Get Mystery Box with random crypto!

ከተበሉስ አይቀር በጎጃም ቡዳ! ።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።    ጎጃሜ ነኝ።ያውም ማርቆሴ | ወግ ብቻ

ከተበሉስ አይቀር በጎጃም ቡዳ!
።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።

   ጎጃሜ ነኝ።ያውም ማርቆሴ!የበላይ ዛር የሚያክለፈልፈኝ!እናላችሁ አምና እናት ከተማ ማርቆስን ለቅቄ ለአስኳላ ወደባህር   አዝግሜ ኖሮ ጠሀዩ ልብ ልቤን ሲጠብሰኝ ጊዜ በሳምንቴ ተመልሼ ወደማርቆስ!

  "ኧግ 'የኢንበርስቲ' ተማሪ!ይኸ ነው እንግዲህ ?በሳምንት ምላሽ ሆነ?"ኮብራ ምላሷ ጎረቤታችን ስንቴ ናት የምትለክፈኝ።

"የረሳሁዋቸው እቃዎች ስላሉ ትምህርት ሳይጀመር ልውሰዳቸው ብዬ ነው።''
  ''ነው?እምምምምም" ከንፈሯን አጣማ ትታኝ ሄደች።ከስንቴ ጋር ስሆን የETV ዜና ሳይቀር ይናፍቀኛል።የመሰለ ገ/ሕይወት ለንቦጭ ሁላ ውል ይልብኛል።ከያዘች አትፈታማ!ጥቃቅን ማብራሪያን ፍለጋ ልብህን እንደ ሎሊ ፖፕ ትጠባዋለች ነው 'ምልህ!!

አሁን በቀደም ዕለት ሱሪ ለብሼ የማላውቀው እኔ ቬል ሱሪዬን ወትፌ ስመናቀር አገኘችኝና

"ኧሯ!ሚጡ...ሱሪ ሲያምርብሽ አንቺ!"

"አመሰግናለሁ ...ያው የጊቢ ተማሪ እንምሰል ብለን ነው!"

"ኧራ!ልበሽ ኧረ!ለማናባቱ ብለሽ ደሞ!ይወጭቀው!ስንት ገዝተሽው ነው?"አለችኝ ሱሪዬን ቀለሙ እስኪለቅ እያየች።

"ቀላል ነው...950 "

"ዘጠኝ ከአምሳይ?ሸጋ ነው አንች!ተየት ነው የገዛሽው?ተአዲሱ ገበያ ነው?"

"አዎ ከዛው ነው"

"አምሮብሻል ነጋ ይሙት!ተንግዲህ ቀሚስ እንዳትለብሽ እንዲያውም...እና..."አቋረጥኳት

"በይ እሺ ሰላም ዋይ ስንቴ ጓደኞቼ እየጠበቁኝ ነው""ብያት ሄድኩ።'እህ ብዬ ከሰማሁዋት የገዛሁበትን ቀንና ሰዓት...ያጋዛኝን ሰው...የሸጠልኝን ሰው ...የልብሱን ብራንድ...መጠየቋ አይቀርም።ደሞ 'አምሮብሻል' ይባልልኛል!( ሰፈር ውስጥ "እናንተ!ያች የወለላ ልጅ ተበላሽታ አይል!ያችን የዶሮ ኩላሊት እምታክል ቂጧን በሱሪ ወትፋ ስትሞላፈጥ አይቻት..."እንደምትል መች ጠፍቶኝ?ዶሮ ኩላሊት ባይኖራት ራሱ የኔን ቅጥነት ለማጉላት ሲሆን እነስንቴ ቤት አላት)

የረሳሁዋቸውን እቃዎች ሸክፌ ወደ ባህርዳር ከተመለስኩ በሁዋላ ከዶርም ጓደኞቼ ጋር ብዙ ጊዜ እሰጥ አገባ ውስጥ የሚከተን ነገር ነበር።"ጎጃሜ ቡዳ ነው " የሚሏት ነገር!

"ጎጃሜ ቡዳ ነው
ብለሽ ያወራሽው
ሰው ሰውን ሲበላ
የታባሽ አየሽው?"  ከአፌ የማይጠፋ ግጥም ሆነ። በጨዋታችን መሀል አቦሰም ጥለን ዕድሉ የኔ ከሆነ "ድሮስ ጎጃሜ!"ይላሉ አፋቸውን ሸርመም አድርገው።ነገሮች በአንድም በሌላም መንገድ የዕድል ገፃቸው ወደኔ ከዞረ "ጎጃሜ አይደለች?"የሚሉት ጥቂት አይደሉም።አንዱማ እንዲያውም የሆነ ቀን  'ላማክርሽ እፈልጋለሁ'ብሎ በቁምነገር ቀጠረኝና ተገናኘን።

"እየውልሽ ጊዜ...እእ...እንትን ነው"
"ምን?"
"የሆነች ልጅ ወድጄ..."
"ኧረ?ማናት?"
"አታውቂአትም"
"እና አናግረሀታል?"
"ለሱ ነውኮ የፈለኩሽ"
"እንዳናግርልህ?"
"ኧረ በንግግር የሚገባት አይደለችም ልጅቱ"
"እና ምን ላርግልህ?"
"ያ...ው...ጎጃሜ አይደለሽ?እናንተኮ እዚህ ነገር ላይ አትታሙም...መ...ስተፋቅር እንድትሰሪልኝ ወይ እንድታሰሪልኝ ነበር" ብሎኝ እርርርርርፍ!
     ከዚህም ከዚያም የጎጄን ቡዳነት ሲደጋግሙብኝ መገንፈሉን እየተውኩ እኔው ራሴ በራሴ መቀለድ ጀመርኩ።

"ጎጃሜ ቡዳ ነው
  ብለሽ ያወራሽው
  ሰውን ሰው ሲበላው
  የታባሽ አየሽው ?"

እል የነበርኩት ልጅ

"ቡዳ ነው ይሉታል
  ጎጃምን በሙሉ
መች ጣዕሙ ሊታወቅ
ሰው ይዘው ካልበሉ"  ማለት ጀመርኩ።በሊታን መምረጥ ቢቻል ከተበሉስ አይቀር በጎጃም ቡዳ!ፍቅር ነዋ ምትለፈልፈው!!

  ማዕዶት ያየህ(ዘማርቆስ)
(
@gize_yayeh)

15/09/2015 ዓ.ም.


@wegoch
@wegoch
@paappii