Get Mystery Box with random crypto!

ይሉኝታ(ክፍል 2)   ያገኘኝ ሁሉ ሲልከኝና ሲያዘኝ ውዬ የዛለ ሰውነቴን እየጎተትኩ ቤቴ እገባለሁ | ወግ ብቻ

ይሉኝታ(ክፍል 2)

  ያገኘኝ ሁሉ ሲልከኝና ሲያዘኝ ውዬ የዛለ ሰውነቴን እየጎተትኩ ቤቴ እገባለሁ።እናቴ የቡና እቃዎቿን እያቀራረበች በመሀል ቀና እያለች ስታስተውለኝ ትቆይና

"አዋጥተው እንደገዙት መጋዣ ሲጭኑህ ይውላሉ አይደል?እንደው እምቢ አልፈጠረብህም አቡሽ?እምቢ አትልም?"

"ይረግሙኛል ብዬ ነውኮ"

"ኤዲያ!የረገሙህስ እንደው?አንድ ሳህን  ጤፍ ይገዙልህ መሰለህ?አዬ አለመታደል!እንዲህ እብን ሆነህ ትቀር?አድገሀልኮ ደስታ!18 ሞላህኮ!ልጅ አትባል ከንግዲህ"
ስትለኝ በመሀል አንድ ድምፅ አቋረጣት

"እንዴት ውላችሁዋል እናንተ?"እያሉ ወደውስጥ ዘለቁ እትየ አትጠገብ።እኚህን ሴትዮ ሳያቸው ያጥወለውለኛል።በነገር ሰው ሲወጉ ወደርም የላቸው።በቀደም ከመሸ ተልኬ ስወጣ ከማህሌት(የሰፈሬ ልጅ) ጋር ሱቅ ተገናኘንና የሆነ ያልሆነውን እያወራን ስንራመድ እትየ አትጠገብ በዛ ረጅም ቁመታቸው ሀውልት መስለው ከፊትለፊታችን ተገነጨሩ።ማህሌት ትከሻ ላይ ጣል ያረኩትን እጄን በፍጥነት አውርጄ ሰላምታ አቀረብኩላቸው።በውሉ ያልተሰማኝን ነገር አልጎምጉመው ሄዱ።በነጋታው ቤታችን መጡና

"እንዴት ውላችሁዋል ቤቶች?"አሉ በጎንዮሽ እያገረመረሙኝ።ወዲያው ወደኔ ዘወር አሉና

"ደስታ...ምነዋ ዛሬስ የጋሽ አለሙ ልጅ የት ሄዳ ነዋ?"አሉኝ።በአስማት እንዳደረቁኝ ሁላ ቀጥ ብዬ ቀረሁ።አባቴ

"ኧ?ደሞ የጋሽ አለሙ ልጅ እዚህ ምን ታረጋለች ?" ጥያቄአዊ አስተያየቱን እያነጣጠረብኝ።

"አብረው አያጠኑም እንዴት?ትናንት እዚህ አምሽታ ስትወጣ ያየሁዋት መስሎኝ"ብለው እርርርፍ!ምን ያልተመኘሁላቸው እርግማን አለ?ሙሴ በበትሩ ለድድ ሩብ ጉዳይ የሆነ ጥርሳቸውን ቢያረግፈው ደስታዬ! ኢያሱ ያቆማት ፀሀይ እንትናቸውን ለምች ትስጠው!ሌላ ክፉ አልመኝም!

"ኧረ ማታኮ ሱቅ ተገናኝተን እየሸኘሁዋት ነው ያዩን እዚህ አላመሸችም"አልኩኝ እየተርበተበትኩ።

እናቴ 'ለዚህም ደርሰሀላ?!'አይነት አስተያየት አየችኝ።እየተጎተቱ መጥተው የነገር መርዛቸውን አርከፍክፈውት ሄዱ።ከዛ ወዲህ ቤታችን ሲመጡ በጤና አይመስለኝም።እስኪወጡ ሱባኤ እይዛለሁ።ዛሬ ደግሞ ምን ሊሉኝ ነው እያልኩ ስብሰለሰል

"ደስታየ...ነገ ትምህርት አለህ?"አሉኝ።

ይቀጥላል

ማዕዶት ያየህ(ዘማርቆስ)
(gize_yayeh)

@wegoch
@wegoch
@paappii