Get Mystery Box with random crypto!

አነቃቂው መድረኩ ላይ እየተንጎራደደ 'በህይወቴ ምርጡ ጊዜ ሚስቴ ያልሆነች ሴት እቅፍ ውስጥ ያሳለፍ | ወግ ብቻ

አነቃቂው መድረኩ ላይ እየተንጎራደደ "በህይወቴ ምርጡ ጊዜ ሚስቴ ያልሆነች ሴት እቅፍ ውስጥ ያሳለፍኩት ጊዜ ነው!" ሲል ተነገረ።

ለመነቃቃት አዳራሹ ውስጥ የተሰበሰበው ሰው በድንጋጤ ክውታ ተዋጠ።

አነቃቂው ንግግሩን በመቀጠል "እናም ያቺ ምርጥ ሴት፣ ዘጠኝ ወር በሆዷ፣ ከእዛም በጀርባዋ፣ ከእዛም በእቅፏ ያሞላቀቀችኝ ምርጥ ሴት፣ ያቺ ስጦታ ሳልሰጣት ያቀፈችኝ ምርጥ ሴት እናቴ ናት?!" ሲል ተናገረ።

አዳራሹ በሳቅ እና በጭብጨባ ተሞላ።

**
ከሳምንት በኋላ በእዚህ የአነቃቂ ንግግር ላይ የተገኘ ሥራ አስኪያጅ ድግስ ብጤ አዘጋጅቶ ዘመድ አዝማድ፣ ጓደኛ ቤቱ ጠራ። ዝግጅቱ ላይ ወዲህ ወዲያ እያለ ሰው ሲያስተናግድ፣ ሲጎርስ ከመጠጡ ሲጎነጭ ሞቅ ከማለት አልፎ ሰከረ።

ይሄኔ ነው እንግዳው ምግብ በልቶ፣ ጠጥቶ ሳይዝናና መሄድ የለበትም ሲል በአነቃቂ ንግግር ስልጠና ላይ ተገኝቶ የሰማውን ቀልድ ለታዳሚው ለመጋበዝ በመወሰን ድምጹን ጠራርጎ ንግግር የጀመረው።

"በህይወቴ ምርጡ ጊዜ፣ ሚስቴ ያልሆነች ሴት እቅፍ ውስጥ ያሳለፍኩት ጊዜ ነው!" ሲል ተነገረ።

ይሄኔ የሚስቱ ፊት፣ እንደመቅላት፣ አመድ እንደ መንዛት፣ አሸቦ እንደመምሰል ከእዛም ወደ ጥቀርሻነት ተለወጠ። ንግግሩን የሰማው የድግሱ ታዳሚ በድንጋጤ የጨው አምድ መሰለ።

ይሄኔ ባልየው በአነቃቂ ንግግሩ ወቅት የተነገረው የቀልዱ ሁለተኛ ክፍል ምን እንደሆነ ስለዘነጋ ለማስታወስ ለሀያ ሰከንዶች ያህል በዝምታ ከቆየ በኋላ ትዝ ሊለው ስላልቻለ ጎሮሮውን ጠራርጎ...

"...እናም ያቺ ሴት ማን እንደሆነች አላስታውስም!" ሲል ንግግሩን ደመደመ።
**
ማስታወሻ፣

ሰውየው ንግግሩን እንደጨረሰ ከሚስቱ በተሰነዘረበት የውስኪ ጠርሙስ ፍንከታ ምክንያት ኮማ ውስጥ ስለገባ አሁን ላይ ሆስፒታል ተኝቶ እስኪነቃ እየታከመ ይገኛል።

@wegoch
@wegoch
@paappii

By #Tilahun ango Girma