Get Mystery Box with random crypto!

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ነሐሴ ሃያ አምስት በዚህች ቀን ቅዱስ እንድ | ውሉደ ያሬድ ሰንበት ትምህርት ቤት



አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ነሐሴ ሃያ አምስት በዚህች ቀን ቅዱስ እንድርያኖስ በሰማዕትነት አረፈ ከእርሱም ጋር የነበሩ ሃያ አራቱ ባልንጀሮቹ በሰማዕትነት አረፉ።



ይህም እንድርያኖስ ከመክስምያኖስ መኳንንቶች አንዱ ነበረ፤ እርሱም የጐልማሶች አለቃ ነበረ። ለጣዖት መስገድን እምቢ ስለአሉ ንጉሡ ምእምናንን ሲያሠቃያቸው ቅዱስ እንድርያኖስ የሰማዕታትን የልባቸውን ቆራጥነትና በመከራቸው ላይ መታገሣቸውን ተመልክቶ አደነቀ።

እንዲህም አላቸው ይህን ያህል ስትታገሡ ምን ታገኛላችሁ ቅዱሳን ሰማዕታትም የሚጠብቀንን ተስፋ ለመናገር አንደበታችን አይችልም አሉት ስለ ዓለም ድኅነትም ክርስቶስ መከራ እንደተቀበለ ከብሉይና ከሐዲስ መጽሐፍ ነገሩት።

እንድርያኖስም በሰማ ጊዜ ጽሕፈትን ወደ ሚያውቁ ብልሆች ሰዎች ሔደና እኔ ከዛሬ ጀምሮ ክርስቲያን ነኝ ስሜን ከገድለኞቹ ጋራ ጻፉ አላቸው። ለንጉሥ መክስምያኖስም እንዲህ እንዳለ በነገሩት ጊዜ ጠርቶ እንድርያኖስ ሆይ አበድክን አለው እንድርያኖስም ከቀድሞው እብደቴ ተመለስኩ እንጂ እኔ አላበድኩም ብሎ መለሰለት። ንጉሡም ሰምቶ ወደ ወህኒ ቤት ከንጹሐን ሰማዕታት ጋራ እንዲጨምሩት አዘዘ። ከአገልጋዮቹም አንዱ ሄዶ ለሚስቱ እንጣልያ ነገራት በሰማችም ጊዜ ደስ እያላት ወደ ወህኒ ቤት ሄደች ሃያ አራቱ ቀዱሳን ሰማዕታት የባሏን ልብ ያጽናኑ ዘንድ ለመነቻቸው።

እርሱንም እንዲህ አለችው እንግዲህ ላህይህ ደምግባትህም ርስትህም ጥሪትህም አያስትህ ሁሉም ከንቱ ነውና ነገር ግን በእርሱ ዘንድ የማያልፍ መንግሥትን ትወርስ ዘንድ የክብር ንጉሥ ክርስቶስን ተከተለው ይህንንም ብላ ወደቤቷ ገባች።

ከዚህም በኋላ እንድርያኖስን ለፍርድ እንደሚያቀርቡት በአወቀ ጊዜ ሊሰናበታት ወደ ሚስቱ ሔጅሄደ መምጣቱንም ሰምታ የሸሸ መሰላት ደጇንም ዘግታ በውስጥ ሁና እንዲህ እያለች ዘለፈችው ትላንት ትላንትና ሰማዕት ተብለህ ዛሬ ክርስቶስን ካድከውን እንድርያኖስም ሰምቶ የሃይማኖቷን ጽናት አደነቀ እንዲህም አላት እኅቴ ሆይ እንድስናበትሽ ክፈችልኝ አላት። በሰማችም ጊዜ ከፈተችለት ከዚህም በኋላ ሁሉን እያነጋገራት እስከ እሥር ቤት ወሰዳት እንጣልያም ከዚያ በደረሰች ጊዜ የታሠሩትን ቅዱሳን ተሳለመቻቸው ሰማዕታት የታሠሩበትን ማሠሪያቸውንም ሳመች ቍስላቸውንም አጠበች።

