Get Mystery Box with random crypto!

ከቀበሌ እስከ ዞን ያለውን አደረጃጀት ለውጥ ማምጣት በሚችል መንገድ ማደራጀት ተጀምሯል - ሌተናል | YeneTube

ከቀበሌ እስከ ዞን ያለውን አደረጃጀት ለውጥ ማምጣት በሚችል መንገድ ማደራጀት ተጀምሯል - ሌተናል ጄኔራል አስራት ዴኔሮ

በመተከል ዞን የግብረ ሃይሉ መሪ ሌተናል ጄኔራል አስራት ዴኔሮ ከቀበሌ እስከ ዞን ያለውን አደረጃጀት ለውጥ ማምጣት በሚችል መንገድ ማደራጀት ጀምረናል ብለዋል።

"ተፈናቃዮች ወደ ቀድሞ ቀያቸው ሲመለሱ አስተማማኝ ሠላም እንዲሰፍን የአካባቢውን ህዝብ የሚመስል የሚሊሻ አደረጃጀት ተፈጥሯል፤ ወደ 10 ሺህ የሚጠጉ የሚሊሻ አባላትም ከዛሬ ጀምሮ የመጀመሪያ ዙር ስልጠና ይወስዳሉ" ብለዋል፡፡

ሽፍታው የሚንቀሳቀስባቸውና የጸጥታ ስጋት ያለባቸው 32 ቀበሌዎች በሚቀጥሉት 15 ቀናት ሙሉ በሙሉ ከሽፍታው እንቅስቃሴ ነጻ እንዲሆኑ አመራሩ ታች ድረስ ወርዶ መስራት እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

የሠላም ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ስዩም መስፍን ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ከመመለሳቸው በፊት የአካባቢው ሠላም አስተማማኝ መሆኑን ማረጋገጥ እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡

ተፈናቃዮች በሚቋቋሙበት ጊዜ የሚፈጠረውን ውዝግብ ለመፍታት አስቀድሞ ትክክለኛ ቁጥራቸውን መለየት እንደሚገባ ገልጸው፣ ለዚህ ደግሞ የሠላም ሚኒስቴር ከሚመለከታቸው ጋር ይሰራል ብለዋል።

በሚኒስትር ማዕረግ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ አቶ ተስፋዬ በልጅጌም ተፈናቃዮችን ለመመለስ ማወያየት፣ የዕርቀ ሠላም ስራና ሌሎችም ቅድመ ሁኔታዎች እንደሚሟሉና ያ ሳይሆን የመመለሱ ስራ እንደማይሰራ አረጋግጠዋል።

ምንጭ፡- ኢዜአ
@YeneTube @FikerAssefa