Get Mystery Box with random crypto!

በእንተ ቆላስይስ 1፥16 የአይሁዳውያን መሠረተ እምነት ከሆኑት ዶግማዎች መካከል በቀዳሚነት የሚሰ | የነፍሴ ጥያቄዎች

በእንተ ቆላስይስ 1፥16

የአይሁዳውያን መሠረተ እምነት ከሆኑት ዶግማዎች መካከል በቀዳሚነት የሚሰለፈው የእግዚአብሔር ብቸኛ ፈጣሪነት ነው። የብሉይ ኪዳንም የመጀመሪያ ክፍል የእግዚአብሔርን አስገኚነት በመናገር የሚጀምረው በዚህ አግባብ ነው(ዘፍ 1፥1)። ኢሳይያስም በትንቢቱ የዘፍጥረት 1፥1 ምንባብ በሚያጸና መልኩ ይኽን ይላል፣ “ብቻዬን ሰማያትን የዘረጋሁ፣ ምድርን ያንጣለልሁ፣ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤”(ኢሳ. 44፡24)። ወደ አዲስ ኪዳን ስንመጣ ደግሞ ሁሉም ነገር የተፈጠረው በእግዚአብሔር ልጅ በክርስቶስ ኢየሱስ እንደሆነ ንዋይ ሕሩይ ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ በማለት ያረጋግጥልናል፦

“ሁሉ ነገር በእርሱ ተፈጥሮአል፤ በሰማይና በምድር ያሉ፣ የሚታዩና የማይታዩ፣ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ኀይላት፣ ገዦች ቢሆኑ ወይም ባለ ሥልጣናት፣ ሁሉም ነገር በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል።”
— ቆላስይስ 1፥16

ከላይ ባለው በጥቅሱ ውስጥ ሐዋርያው “ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋል”(ἐν αὐτῷ ἐκτίσθη τὰ πάντα ) ይለናል፡፡ ይኸውም በእግዚአብሔር አብ ልጅ ዓለማት መፈጠሩን እናም ልጁ ኢየሱስ ልክ እንደ አባቱ የአምላክነት ተግባርን ይከውን እንደነበር ያስገነዝበናል። ሆኖም የክርስቶስን አምላክነት የማይቀበሉ ወገኖች በሚከተለው ሙግት በቆላስይስ 1፥16 የተጠቀሰውን የጌታችንን ፈጣሪነት ለማስተባበል ይሞክራሉ። ይኸውም፤ “' ሁሉ ነገር በእርሱ ተፈጥሮአል' የሚለው አዲስ ፍጥረትን የሚያመለክት እንጂ ክርስቶስ ፍጥረታትን ካለመኖር ወደ መኖር ማምጣቱን የሚያመለክት አይደለም” የሚል ነው።

ከላይ የሚገኘው ሙግት ቢያንስ ሶስት መሠረታዊ ነጥቦችን ያላገናዘበ ነው። ይኸውም፤

1ኛ. መና*ቃን ይህ ትርጓሜያቸው የቋንቋ (Linguistic approach) ድጋፍን መሠረት ያላደረገ ነው። ምክንያቱም ἐκτίσθη “ኤክቲስቴ” የሚለው ቃል ቊማዊ ፍጥረትን እንጂ በፍጹም ተምሳሌታዊ ገለጻን ለማመልከት ግልጋሎት ላይ አይውልም[1]። ይህ ማለት የመና*ቃን ሙግት ከጅምሩ ወንዝ የማያሻግር ሆኖ ይቀራል ማለት ነው።

2ኛ.ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ በሮሜ 11፥36 የአብ ፈጣሪነትን የገለጠበትን ምንባብ ከቆላስያስ 1፥16 ጋር በትይዩ ተመልከት፤

አብ፦
“#ሁሉም(τὰ πάντα) ከእርሱ፣ #በእርሱ(δι’ αὐτοῦ)፣ #ለእርሱ(εἰς αὐτὸν) ነውና፤ ለእርሱ ለዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን።”
— ሮሜ 11፥36 (አዲሱ መ.ት)