ከዚህም በኋላ ንጉሡ ቅዱሳኑን ከእሥር ቤት እንዲያመጧቸው አዘዘ በመጡም ጊዜ ከሥቃይ ብዛት የተነሣ እንደደከሙ አያቸው። እንድርያኖስንም በፊቱ አቁሞ ለአማልክት ሠዋ አለው ቅዱሱም እርሱንና የረከሱ አማልክቶቹን ረገመ ንጉሡም የሆድ ዕቃው እስኪፈስስ ሆዱን እንዲደበድቡት አዘዘ በዚያን ጊዜም የእንድርያኖስ ዕድሜው ሃያ ስምንት ዓመት ነበር። ከዚህም በኋላ እንድርያኖስን ከባልንጀሮቹ ሰማዕታት ጋራ ወደ እሥር ቤት መለሱት እንጣልያም መጥታ የቅዱሳንን ደማቸውን ጠራረገችላቸው። እሊህ ቅዱሳንም እንድርያኖስን እንዲህ ብለው ተሳለሙት እንድርያኖስ ሆይ ስምህ በሰማያት በሕይወት መጽሐፍ ተጽፏልና ደስ ይበልህ።

ንጉሡም መስፍ አምጥተው የቅዱሳኑን ሁሉ ጭናቸውን በድጅኖ ይሰብሩ ዘንድ አዘዘ እንጣልያም የእንድርያኖስን እጆቹንና እግሮቹን በመስፍ ላይ ለማኖር ቀደመች ነፍሱንም በእግዚአብሔር እጅ እስከ ሰጠ ድረስ የእንድርያኖስን ዐጥንቶቹን ወታደሮች ቀጠቀጡ የቅዱሳኑንም ሁሉ ጭናቸውን ሰብረው ወደ እሳት ወረወሯቸው እሳቱ ግን ከቶ አልነካቸውም። ምእመናንም መጥተው በጨለማ ወደ ሌላ ቦታ ወሰዱአቸው የመከራውም ወራት እስቲያልፍ ሠወሩአቸው እንጣልያም የእንድርያኖስን የእጁን ቁራጭ ወስዳ በትራሷ ውስጥ አኖረችው ከዚህም በኋላ የሀገሩ ገዥ እንጣልያን ሊያገባት ወደደ በአወቀችም ጊዜ የባሏን የእጅ ቁራጭ ይዛ በመርከብ ሸሸች የቅዱሳኑ ሥጋ ወዳለበትም ደርሳ ወደ እነርሱ ይቀበሏት ዘንድ ለመነች ጌታችንም ልመናዋን ተቀብሎ አሳረፋት ከእነ ርሱም ጋራ ተቀበረች።

ለእግዚብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን ሰማዕታት አማላጅነት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ለዘላለሙ ትኑር አሜን።



