Get Mystery Box with random crypto!

ይሉኝታ(ክፍል 1)   እግዜሩ ያለ የሌለ አቅሙን ሙጥጥ አድርጎ የሰራውን ይሉኝታ ሁሉ የሆነ ጊዜ | ወግ ብቻ

ይሉኝታ(ክፍል 1)


  እግዜሩ ያለ የሌለ አቅሙን ሙጥጥ አድርጎ የሰራውን ይሉኝታ ሁሉ የሆነ ጊዜ ላይ መሸከም ከብዶት ሳለ ወደ ቀራንዮ ጫፍ መስቀሉን ሲጎትት ቀረብ ብሎ እንዳገዘው ምስኪን እኔም ጠጋ ብዬ"አባት ሆይ! ይህን ሁሉ ይሉኝታ ብቻህን?ባይሆን ትንሽ ላግዝህ !"ብዬ ያንን ለምድር ለሰማይ የከበደ ይሉኝታ ተቀበልኩት።እሱም በይሉኝታ መቅረቤን አይቶ "ላለው ይጨመርለታል"በሚለው መርህ በእገዛ ሰበብ የተቀበልኩትን ይሉኝታ መልሶ ሳይወስድልኝ ቀረ።እነሆ እኔም ከዛ ወዲህ ትልቅ ትንሹ  ሲያሻው እንደ ስጋጃ እየረገጠ፣ሲፈልግ እንደማስቲካ እያላመጠ፣ባስ ካለም እንደ እንቧይ እያፈረጠ በይሉኝታዬ እኔው ላይ ዳንኪራውን ይመታል።

  "ልጅ ደስታ!እስቲ ና ወዲህ" ይሉኛል እማ አልጣሽ ከመንገዱ ጫፍ ወገባቸውን ይዘው ይቆሙና።

  እማ አልጣሽን ሳያቸው አስማተኛ አሮጊት ይመስሉኛል።በፈገግታቸው ተሸፍኖ ያለውን ከባድ ቁጣ ከእግዚአብሔር በላይ ሳልፈራው አልቀርም።እንደው አንዲት ነገር አዝዘውኝ እምቢ ብላቸው  ፈገግ ያለ ገፃቸውን በቅፅበት ክስክስ ያደርጉና በቅርባቸው ያለ ጭራሮ ቢጤ አንስተው ድግምት ነገር እያነበነቡ መሬቱን ጫር ጫር ቢያደርጉት ሽንቴን ልሸና ምናምኔን አውጥቼ ባንከፈረርኩበት እንደ እንጨት አድርቀው የሚያስቀሩኝ ይመስለኛል።ወይ ስፈራቸው!

  "አቤት እማ አልጣሽ" እላለሁ አጠገባቸው ስደርስ።

"ደስታየነህ...እንደው መቸም አንዴ ሲፈጥርህ የአሮጅትና የሽማግሌ መጫወቻ ሁን ብሎሀል...አንተም ጣድቅ ነህ መቸም አልታዘዝም አትልም...እንደው እሱ መድሀኔዓለም ምቀኛህን ውጋት ይዘዝበት!"

"አሜን እማማ"

"እንደው ያችን እላይ መንደር ያለችዋን አትጠገብን አወቅሀትም አይደል?"

"እትየ አትጠገብ የጋሽ ባህሩን ባለቤት አይደል?"

"እ...የባህሩ ምሽት!ሰልስትና እለታ ቸግሮኝ 50 ሳህኔ ማሽላ ተበድሬአት ነበር...አሁን የሻለቃ(ሻለቃ ማለት በደርግ ጊዜ በውትድርና ያገለግል የነበረ ባለቤታቸው ነው።)  ጡረታ ሲመጣ ሸምቸ መግባቴ ነው...ንስማ አድርሰህላት ና ጀታየነህ እመርቅሀለሁ"አሉኝ እግራቸው ስር በማዳበሪያ ታስሮ ወደተቀመጠው እህል እያዩ።የእትዬ አትጠገብን ቤት ርቀት ሳስብ ማዳበሪያው ገና ሳልሸከመው ደከመኝ።በመንገዴ የማገኛት ክፉ አቀበት ከጦሳ ተራራ ገዝፋ ብትታየኝም 'እምቢ' ግን አልልም።ይሉኝታዬን ለማን ሸጬው?

  እንደፈረደብኝ ያንን በግምት 65 ኪሎ የሚሆን ማዳበሪያ ተሸከምኩትና መንገዴን ጀመርኩ።እትየ አልጣሽ ከሁዋላዬ ሲመርቁኝ አልፎ አልፎም በሞኝነቴ ሙድ ቢጤ ሲይዙብኝ ይሰማኛል።

"ተባረክ ደስታየነህ ብሩክ ሁን!አሁን የማን ልጅ እሽ ብሎ ይታዘዛል በዚህ ዘመን?እድሜ ይስጥህ!ወገብህን ተውልቃት፣እጅህን ተቁርጥማት ይሰውርህ!"ይሉና ደሞ ድምፃቸውን ዝቅ አድርገው

"አይይይ እንደው መድሃኔዓለም!እንደው እንዲህ ማንም የሚጭነው አህያ ሆኖ ይቅር!ኧረ አህያስ ሲበዛባት ትለግማለች..." ሲሉ ከነሸክሜ ዞር ስል እንደገና ድምፃቸውን ሞቅ ያደርጉና

"እንጀራ ይውጣልህ ደስታየነህ!ምቀኛህን እግሩን ያልምሸው የኔ ዓለም!ውለህ ግባልኝ ክፉ አይንካህ!" ይሉኛል።

ይቀጥላል

ማዕዶት ያየህ

17/07/2015 ዓ.ም.

@wegoch
@wegoch
@paappii