Get Mystery Box with random crypto!

°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°    ዘርሽ ቢቆጠር ጉድፍ የለበትም።የጀግና ዘር | ወግ ብቻ

°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°
   ዘርሽ ቢቆጠር ጉድፍ የለበትም።የጀግና ዘር ነሽ!በአባትሽ በኩል ቢኬድ ቅድመ አያትሽ የሚኒሊክ ዘብ ጠባቂ የቅርብ ወዳጅ ነበሩ።በእናትሽም በኩል ቢኬድ ምንጅላትሽ የሽምብራ ቆሬ ጦርነት ላይ የግራኝ አህመድን አሽከር በቀይ ጥይት ግራ ቂጡን ነድለውት ሲቅመደመድ ኖሮ መሞቱን አዲስ ዘመን ጋዜጣ የሆነ ጊዜ ላይ አስነብቧል።

  በማን እንደወጣሽ ባይታወቅም፣ዕድልሽ ይሁን ተፈጥሮሽ ግልጽ ባይሆንም፣ከአንድ ወንድ አትረጊም።ተረግመሽ ነው መሰል ከሚያጋጥሙሽ ወንዶች 25 % የሚሆኑት የጥሪ ማሳመሪያ ተጠቃሚዎች ናቸው። ልክ ስትደውይ
  "ወይ ሞልቶ ላይሞላ
   ለዚች ዓለም ኑሮ
   እኔ አልጨነቅም
   ከዛሬ ጀምሮ" የሚል መፈክር ይሁን ዘፈን ያልለየለት ብሶት ትሰሚያለሽ።(ሳትረገሚማ አትቀሪም!) ሌሎቹ 25 % የሚሆኑት ደግሞ የትንሽ ጣታቸውን ጥፍር የሚያሳድጉ ናቸው።ደህና መትረየስ እንዳነገበ ጀግና በጥፍራቸው አይን አ*ቸውን እየመነገሉ፣የከናፍራቸው ጫፍ ላይ የወጣችን ቡግር እየፈነቀሉ ቀንሽን ለሰማይ ለምድር የከበደ 'ትራጀዲ'ያደርጉብሻል።(በእርግጠኝነት ምንጅላትሽ የመቱት አሽከር ነው የረገመሽ!)

'እፎፎፎይ'ብለሽ ወደ ሌላኛው 25% ስትሮጪ መፈናፈኛ እስኪያጣ ሱሪውን የሚያስጠብብ፣ቀሪው 25% ደግሞ የሞተ ፍየል በብብቱ የያዘ እስኪመስል ድረስ አስጨናቂ ጠረን ያለው፣ላቡ ከብብቱ ስር እንደቀበና የሚወርድ ክልል-ዘለል የሆነ ፌደራላዊ ግማት ላይ ትወድቂያለሽ ።

"እና እንዴት ነው ኑሮው?"ይልሻል አፉ እንደተቀየደ ፈረስ ድዱን እያሰጣ።

  "ደህና ነው መቸም" ትያለሽ ሰው ያገኘሽ መስሎሽ።

"እናስ ተማሪ ነሽ ሰራተኛ?"ይልሻል  እንዳገጠጠ አንዴ ከላይ ወደታች፣አንዴ ደግሞ ከታች ወደ ላይ scan እያደረገሽ።

  አንድ ቀን አልፎልሽ በፀሃፊነት ወደምትሰሪበት ድርጅት ለጉዳይ የመጣ ነጋዴ ነኝ ባይ ትተዋወቂያለሽ...ቀጠሮ ትይዣለሽ።ደሞዝሽ በፈቀደው መጠን ለመዘነጥ ትሞክሪያለሽ።ከታች እናትሽ መሰረተ-ትምህርት ሲማሩ ለብሰውት ይሄዱ የነበረውን ቀሚስ ከወገቡ አስቆርጠሽ በሰውነትሽ ልክ አሰፍተሽ ለብሰሻል።ከላይ ከሰልቫጅ ተራ በ80 ብር የገዛሻትን ቲሸርት ጣል አድርገሻል።ባለፈው ወር እቁብ ሲደርስሽ የገዛሻትን የ 200 ብር ሽቶ "ምናባቱ!ሺህ ዓመት አይኖር!"ብለሽ የግራ ብብትሽ ስር አንዴ ረጭተሻታል። የቀኙንም'ኮ ልትረጭው ነበር ግን አሰብ አረግሽና "መቸስ ከጎኑ ስሄድ አንድ ጎኔ ነው በሱ በኩል የሚሆን"ብለሽ ተውሽው።ኤታባቱ!ሺህ ዓመት አይኖር!