ወልድ፦
“ሁሉ ነገር በእርሱ ተፈጥሮአል፤ በሰማይና በምድር ያሉ፣ የሚታዩና የማይታዩ፣ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ኀይላት፣ ገዦች ቢሆኑ ወይም ባለ ሥልጣናት፣ #ሁሉም(τὰ πάντα) ነገር #በእርሱና(δι’ αὐτοῦ) #ለእርሱ(εἰς αὐτὸν) ተፈጥሮአል።”
— ቆላስይስ 1፥16 (አዲሱ መ.ት)

በሁለቱም ጥቅሶች ውስጥ “ሁሉም” (τὰ πάντα “ታ ፓንታ”) ፤ “በእርሱ” ( δι’ αὐτοῦ ዲ አውቱ)፤ “ለእርሱ” (εἰς αὐτὸν ሔይስ አውቶን)፤ የሚሉትን ቃላቶችን ተጠቅሞአል። ስለዚህ ቆላስይስ 1፥16 ላይ የወልድን ፈጣሪነት አያሳይም ካሉን፣ በተመሣሣይ የሮሜ 11፥36 ምንባብም እንዲሁ የአብን ፈጣሪነት አያሳይም ብለው መደምደም ይኖርባቸዋል። ምክንያቱም ሐዋርያው ለሁለቱም አካላት ተመሣሣይ ሰዋስዋዊ ውቅር ተጠቅሞአልና።

3ኛ.የመና*ቃን ችግር ሐዋርያው በክርስቶስ ተፈጠሩ የሚለን በሰማይ የሚኖሩ ገዢዎች እና ሥልጣናትን መሆኑን አለማስተዋል ነው።

“ሁሉ ነገር በእርሱ ተፈጥሮአል፤ በሰማይና በምድር ያሉ፣ የሚታዩና የማይታዩ፣ ዙፋናት፣ ቢሆኑ ወይም ኀይላት፣ *ገዦች*(ἄρχαι) ቢሆኑ ወይም *ባለ ሥልጣናት*(ἐξουσίαι)፣ ሁሉም ነገር በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል።”
— ቆላስይስ 1፥16

ጳውሎስ በሌላ ጽሑፉ ላይ ክርስቲያኖችን የሚዋጉ ዓመፀኛ መናፍስት ፍጥረታትን በሚመለከት “ገዦች ” እና “ሥልጣናት” የሚሉትን ቃላት ተጠቅሟል።

“ምክንያቱም ተጋድሎአችን ከሥጋና ከደም ጋር ሳይሆን ከዚህ ከጨለማ ዓለም *ገዦች*(τὰς ἀρχάς)፣ *ከሥልጣናትና*(τὰς ἐξουσίας) ከኀይላት እንዲሁም በሰማያዊ ስፍራ ካሉ ከርኩሳን መናፍስት ሰራዊት ጋር ነው።”
— ኤፌሶን 6፥12 (አዲሱ መ.ት)

ይኽም ማለት ኢየሱስ ቅዱሳን ሆነ እርኩሳን መናፍስትን የፈጠረ አምላክ መሆኑን በግልጽ ያመለክታል።በአጠቃላይ ቅዱስ ጳውሎስ የክርስቶስን የበላይነት፣ አድራጊ ፈጣሪ መሆኑን በግልፅ እየተረከልን ነው። እርሱ ተራ መልአክ ወይም ተራ ሰው አይደለም፣ ነገር ግን ከሁሉም በላይ የሆነ፣ ሊመለክ የሚገባው ፈጣሪ ነው። ለእርሱ ከዘላለም እስከ ዘለዓለም ክብር ይሁን! የሚያመልከው አሜን ይላል።

[1] መጽሐፈ ጥበብ 1፥14፤ 10፥1፤ 11፥18፤ ዘዳግም 4፥32፤ ዘፍጥረት 6፥7; ሲራክ 24፥9፣ ሲራክ 15፥14፤ መጽሐፈ ኢዮብ 13፥18፤1 ቆሮንቶስ 11፥9፤ ኤፌሶን 3፥9፤ ሮሜ 1፥25፤ ራእይ 10፥6፣ ራእ 14፥7

(በወንድም ሚናስ)

Share join share
@yenebsetiyakewoch
@yenebsetiyakewoch