በዚህችም ቀን ቅዱሱ አባት አባ ቢጻርዮን አረፈ። የዚህም ቅዱስ ወላጆቹ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ምእመናን ነበሩ። ባደገም ጊዜ የምንኵስና ልብስን ለብሶ እግዚአብሔርን ሊያገለግል ወደደ ዓለምንም ንቆ ወደ አባ እንጦንስ ሄደ ለእርሱም ደቀ መዝሙር ሁኖ ብዙ ዘመናት አገለገለው። ከዚህም በኋላ ወደ አባ መቃርስ ሄዶ፣ ቅዱሳን አረጋውያን መነኰሳትንም አገለገላቸው። በአስቄጥስም ገዳም ይዘዋወር ነበር በቤት ውስጥም አያድርም ነበር። ምንጣፍና ልብስ እስኪያጣ ድረስ ምንም ምን ጥሪት አልነበረውም መነኰሳቱም የማቅ ጨርቅ ይሰጡት ነበር። ወገቡንም ታጥቆ በመነኰሳቱ መንደር ይዞር ነበር በቤቶቻቸውም ደጃፍ እያለቀሰ ይቀመጥ ነበር። የማያውቀውም ወደርሱ በደረሰ ጊዜ አባቴ ሆይ ምን ያስለቅስሃል ይለው ነበር። እርሱም ንብረቴን ስለዘረፉኝ እንዳልሞት ሸሸሁ ከወገኔም ክብር ተለይቼ በጕስቍልና ወደቅሁ ይለው ነበር። የቃሉንም ምልክት የማያውቅ የጠፋውን ገንዘብህን እግዚአብሔር ይመልስልህ ብሎ ካለው ይሰጠው ነበር። እርሱም ተቀብሎ ይሄድና ለሌለው ይሰጥ ነበር። የቃሉን ምልክት የሚያውቅ ግን በፈቃደ ነፍስ የሚሠሩ ትሩፋትን ሰይጣን ከሰዎች የማረካቸው መሆኑን ልብ ብሎ ያስተውል ነበር። አባቶችም ጭንቅ የነበረ ተጋድሎውን ስለርሱ ይናገሩ ነበር። እርሱ አርባ መዓልትና አርባ ሌሊት ከቶ ሳይተኛ ቁሞ ኖሯልና። በምንኵስናውም ወራት ብዙ ጊዜ በየአርባ ቀን ጾመ እነሆ እንዲህ እየተጋደለ ድንቆችንም እያደረገ ኀምሳ ሰባት ዓመታት ኖረ። ቅዱሳን አባ ዱላስና አባ ዮሐንስም ከተአምራቱ ተናገሩ እነርሱ ከርሱ ጋር ወደ ኤርትራ ባሕር ዳርቻ ሄዱ እጅግም በተጠሙ ጊዜ እንደተጠሙ አውቆ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ መራራውንም ውኃ ጣፋጭ አድርጎላቸው ጠጥተዋል።

በሁለተኛም ጊዜ ወደ ፈሳሽ ውኃ ደርሶ መሸጋገሪያ አጣ ወደ ጌታችንም ጸለየ ያን ጊዜም እንደ የብስ በባሕሩ ላይ ሄደ። በአንዲት ቀንም የከበሩ አባቶች በጸሎታቸው ያድኑት ዘንድ ጋኔን ያደረበትን ሰው ወደ አስቄጥስ ገዳም ሰዎች አመጡ አባቶችም እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ እርሱ ከከንቱ ውዳሴ ስለሚሸሽ ብንነግረው ይህን ጋኔን የያዘውን አያድነውም። ከዚህም በኋላ ምክንያት አድርገው አባ ቢጻርዮን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለጸሎት ወደሚቆምበት ቦታ ያንን ጋኔን ያደረበትን ሰው አስተኙት። አባ ቢጻርዮንም በገባ ጊዜ ያን ጋኔን ያደረበትን ሰው ተኝቶ አገኘውና ቀሰቀሰው እጁንም ይዞ ተነሥ አለው ያን ጊዜም ድኖ ተነሣ አእምሮውም ተመለሰ። ያዩትም እጅግ አደነቁ ለሚፈሩት ስለሚሰጠው ጸጋውም እግዚአብሔርን አመሰገኑት። የዚህም ቅዱስ ተአምራቶቹ ከነገርናችሁ የበዙ ናቸው እግዚአብሔርንም አገልግሎ በሰላም አረፈ።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ ጻድቅ ጸሎት ያማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።



ዳግመኛም በዚህች ቀን የሰማዕት ኤልያኖስና የእኅቱ አውዶክስያ መታሰቢያቸው ነው። በረከታቸው ከእኛ ጋራ ለዘላለሙ ትኑር አሜን።

አሜን።

"ጽዮንን የሚወዳት አይደክምም"
ቅዱስ ያሬድ