  ፀጉርሽን በ 50 ብር ካስክ አፍሪካዊ ለዛውን ታሳጭዋለሽ።ተመስገን ነው!ሰሞኑን ማበጠሪያ አይሰበርብሽም!በፈቃደኝነት የሚያፈናቅል ሽታ ያለውን ሎሽንሽን መላ ሰውነትሽን ተቀብተሻል...ለእግርሽ ግጣም ከቆራሌው የተረፈች አንዲት ክፍት ጫማሽን ግጥም ታደርጊና ትሄጃለሽ !ወደ 'ዴትሽ'

ሰውዬሽም ከሞላ ጎደል ዘንጧል።

  "ምን ይምጣ የሚበላ?"
  "አንተ የተመቸህ ይሁን"
ጥብስ ይታዘዝና ጠበሳው ይቀጥላል ። ጥብሱ እስኪደርስ...

"እና...ደሞዜ 3000 ብር ነው አልሺኝ?"
"3200"
"ያው ነው...አሁን እኔ ወደዚህ ስመጣ የኮንትራት ታክሲ 200 ብር ነው የከፈልኩት" ብሎ ኩም ያረግሻል።ጥብሱ ደርሶ ከተበላ በሁዋላ
  "እና የቤት ኪራይ 600 ብር ነው የምከፍለው አልሽኝ?"
  "550"
  "ያው ነው 50 ብር ማለትኮ ለአስተናጋጅ የሚሰጥ 'ቲፕ' ነው"
  "እሱሰ ልክ ነህ"ከጥቂት ዝምታ በሁዋላ
"ተጫወች እንጂ ምነው?እኔ ዝም የሚል ሰው አልወድም...የምሬን ነው!የሚያስጨንቅሽ ነገር ካለ ንገሪኝ"
"ኧረ የለም!አመሰግናለሁ"
  "ምስጋና ስንቅ አይሆንም ...ባይሆን..."
  "ባይሆን ምን?"
  "ባይሆን ሌላ ጊዜ በደንብ ታጫውችኛለሽ እ?ሃሃሃሃሃ"
በኮንትሮባንድ የገባ ሳቅ ይለቅብሻል።
"እንሂድ እየመሸ ነው"ትያለሽ ሰዓትሽን አየት ታደርጊና።
"ኧረ ገና ምኑን ያዝነውና!አይዞሽ እኔ ራሴ ነኝ በኮንትራት ታክሲ ቤትሽ የማደርስሽ"ብሎ ሳይሰማሽ መጠጥ ያዛል ።'አልኮል አልጠጣም' ብለሽ ለመገገም ትሞክሪያለሽ።
"ምናይነቷ ናት ባካችሁ?ልንዝናና አይደል ወይ የመጣነው?እንደ ህፃን ፋንታ ልትጠጪ ነው?"ብሎ እንደምንም ቀበጣጥሮ አንድ ቢራ ያስከፍትልሻል።እየተሽኮረመምሽ መቀማመስ ትጀምሪያለሽ።ሞቅ ሲልሽ ፍርሀት ቢጤ ይሰማሽና

"እየመሸ ነው ብሄድ ሳይሻል አይቀርም"ስትይ ሰዓቱን አየት ያደርግና 
"ሆሆሆሆ እንዴት ያለችው ላይ ጣለኝ ባካችሁ?ገናኮ 3 ሰዓት ነው...ምን የሚያስቸኩል ነገር አለ?ገብተሽ አታበስይ ምናለሽ?"

