Get Mystery Box with random crypto!

... ዝም ያለ መልክ ረጋ ያለ ሰውነት ያስደነግጣል? ለምን እንደምደነግጥ እኮ ነው ያልገባኝ። ል | ወግ ብቻ

...
ዝም ያለ መልክ ረጋ ያለ ሰውነት ያስደነግጣል?
ለምን እንደምደነግጥ እኮ ነው ያልገባኝ።
ልክ ሳየው ልቤ ምቱን ያፈጥነዋል፤ እጆቼ መንቀጥቀጥ ፊቴ መቅላት ይጀምራል። አይኖቼን ምን ለይ እንደማሳርፍ እንዴት ማውራት እንዳለብኝ ግራ እጋባለው። መንገድ ለይ ከሆንኩ ደግሞ ልክ ገና ከቤት እንደወጣ ሰው እግሬ ይማታብኛል፤ አየር ለይ የምረግጥ ይመስል እወላከፋለው። ስለ ራሴ የነበረኝ መረዳት ሚዛኑን ይስትና ፊቴ ለይ ያለች ትንሽዬ ነጥብ ትታየው ይሆን ብዬ ስጨነቅ ራሴን አገኘዋለው።

አይንን ያዝ በሚያደርግ መልኩ አይደለም አይኖቼን አስሮ ያቆያቸው፤ አንደበተ-ርትዑነቱም አይደለም ሲያወራ በሰማሁት የሚያሰኘኝ፤ በሩቅ በሚታየው ሞገሱም አይደለም ልቤን ሲያርደው የሚውለው።

እዩኝ በሚሉ መልኮች መሀል ነው የሱን ዝም ያለ ውበት ያየሁት፤ ከብዙ ተናጋሪዎች መሀል ገኖ ነው የሱ አድማጭነት እልፍ የሚያስወራኝ እልፍ የሚያፅፈኝ። ስክነት ያለው ህይወቱ ነው በሺህ ችኩል በሺህ ጥድፊያ መሀል ሁሉን አደብዝዞ እሱን ብቻ የሚያስመለክተኝ። የእውነቱን ኑሮ ነው ኑረቱን እንድወድለት ያስገደደኝ።

ያወራኝ እለት ቃላት ብቻ አልነበረም ከአንደበቱ የሰማሁት፤ ዝም ቢል እንኳን ብዙ መናገር የሚችል ገፅ ተችሮታል። እሱ ሲያወራ ስረታ እሱ ሲናገር ስርድ ይታወቀኛል። መቼ አምኜ መቼ እንደተቀበልኩት መቼስ ልቤን አሳልፌ እንደሰጠው እንጃ። ግን ከነበርኩበት ሁካታና ጥድፊያ አውጥቶ ሲያሰክነኝ ይሰማኛል። ዘመንን ማዘዝ ይችል ይመስል እሱ ጋር ስሆን የረሳሁት ሰላም የረሳሁት ፀጥታ በእርጋታ ከሚፈስ ጊዜ ጋር ዙሪያዬን ይከበኛል። ሰው ለመማረክ አለኝ የሚለውን የማንነት መልክ ይዞ ከውድድር አይሰለፍም ይልቁንስ ባለበት ይቆያል እንጂ። ከራሱ ጋር፤ የታይታ ካልሆነው ገዢ ስብዕናው ጋር።
እናም ሚዛን ልኬቱን ማጣት ይጀምራል። ከተናገሩት ሁሉ ይልቅ እሱ ይደመጣል፤ ከታዩት ሁሉ ይልቅ አይን ለማረፊያው እሱን ይናፍቃል፤ ከተገዳደሩት ሁሉ ይልቅ እሱ ሳይታገል ይጥላል። በቀደዱለት አይፈስም ነገር ግን በዙሪያው ያለውን ሁሉ ይዞ ወደ እራሱ መንገድ መሻገር ይቻለዋል።

"ይሄ ሰው ማንነው?" ያሰኘኛል፤ ማንነው? የጊዜው ኑረት እንዲህ የሚገላበጥለት። ማንስ ነው? ብቻውን ኑሮ በብዙ ሚረታው። እንዴት ሆኖለት ነው ሲያደምጥ መሰማት ሲመለከት ማውራት ለሱ የተቻለው። እንዴት ብረዳው እንዴት ቢገባኝ ነው ሚዛኔን በእሱ ተክቼ ሰው የማገዝፈው ከልኬት ማወረደው። ምኔን ቢያገኘው ምኔን ቢነካው ነው ዛሬ ገና መኖር የጀመርኩ ይመስል እጆቹ ካልያዙኝ የምንገዳገደው።

በዚህ ልክ የራስ ሰው በዚህ ልክ አዋቂ በዚህ ልክ አስተዋይ... ይሄ ሰው ማነው?

@wegoch
@wegoch
@paappii

By mahi