Get Mystery Box with random crypto!

በቱርክ እና ሶርያ በደረሰ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ የሟቾች ቁጥር ከ11 ሺኅ በላይ ሆኗል በደቡ | YeneTube

በቱርክ እና ሶርያ በደረሰ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ የሟቾች ቁጥር ከ11 ሺኅ በላይ ሆኗል

በደቡብ ምስራቅ ቱርክ በጋዚያንቴፕ ከሶሪያ ድንበር አቅራቢያ በተከሰተዉ ኃይለኛ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ በቱርክ ብቻ ከ8,574 በላይ ሰዎች ህይወት አልፏል።የቱርኩ ፕሬዝዳንት ሬሴፕ ጣይብ ኤርዶጋን በሰኞው አሰቃቂ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ከሞት በሕይወት የተረፉ ሰዎችን በማግኘት አፅናንተዋል።

የቱርክ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ  ተከትሎ አስተዳደራቸው በሰጠው ደካማ ምላሽ ላይ ትችት ገጥሟቸዋል። አንዳንድ ክፉኛ በተጠቁ አካባቢዎች የሚኖሩ ቤተሰቦች የነፍስ አድን ጥረቱ ዝግ ያለ እንደነበር ገልፀዋል። ኤርዶጋን በመጀመሪያ የአደጋ ምላሽ ወቅት ችግሮች እንደነበሩ አምነዋል። ነገር ግን መዘግየቱ የተፈጠረው በተበላሹ መንገዶች እና አየር ማረፊያዎች የተነሳ ነው ብለዋል። በሃታይ ግዛት አንታክያ የሚኖሩ የ64 አመት አዛውንት "ከመሬት መንቀጥቀጡ ተርፈን ነበር ነገርግን እዚህ በረሃብ ወይም በብርድ እንሞታለን" ሲሉ ያለውን ሁኔታ ገልፀዋል።

ከ11 ዓመታት በላይ በዘለቀው የእርስ በርስ ጦርነት ክፉኛ በተጎዳችው ሶሪያ፣ በአደጋው ከ2,530 በላይ ሰዎች መሞታቸውንና 3,500 የሚያህሉ ሰዎች መቁሰላቸውን የሶርያ የመንግስትና ወዶ ገቡ የነጭ ቆብ የረድኤት ተቋም አስታዉቋል። የሶሪያ መንግስት በሚቆጣጠራቸው አካባቢዎች ወደ 250 የሚጠጉ ትምህርት ቤቶች በመሬት መንቀጥቀጡ ምክንያት ጉዳት ደርሶባቸዋል ሲል በሀገሪቱ መንግስት ስር የሚተዳደረው ሳና የዜና አገልግሎት የትምህርት ሚኒስትሩን ዳሬም ታባን ጠቅሶ ዘግቧል።

ጉዳት የደረሰባቸው ትምህርት ቤቶች በአሌፖ፣ ላታኪያ፣ ታርቱስ፣ ሃማ እና ኢድሊብ የሚገኙ መሆናቸውን ጠቁመው 126 ትምህርት ቤቶች ወደ መጠለያነት ተለውጠዋል።

ነጭ ሄልሜትስ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቤተሰቦች በፍርስራሹ ውስጥ እንደቀሩ እና የሟቾች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል አስጠንቅቋል። ቀደም ሲል የበጎ ፈቃድ ድርጅቱ አራት አባላቶቹ እና ቤተሰቦቻቸው በመሬት መንቀጥቀጡ መሞታቸውን አስታውቆ ነበር።

ቱርክ በዓለም ላይ ከፍተኛ የሆነ የመሬት መንቀጥቀጥ ከሚደርስባቸው ዞኖች ውስጥ አንዷ ነች። እ.ኤ.አ. በ 1999 በቱርክ ሰሜን ምዕራብ ክፍል በደረሰ ከባድ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ከ17,000 በላይ ሰዎች ህይወታቸው አልፏል።

Via:- ዳጉ ጆርናል
@Yenetube @Fikerassefa