Get Mystery Box with random crypto!

ዝንቁል ።።።።።። ከአያቴ ስድቦች ሁሉ ግንባሬ ላይ የተለጠፈ እስኪመስለኝ ሳስበው የሚያሳፍረኝ ስ | ወግ ብቻ

ዝንቁል
።።።።።።

ከአያቴ ስድቦች ሁሉ ግንባሬ ላይ የተለጠፈ እስኪመስለኝ ሳስበው የሚያሳፍረኝ ስድብ ነው...ዝንቁል!ከሆነ ጊዜ በሁዋላ ከስድብነት ወደ ቅፅል ስምነት ተቀየረና ሳልወድ "አቤት" የምልበት መጠሪያዬ ሆኖ አረፈው።

"ዝንቁል ነይ አያ ከባዱ መጧል ሰላም በይው"ትለኛለች የምወደው አጎቴ ሲመጣ።
"ምነው እማ ስንቄ ካልጠፋ ስም?"ይላል አጎቴ እየሳቀ።ሰው ስሜን ሰምቶ ሲስቅ ለጉድ ነው 'ምሸማቀቀው!አንገቴን ወደ መሬት ትክል!በተለይ አጎቴ ከሳቀ!
"ምን ላርጋት እህ ብልጠት ያልሰራባትን!ነክሮ የተዋትን ከባድሰው!እንደው ፍርጃ ነውኮ እናንተየ!ሰው እንዴት በአስራ አምስት አመቱ እሳትና ውሀ አይለይም?ወይ አንች የአብማይቱ አታሳይኝ የለሽ!"ትላለች ሞኝነቴን ስታጎላ።በእርግጥ ሱቅ ስላክ ባለሱቆቹ ይከስራሉ ብዬ ስለማስብ መልስ አልቀበልም ብዬ አልቅሼ አውቃለሁ...አልክድም አምና አያቴ ለእንግዳ ሰርታ ያስቀመጠችውን ድንች ወጥ አሙቂ ያለችኝ ጊዜ እንዲጣፍጥላትና እንድትመሰገን ብዬ ብርጭቆ ሙሉ ስኳር ጨምሬበታለሁ።

"የሆነስ እንደሆን ስሙ ተዋህዷት አለቅጥ ቂል ያረጋታል እንጂ ምን ይበጃታል እማ ስንቄ?"ይሄኔ የእማ ስንቄ ቀይ መብራት ይበራል።ርዕስ ታስቀይራለች።በስሜ አልያም በጅልነቴ ዙሪያ ምክር ወይ አስተያየት ቢጤ ሊሰጧት ከቃጡ መስሚያዋ ጥጥ ነው።

"አንተ ከባዱ...እንደው ያች በቅሎህ ተሻላት አደራህ?"ትላለች የዝንቁልነቴን መዝገብ ትከድንና።እሷ ለመጣ ለሄደው የሞኝነቴን ነገር ተናግራ አልታክታት ቢልም እኔ ግን መስማቱ መረረኝና አንድ ቀን እንዲህ አልኳት።

"እማ ስንቄ"

"ኧ!ስንቋ አለቀኮ ብያለሁ እችን የቋቁቻም ዘር!እሰሰይ!የቆሎ ጓደኛዋ መሰልኳት?"

"ሁለተኛ ዝንቁል እንዳትይኝ!እናቴ ያወጣችልኝ ወርቅ የሆነ ስም አለኝ!ማንጠግቦሽ በይኝ"

"የጠገበ አህያ ይውጣብሽና ያላልኩሽ እንደሁ ትመችኝ?" አኩርፌ ወደውስጥ ስገባ የጎረቤታችንን የእማ ዝማምን ድምፅ ሰማሁ።ዘውትር  እየተጨናበሱ የሚመጡት እሳት ሊጭሩ ነው...የምጭርላቸው እኔ ብሆንም ...የአያቴ ጥሪ ተከተለ

"ዝንቁል ነይ ለዝማም እሳት ጫሪላት"

ማዕዶት ያየህ(ዘማርቆስ)
(
@gize_yayeh)

08/09/2015 ዓ.ም.


@wegoch
@wegoch
@paappii