"እሱስ አላበስልም...አከራዬ ደስ አይላቸውም እንጂ..."
"አአአአይ ...ለዛሬ የኪራይ ቤትሽን እርሻት...እዚሁ ቆንጆ room እይዝልሻለሁ" ሲልሽ መፍራት ትጀምሪያለሽ።

"ኧረረረረ አያስፈልግም ቤት እገባለሁ"ስትይ
"ለማንኛውም እየጠጣሽ "ይልሽና በተቀመጥሽበት ትቶሽ ወደ እንግዳ ተቀባዪአ ይሄዳል።ከቆይታ በሁዋላ አንድ ቁልፍ ይዞ ይመጣል።

"ምን...ባክሽ...' 'ሩሞቹ' ተይዘው አልቀዋል' አለችኝኮ...አይዞሽ double bed ነው የያዝኩት...መቼም የመሸበት አላሳድርም አትይም ሃሃሃሃሃ"
አሁን የምር...የምር...የምር ትፈሪያለሽ።ያቺ ተቆንጥጣ ያደገችዋ...ያቺ በዘመን ግሳንግስ ቀለሟን ያደበዘዝሽው አንቺነትሽ እየተፍገመገመች
"አምልጪ!...ተበላሽ! ትልሻለች።
"አአአአይ....ኧረ አትቸገር እዚሁ አካባቢ አንድ ጓደኛ አለችኝ እሷ ጋር እደውላለሁ..."
"ቆይ አላመንሽኝም ማለት ነው?ስታስቢው በጥብስና በቢራ የሴትን ገላ የምገዛ ርካሽ እመስላለሁ?I really feel sorry እንደዛ ካሰብሽኝ"
"ኧረ...እንደዛ ማለቴኮ አይደለም...አስቸገርኩህ ብዬ ነው እንጂ!እሺ በቃ" ትይውና

"እሳትና ጭድ አንድ ክፍል ውስጥ ያድሩ ዘንድ ደግ አይደለም...አንዳቸው የሌላቸው መጥፊያ ይሆናሉና " የሚለውን ቃል ጥሳችሁ አንድ ጣራ ስር ታድራላችሁ።

ጧት ለሰዓታት የተቃጠልሽበት ፀጉርሽ ፈርሶ...ጋኔል ያደረባት ጃርት መስለሽ ወደሰፈርሽ ትመለሻለሽ።ወደ መዳረሻሽ ገደማ ፋርማሲ ታይና ጎራ ትያለሽ።ሰው የተባለ ፍጡር ገና ከእናታቸው ማህፀን ሳሉ ጀምሮ የማያምኑት አከራይሽን ፋርማሲ ውስጥ ስታያቸው ልብሽ በአፍሽ ልትወጣ ትደርሳለች።በተጠራጣሪ አይኖቻቸው ከእግር እስከራስሽ አብጠርጥረው ያዩሽና
"አንች የኔ ዓለም የት ጠፍተሽ ነው ስታሸብሪን ያመሸሽ?"ይሉሻል።

"እንዴት አደሩ እትዬ?ማታ...ኮ አምሽቼ የምጨርሰው ስራ ኖሮኝ ሰዓት ስለሄደብኝ እንዳልረብሻችሁ ብዬ እዛው አድሬ ነው"

"ኧሯሯሯሯሯ!እና ስልኩ ቢከፈት ምን ይላል አደራሽ?...በዚህ በከፋ ዘመን እንደው ሰውስ ያስባል አይባልም?ጅብ በመውጫው አንችን ፍለጋ እንጉለሌ ልህድ?"

"ይቅርታ በጣም"

"የሆነው ሁኖ...ምን ልትገዥ ነው?"
ብለው እጅ ከፉ እንደተያዘ ሌባ ያፋጥጡሻል።

"እ...እንቅልፉ ነው መሰል ትንሽ ራሴን አሞኛል ማስታገሻ ልግዛ ብዬ"

"እህህህህም ነው?በይ...ደህና ዋይ"ብለውሽ ከፋርማሲው ሲወጡ የዘመናት ሀጥያትሽ የተፋቀልሽ ያህል ይቀልሽና "እፎፎፎፎፎፎይ!"ትያለሽ በሆድሽ።የምትገዥውን ገዝተሽ ስትወጪ አከራይሽ ፋርማሲው በር ላይ ቆመዋል።ስታያቸው ስቅቅ ብለሽ ታልፊያቸዋለሽ።ከማለፍሽ ወደ ፋርማሲው ድጋሚ ሲገቡ ታይና ጠጋ ብለሽ ለማየት ትሞክሪያለሽ።

"የኔ ዓለም...እንደው አሁን የወጣችቱ ልጅ የገዛችው ክኒና የምንድነው?" ይሉታል መድሀኒት ሻጩን።