Get Mystery Box with random crypto!

በስምንት ቢሊየን ብር ወጪ በግንባታው ዘርፍ የልህቀት ማዕከል ሊገነባ መሆኑ ተገለጸ ለልህቀት ማ | Wuhalek Ethiopian Construction Talk Show. 0941431700

በስምንት ቢሊየን ብር ወጪ በግንባታው ዘርፍ የልህቀት ማዕከል ሊገነባ መሆኑ ተገለጸ

ለልህቀት ማዕከሉ ግንባታ በለገጣፎና በሰንዳፋ መካከል ባለ በረክ በሚባል ወረዳ ውስጥ 14 ነጥብ 2 ሄክታር መሬት መፈቀዱ ተነግሯል

ሰኞ ነሐሴ 23 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በግንባታው ዘርፍ የሚታየውን የአቅም ውስንነት በዘላቂነት ለመፍታት በስምንት ቢሊየን ብር ወጪ በመጪው ህዳር ወር የልህቀት ማዕከል ሊገነባ መሆኑን የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡

በኢ.ፌ.ዴ.ሪ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ታምራት ሙሉ ለኢፕድ እንደገለፁት፤ በተደጋጋሚ በኮንስትራክሽን ዘርፉ ላይ የሚታዩና አገርን የሚጎዱ ክፍተቶችን በማያዳግም መልኩ ለማረም እየተሠራ ነው፡፡ ከሚወሰዱ እርምጃዎች መካከልም በኮንስትራክሽን ዘርፍ የሚታየውን የአቅም ውስንነት በዘላቂነት ለመፍታት በመጪው ህዳር ወር የልህቀት ማዕከል ይገነባል፡፡

የልህቀት ማዕከሉ የተለያዩ ጠቀሜታዎች ቢኖሩትም፤ በተለይ የኮንስትራክሽን ዘርፉ ላይ የሚታየውን የአቅም ውስንነት ይቀርፋል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ የኮንስትራክሽን ታሪክ ቢኖራትም በዘርፉ ተወዳዳሪ አለመሆኗ የሚያስቆጭ መሆኑን ተናግረዋል።

እንደ ኢንጂነር ታምራት ገለፃ፤ ትላልቅና ውስብስብ ፕሮጀክቶችን ጨምሮ በአገሪቱ የኮንስትራክሽን ዘርፉ ግብዓቶች ጥራት የሚረጋገጠው ወደ ውጭ አገር ናሙና ተልኮ ነው፡፡ ይህ ለብዙ አደጋዎች የሚያጋልጥና የአገሪቱንም የኮንስትራክሽን ታሪክ የማይመጥን ነው። ስለሆነም ይህን የልህቀት ማዕከል በመገንባት ሜጋ ፕሮጀክቶችን ጨምሮ ሌሎች የጥራት ማረጋገጫ የሚፈልጉ የግንባታ ግብዓቶችን በአገር ውስጥ እንዲሠሩ የሚያስችል ይሆናል፡፡

በአገራችን የኮንስትራክሽን ዘርፍ ብዙ ዓመታትን ያስቆጠረ ቢሆንም፤ በሚገባው ልክ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ መሆን ያልቻለው መሰል ማዕከላት ባለመኖራቸው መሆኑን ጠቁመው፤ አሁንም ድረስ በአገሪቱ የሚከናወኑ ትላልቅና ውስብስብ የሚባሉ ፕሮጀክቶች በውጭ ፕሮጀክቶች እየተሠሩ መሆናቸው አሳሳቢና ሊቀረፍ የሚገባ ነው ብለዋል፡፡

በተጨማሪም የልህቀት ማዕከላት አለመኖራቸው የዘርፉ ኢንዱስትሪ በውጪ የግንባታ ምርቶች፣ ኮንትራክተሮች እና የግንባታ ዕቃዎች ጥራት መለኪያዎች ላይ ጥገኛ እንዲሆን ማድረጉን ገልፀው፤ ማዕከሉ ከውጭ ጥገኝነት ለመላቀቅና የባለሙያዎች አቅም ከመገንባት አንፃር ጉልህ ሚና ይኖረዋል ሲሉ ገልፀዋል፡፡

የልህቀት ማዕከሉን መገንባት ከላይ የተጠቀሱትን የኮንስትራክሽኑን ዘርፍ ችግሮች ለመቅረፍ ይረዳል። በመሆኑም መንግሥት ለግንባታው የሚሆን መሬት ከመስጠቱም ባሻገር የዲዛይን ሥራዎች በመጠናቀቅ ላይ መሆናቸውን ኢንጅነሩ ጠቁመዋል፡፡ በመንግሥት አስፈላጊው በጀት ተይዞለታልም ነው ያሉት፡፡

ለልህቀት ማዕከሉ ግንባታ በለገጣፎና በሰንዳፋ መካከል ባለ በረክ በሚባል ወረዳ ውስጥ 14 ነጥብ 2 ሄክታር መሬት መፈቀዱንና በአካባቢው ላይ ለልማት የሚነሱ አርሶ አደሮችም ተገቢው የካሳ ክፍያ ተከናውኖ መሬቱን መረከባቸውን ተናግረዋል፡፡

የዲዛይን ሥራው ከኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ዲዛይንና ቁጥጥር ሥራዎች አማካኝነት እየተሠራና መገባደድ ላይ መድረሱን እንዲሁም ለመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ ከ300 ሚሊየን በላይ ብር መመደቡን ጠቁመዋል፡፡

የልህቀት ማዕከሉ የግንባታ ግብዓቶችን ጥራት ለማረጋገጥ የሚረዱ ላቦራቶሪዎች የሚኖሩት፤ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ልምምድ የሚደረግበት፤ ጥናትና ምርምር የሚካሄድበት እና የምህንድስናና የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት አቅም ግንባታ ሥልጠናዎች የሚከናወኑበት ይሆናል፡፡

የማዕከሉ ግንባታ በተለያዩ ምዕራፎች ተከፋፍለው እንደሚሠሩ የገለፁት ኢንጂነር ታምራት፤ በ2015 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ምዕራፍ ሥራዎች ይጀመራሉ ብለዋል፡፡ የመጀመሪያው ምዕራፍ በሦስት ዓመት ውስጥ የሚጠናቀቅ ሲሆን፤ ቀሪው ደግሞ በኹለት ዓመት ውስጥ የሚጠናቀቅ ይሆናል ተብሏል፡፡ በአጠቃላይም የልህቀት ማዕከሉ ግንባታ ስምንት ቢሊየን ብር የሚጠጋ ገንዘብ እንደሚፈጅም ተገልጿል፡፡
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n