Get Mystery Box with random crypto!

አክስቴን እንዴት ፖለቲከኛ እንዳደረጉብኝ ።።።።።፡።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።። ጊቢያችን በ | ወግ ብቻ

አክስቴን እንዴት ፖለቲከኛ እንዳደረጉብኝ
።።።።።፡።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።

ጊቢያችን በሰጠን የ9ቀን  እረፍት ምን እንደምሰራበት ሳቅድ 5ኛው ቀን ላይ ደረስኩ...ያለ ቁምነገር!ወይ አላነበብኩ...ወይ ወግ ቢጤ አልሞነጨርኩ...ወይ ስካርፌን ጠምጥሜና ፀጉሬን አጎፍሬ የተነሳሁትን የአብዮተኛ ገጣሚት ፎቶ ፌስቡኬ ላይ አልለጠፍኩ...ብቻ የሆነ ቀን አክስቴ ዓይኔ ላይ ውል ስትልብኝ ተነሳሁና ቤቷ ሄድኩ።

"ቅንጭር ከየት ተገኘሽ?" አለችኝ።ከሲታነቴን ስታጋንን ነው "ቅንጭር"የምትለኝ።

"እታባ ደግሞ!እይ እስቲ እንዴት እንደወፈርኩ...ባህርዳርኮ ተመችቶኛል" ሰው ከሲታነቴን ሲነግረኝ ደሜ ነው ሚፈላው።

"አየሁት እቴ!ጣውላ ቂጥ!ምንሽ ነው የወፈረው?ያው የተላገ ጣውላ እንደመሰልሽ ነው!እንደው በምስክር ሞት ምናል ደህና ደህና ነገር ብትበይ?"

"ማነው ደግሞ ምስክር?"

"ምስክር ነዋ!"

"እኮ አላወቅሁትም"

"አይ እንግዲህ!አላወቅሁትም አይባልም አላወቅነውም ነው 'ሚባለው" ብላኝ እርፍ።ከመቀመጤ ሪሞቷን ቀሰረችና የጦፈ የፓለቲካ ክርክር ያለበትን ጣቢያ መርጣ ተደላድላ መከታተል ጀመረች።

"እታባ ኧረ ቀይሪው በማርያም!"

"ዝም በይ!ጁንታ!ምን ታውቂያለሽ ስለሀገር?ዝፈኝ አይበሉሽ እንጂ!"

"መቼስ ከሞት ዜና ዘፈን ይሻላል"

"እዬዬም ሲደላ ነው ቅንጭር!አታድርቂኝ !እዚሁ ደፍቼሽ መቃብርሽ ላይ ችግኝ እንዳልተክል!"

(ምንድነው ያስነኩብኝ ይችን ሴትዮ?ጊቢ ልሄድ ስል ልትቆርብ እያኮበኮበች አልነበር?ማነው የፖለቲካ ጋኔል ያስመታብኝ? )

"እታባ ቆረብሽ አይደል?"

"ሲኖዶሱን ከፍለውት በየት በኩል?"( ምንም ብጠይቅ መልሷ ውስጥ ፖለቲካ አለ)
ወዲያው  4ዓመት የሞላው የልጅ ልጇ(የአክስቴ ልጅ) ወዲህ ወዲያ እያለ ሲጫወት ድመታቸው ላይ ቆመባትና አስጮሀት ።አክስቴ ብስጭት ብላ አምባረቀችበት

"የ20ሚሊየኑ  ባስ እላይህ ላይ ይውጣ!አፍርጠህ ትገድላት?" ለደቂቃዎች ክርክሩን ስትከታተል ቆየችና

"ቅንጭር...ጥሩ ቀን መጣሽ...ያች እምትወጃት አለችልሽ ሂጅ አቅርቢና ብይ"አለችኝ።መኮረኒ በአትክልቴን እየበላሁ ቤቱ ግድግዳ ላይ የተለጠፉትን አዳዲስ ምስሎች መታዘብ ጀመርኩ።ከፊት ለፊት ያለው ግድግዳ ላይ የዘመነ ካሴን ምስል ከነ ንግግሩ የያዘ መጠነኛ ባነር ተሰቅሏል።ከዓመት በፊት እዚሁ ግድግዳ ላይ የመድሃኔዓለም ስዕለ-አድህኖ ተሰቅሎ እንደነበር ትዝ አለኝና ደነገጥኩ።የቀኝ ግድግዳው ላይ የቀድሞው ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ምስል ተሰቅሏል።ከምስሉ በታች ያለውን ፅሁፍ ሳነብ ነው አክስቴ እንደለየላት የገባኝ።

"ባሏን ብታይ ውሽማዋን ጠላች ሆኖብኝ ነው ስትሞት ስለት ማስገባቴ!እሱ ቸሩ መድሃኔዓለም ነፍስህን በገነት ያኑራት!
                                     ያንተው ወይንሸት "


ወደሌላኛው ግድግዳ ስዞር አንድ ሱፍ ያጠለቀ ሰው  "ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያ ነን" ከሚለው ንግግሩ ጋር ተዘቅዝቆ ተሰቅሏል።

"እታባ ይሄን ሁሉ አንቺ ነሽ የለጠፍሽው?"

"ኋላስ ማን ሊለጥፈው ኖሯል!ግድግዳ ኬኛ!"

"በይ ደህና እደሪ ልሂድ"

"ልሂድ አይባልም ...እንሂድ ነው ሚባለው ቅንጭር"

( )

ማዕዶት ያየህ(ዘማርቆስ)
(@gize_yayeh)

10/09/2015 ዓ.ም.

@wegoch
@wegoch
@wegoch