የእንቁጣጣሽ ሎተሪ በተመሳሳይ መልኩ ስምንት ሚሊዮን ብር ዕጣ ያላቸው ሁለት የሎተሪ ቲኬቶች የያዙ አሸናፊዎች አልቀረቡም።

የዕጣው አሸናፊዎች አለመቅረባቸውን በተመለከተ በሚዲያ ከተነገረ በኋላ ጊዜው ሊያልፍ አምስት ቀን ሲቀረው አንድ ግለሰብ ሶስቱን ቲኬቶች አቅርቦ 12 ሚሊዮን መቀበሉን አስረድተዋል።

የዕጣ አሸናፊዎች መጥተው ገንዘባቸውን አለመውሰድ በተደጋጋሚ እንደሚያጋጥም የሚገልጹት አቶ ቴዎድሮስ በዚህ አጋጣሚም ገንዘቡን የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ተመላሽ ያደርገዋል ብለዋል።

“ህብረተሰቡ ሎተሪ የመግዛት ከፍተኛ ፍላጎት አለው። የዚያን ያህል ደግሞ የማያዩ በርካታ ደንበኞች አሉ” ብለዋል።

በእንቁጣጣሽ የሎተሪ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ዕጣ ዓይነቶችም በተደጋጋሚ ይህ እንደሚያጋጥምም ገልጸዋል።

@Yenetube @Fikerassefa