Get Mystery Box with random crypto!

#Day-285 ጽንአት (የህይወቴ ገጽ) “አንድ ሰው የሚያልቅለት ሲሸነፍ አይደለም፤ የሚያልቅለት | የደራሲያን ቤት 123@🇪🇹 የድሮ ሙዚቃዎች 📷📸

#Day-285 ጽንአት

(የህይወቴ ገጽ)
“አንድ ሰው የሚያልቅለት ሲሸነፍ አይደለም፤ የሚያልቅለት በበቃኝ ሲያቆም ነው” - Richard M. Nixon

በህይወትህ በአንድ ባመንክበትና ትክክል በሆነ ዓላማ እስከመጨረሻው ከመጽናት ውጪ ምንም ቁም ነገር ልታከናውን አትችልም፡፡ ዛሬ ይህንና ያንን እየጀመርክ እስከጥጉ ሳታደርሳቸው ነገ ደግሞ ወደሌላ ነገር ዘወር የማለት ለማድ ካለህ በተቻለህ ፍጥነት ይህንን ዘይቤ መቀየር እንዳለብህ ትመከራለህ፡፡ አብዛኛውን ጊዜ አንድን የጀመርነውን ነገር እስከጥጉ የማንወስድበት ዋነኛ ምክንያት ስንወድቅ ወይም ያልተሳካልን ሲመስለን ነው፡፡ ሆኖም፣ ውድቀት፣ አለመሳካት፣ እንቅፋትና የመሳሰሉት ሁኔታዎች በማንኛውም አንድን መልካም አላማ ይዞ በሚራመድ ሰው ሕይወት ውስጥ የማይቀሩ ሂደቶች ናቸው፡፡ ስለዚህም፣ አንደኛችንን ውድቀትን አያያዝ ብልሃት ማዳበር አስፈላጊ ነው፡፡

ሲወድቁ መነሳት በጽንአቱ የታወቀ ሰው ለወደቀበት ለእያንዳንዱ ክስተት መነሳትን አስመዝግቦ ወደ ፊት የሚራመድ ሰው ነው፡፡ መሳሳት፣ መውደቅ፣ መክሰር፣ ግብን አለመምታትና የመሳሰሉት ብዙዎችን ኃያላን የጣሉ ሁኔታዎች ለእሱ የእድገት ምክንያቶች እንጂ የተስፋ መቁረጥ ምንጮች አይደሉም፡፡

ውድቀትን እንደ አንድ ብቸኛ ክስተት ማየት
ወድቀው የሚቀሩ ሰዎች ሲወድቁ ውዳቂ ነኝ ብለው የሚያስቡ ሰዎች ናቸው፡፡ በተቃራኒው ስኬታማ ሰዎች አንድ ውድቀት የእነሱን ማንነት እንዲወስን አይፈቅዱም፡፡ ውድቀትን እንደ አንድ ብቸኛ ክስተትና እንደ ትምህርት እድል ነው የሚቆጥሩት፡፡

አደራረግን መቀየር ስኬታማ ሰዎች ነገሮችን በአንድ መልኩ ሞክረው አያቆሙም፡፡ ያልተሳካበትን መንገድ በመተው ሁኔታውን በሌላ መልኩ ይቀርቡታል፡፡ ለማከናወን በአይነ-ህሊናቸው ላዩት ነገር አንዱ መንገድ ካልተሳካ ሌላ መንገድ እንዳለው ጽኑ እምነት አላቸው፡፡

ሃላፊነትን መውሰድ ተሸናፊ ሰዎች ለተከሰተው ስህተት የሚወቀስ ሰው ይፈልጋሉ፡፡ በአንጻሩ ስኬታማ ሰዎች ለሰሩት ስህተት ሃላፊነትን የሚወስዱና የተሻለ መንገድን ለመፈለግ የሚነሱ ሰዎች ናቸው፡፡ አንዱ ሌሎችን በመውቀስ ሲረካና ሲያቆም፣ ሌላኛው ሃላፊነትን በመውሰድ መፍትሄ በማግኘት ይረካል፤ ወደ ፊትም ዘልቆ ይሄዳል፡፡

በውስጥ ላይ ማተኮር አሸናፊ ሰዎች ወሳኙ ነገር በዙሪያቸው የተከናወነው ሳይሆን በውስጣቸው የተከናወነው እንደሆነ ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ በእነርሱ ዙሪያም ሆነ በእነርሱ ላይ የሆነው ነገር ውስጣቸውን እስካልነካው ድረስ ምንም እንደማይሆኑ ያውቃሉ፡፡ የደረሰባቸው ማንኛውም አስከፊ ሁኔታ በውስጣቸው ያለውን ጽኑ እምነት ካልነካውና ትክክለኛውን ምላሽ መስጠትን ከለመዱ ወደግብ የመድረሳቸው አሸናፊነት ዘላቂነት ይኖረዋል፡፡