Get Mystery Box with random crypto!

​​​​╔═══❖•ೋ° °ೋ•❖═══╗ .' ከራስ ሽሽት '. | የካምፓስ ህይወት_MAHIR

​​​​╔═══❖•ೋ° °ೋ•❖═══╗
." ከራስ ሽሽት ".
. ( ሶፊያ አህመድ )

╚═══❖•ೋ° °ೋ•❖═══╝

. በ @tibebislam_nw የቀረበ
. ልብ አንጠልጣይ ታሪክ
.━─━────༺༻────━─━


#ክፍል_አምስት. . .⓹
❦•⊰❂⊱• ════ ❦


ሀሰን እስከ ምሽት 5 ሰአት ድረስ የሀዩን የስልክ ጥሪ እየጠበቀ የስልኩ ስክሪን ላይ አፍጥጧል። መሀል መሀል ላይ እንቅልፍ እያዳፋው ከስልኩ ጋር ሲጋጭ ብድግ ይልና ፊቱን በውሀ አርሶ መልሶ ይቀመጣል።

የእሷን ስልክ ምን ያህል በጉጉት እየጠበቀ እንደሆነ ብታውቅ ኖሮ ምናልባት ለመደወል ደቂቃዎችን ባላባከነች ነበር። በህይወታችን ምዕራፍ ውስጥ ስለኛ ደስታ ብለው እኛ ሳናውቀው በድብቅ ብዙ ዋጋ የሚከፍሉልን ሰዎች ይኖራሉ። አንዳንዴ ግን እኛ ለነሱ የምንሰጠው ምላሽ በተቃራኒው ሲሆን እጅግ ያማል!

ሀሰን ከሁለት አመት በላይ በሀዩ ፍቅር መሰቃየቱ ፣ በናፍቆት ተቃጥሎ ህመሙን ለሌላ ሰው አለማሰማቱን ከራሱና ከአላህ ውጪ ማንም አያውቀውም። እንደሌሎቹ ወንዶች ፍቅሩን ገልፆ ሀዩን የራሱ ሊያደርጋት የሚችልበት ድፍረት የለውም። ይሄንን ባህሪውንም የተረዳችው ሀዩ ብቻ ነበረች። ግን እሷም ዛሬ ከልቡ እንጂ ከእይታው ጠፍታ ስቃይ ሆናበታለች።

በእያንዳንዱ ዱዓው መሀል አላህን ሁዩን እንዲሰጠው ሳይለምነው ቀርቶ አያውቅም። ፅናቱ ፣ ተስፋ አለመቁረጡ ከምንም በላይ ጀግንነቱን ያሳያል! ሀዩ ጋር ስላለው ስሜት ፈፅሞ አያውቅም፤ ግን እሱ ጋር የሷ ፍቅር ልቡን ሞልቶታል። በቃ ተስፋው አላህና ፍቅሩ ብቻ ናቸው!

በፊት የነበረው ዝምተኝነት ተፈጥሮአዊ ቢሆንም ሀዩን ካጣት በኋላ ግን እየባሰ መምጣቱ ቤተሰቦቹን በጣም አስጨንቋቸዋል። እሱን ለማስደሰት ምንም ነገር ቢያረጉለትም የሱ ባህሪ ግን ሊቀየር አልቻለም። ደስታውን ሀዩ ስትሄድ አብራ ይዛው ሳትሄድ አትቀርም።


ሀዩ እንቅልፍ እንቢ ሲላት ፈቲን ቀስቅሳ ልታማክራት አሰበች። ግን ፈቲ ጭልጥ ያለ እንቅልፍ ስለወሰዳት ልትሰማት አልቻለችም።
ለሀሰን ለትደውልለት ስልኳን ታነሳና መልሳ ደሞ ታስቀምጠዋለች። ለምን መደወል እንደፈራች ግልፅ ነው። በዚ ሰዓት ጊዜዋን መስጠት የምትፈልገው ለቤተሰቦቿ ብቻ ነው። ከዚ በኋላም ሀሳቧን እንዳትቀይር ሀሰን የሰጣትን ደብዳቤ ከነስልክ ቁጥሩ ቀዳዳ ጣለችው። አበቃ!

ጠዋት ሀዩ በጊዜ ስለምትነሳ ሁሉንም ቀስቅሳ የሱብሂን ሰላት በጋራ ሰገዱ። አባታቸው አቶ ጀማል አንድ ስልክ ተወድሎላቸው ለማውራት ወጡ። ልክ አናግረው እንደተመለሱ

<< ሀዩ እስኪ ቤቱን ፏ አድርጉት! ትልቅ እንግዳ እየመጣ ነው... ብሎ ከኪሱ የተወሰነ ብር አውጥቶ ሰጣት።
ማነው እሱ? አለች ከእናቷ ሞት በኋላ እነሱ ቤት ሌላ ሰው መጥቶ ስለማያውቅ ግራ እየተጋባች።
እሱን በኋላ ታዪዋለሽ...ቶሎ በሉ እሱን ይዤው እስከምመጣ ተዘገጃጁ..ደሞ ቆንጆ ሆነሽ ጠብቂኝ! ብሏት እየተጣደፈ ከቤት ወጣ።

ቆንጆ ሆነሽ ጠብቂኝ ያላት ጆሮዋ ውስጥ ገብቶ ቀረ። ይሄን ያህል ማን ሊመጣ ነው ብላ ግራ ተጋባች።
በተሰጣቸው ብር አንዳንድ ነገር ገዝተው ምግብ ማዘገጃጀት ጀመሩ። ቤቱንም አፀዳድተው አሰማመሩት። ስራ እንደጨረሱ ሁሉንም ልጆች አጣጥባ ቆንጆ አደረገቻቸው። 3 ሰአት ላይ አባቷ ደውሎ ሰፈር እንደደረሱና ለባብሳ እንድትጠብቃቸው ነገራት።

ሀዩም የአባቷ ነገር ግራ ቢያጋባትም ቃሉን ማክበር ስላለባት መስተካከል ጀመረች። ከሁለት አመት በኋላ እራሷን ለማሰማመር ፊቷን በመስታወት አየችው። ትንሽ ከመጥቆርና ሰውነቷ ከመቀነሱ ውጪ ልክ እንደትናንቱ በጣም ቆንጆ ናት። ከሁለት አመት በፊት ትምህርት ቤት አንደኛ ስትወጣ እናቷ የገዛችላትን ቀይ ረጅም ቀሚስ ለብሳ እንዳማረባት ለመጠየቅ ወደነፈቲ ጋር ሄደች። ልክ ሳሎን እንደገባች አባቷ
አሰላም አለይኩም ልጆች... እያለ ወደውስጥ ገባ። ሁሉም ለአባታቸው መልስ እንኳን ሳይሰጡት ከሱ በኋላ ያለውን እንደዚ የተካበደለትን እንግዳ ለማየት አይናቸውን ወደበሩ ወረወሩት።

#ክፍል_ስድስት. ⓺. ይቀጥላል
❦ ════ •⊰❂⊱• ════ ❦