Get Mystery Box with random crypto!

iPhone ባይኖርህ iPhone ያለው ጓደኛ ይኑርህ ።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።። | ወግ ብቻ

iPhone ባይኖርህ iPhone ያለው ጓደኛ ይኑርህ
።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።

  "መልክ ይስጠኝ እንጂ ሙያ ከጎረቤት እማራለሁ" ትላለች እናቴ።

"Snapchat ይኑር እንጂ ሙያ ከጎረቤት እማራለሁ" ዘመን ላይ ሳንደርስ በፊት።ዕድሜ ለካሜራ ጥራትና ለSnapchat እኔና መሰል መልከጥፉአውያን መልክን ትተን ስለሙያ መጨነቅ ከጀመርን ቆየን!በቀደም አንዷ የሰፈሬ ልጅ ቴሌግራሟ ላይ የለጠፈችውን ፎቶዋን አይቼ ጉድ ብዬ አልበቃኝ አለ!ሳውቃትኮ ትል ያላመጠው ቲማቲም ነው ምትመስለው!እንዲያውም የአፍንጫዋን ትልቅነት በተመለከተ እናቷ ወ/ሮ አበሩ ሲቀልዱባት

  "ዝንጀር እስቲ ወጡን አሽትችና ጨውን ንገሪኝ" ይሏታል።ሰፈር ውስጥ ሁሉም "ዝንጀር" ነው የሚላት...ዕውነተኛ ስሟ "ጤና"እስኪረሳ ድረስ!ታዲያ ዝንጀር ዩኒቨርስቲ ስትገባ አጎቷ ከካናዳ IPhone ላከላት።በሄደች በሳምንቷ "ለእታባ አሳይልኝ"ብላ ጊቢ የተነሳቻቸውን ፎቶዎቿን በቴሌግራም ላከችልኝ።

  ወ/ሮ አበሩ ስልኬን እያገላበጡ ፎቶውን አዩትና

  "ሚጡ...የዝንጀርን ፎቶ አምጭው እንጅ"
  "ይኸው ዝንጀር ናትኮ"
   "ክይ!ቅማላም!...መሀይም ነኝ እንጅ መቀለጃ ነኝ?"
   "ኧረ ማርያምን አበርዬ!ይኸ ባለፈው የገዙላት ቲሸርት አይደል እንዴ?"
   "የት ገብቶ ነው ያ ለምቦጭ?ያ ሁላ ቡግር ምን ዋጠው?"
   "አገሩ ተመችቷት ይሆናላ"
   "በሳምንት?እኔ መልኳ መለስ ቢል ብየ በየሳምንቱ የቅቤ ስቀፈቅፍ ኖሬ እዛ ኸዳ በሳምንት ይኸን ያህል ወዝ?ይች በልቶ ካጅ!""

ዝንጀር ለእረፍት ስትመጣ በስልኳ የተወሰኑ ፎቶዎች አስቀረሁና ፌስቡኬ ላይ ለጠፍኩ።ከዚህ ቀደም ለፎቶዎቼ የተሰጡኝን አስተያየቶች መለስ ብዬ ቃኘሁ።

  ጥሎብኝ አንድ መፅሀፍ ባነበብኩ ቁጥር ከመፅሃፉ ጋር ፎቶ ተነስቶ የመለጠፍ ልምድ አለኝ።''የኢትዮጵያ ታሪክ ከኖኅ እስከ ኢህአዴግ"ከሚለው መፅሐፍ ጋር ፀጉሬን አጎፍሬ ለተነሳሁት ፎቶ አንዱ ተንከሲስ እንዲህ የሚል አስተያየት አስቀምጦልኛል።

  "የ77ቱ ድርቅ መልክ ቢኖረው አንቺን ይመስላል።ዘቅዝቄ እንደ መጥረጊያ ብጠቀምሽ ጉራንጉሩ ሁላ አይቀርሽም ስታፀጅው።"

ዝቅ ብሎ ደግሞ ሌላኛው

   "አንቀፅ 39 ፊት!ፊትሽ የመገንጠል ስሜቴን ቀሰቀሰው!ከኢትዮጵያ ውጣ ውጣ የሚለኝ መጣ!" ብሎኛል።ወረድ ስል ደግሞ

  "ፀሀዩ ከሮ ጥላ ተወዶ ፊት!ፊትሽ ህልም ይመስላል...አይቼው ልጮህም አማረኝ ልሮጥም አማረኝ ግን አልቻልኩም...ፍቺና ወይ አስፈቺና ገላግይን አቦ!" ሌላው ደግሞ

"ይኸን ግንባር ይዘሽ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ብትሄጂ የራስሽ ክልል ይኖርሽ ነበር!"

  ከኔ ፎቶ በላይ 'ኮመንቶቹ' ናቸው ላይክ ያገኙት።በዝንጀር iPhone ታሪክ ሳይቀየር በፊት...ከአሁኖቹ "ኮመንቶች" በጥቂቱ

   "ፍንጭትሽ ደስ ስትል...ካንቺ ፍንጭት ከኔ ዲምፕል 'ሼር' አርገን ለምን አንዲት ቆንጅዬ ልጅ አንወልድም?"

  "ዓይኖችሽ  አንድነት ፓርክን ያክላሉ።ፍቀጂልኝና ሰልፊ ልነሳባቸው"
   
  

ወይ iPhone ወይ iPhone ያለው ጓደኛ ይኑርህ!

ማዕዶት ያየህ(ዘማርቆስ)
(
@gize_yayeh)

15/09/2015 ዓ.ም.


@wegoch
@wegoch
@paappii