Get Mystery Box with random crypto!

..... ይህ ቀን ግን እንደተለመዱት ቀናት አይሆንም። መነሻህ ለይ ስራዎችህን ሰዎች እንዲረዱት | ወግ ብቻ

.....
ይህ ቀን ግን እንደተለመዱት ቀናት አይሆንም።

መነሻህ ለይ ስራዎችህን ሰዎች እንዲረዱትና ትኩረት እንዲሰጡት ትሻለህ፤ ቢያበረቱህ፣ ቢያደንቁህ፣ ከጎንህ ቢቆሙ ምነኛ በወደድክ ግን የነገሮች መልክ ሌላ ነው። ሲደክምህ ከማንም ምንም መጠበቅ ታቆምና የተለመደው ስራህን ትቀጥላለህ ብዙ አንድ አይነት ቀናት በአንድ መልክ ያልፋሉ። ከብዙ ቀናት መካከል ግን በሆነችዋ ቀን ነገሮች ይለዋወጣሉ፤ ይህቺ ቀን ላንተ የቀደመውን ተግባርህን የምትፈፅምባት የተለመደች እለት ለሰዎች ግን አንተን አጥርተው የሚያዩባት ልዩ ቀን። ድንገት ሰዎች ለአንተ ትኩረት መስጠት፣ ስራዎችህን ማድነቅ፣ ማሞገስና ማክበር ይጀምራሉ ትደነግጣለህ!
"ልክ እንደተለመደው እኮ ነው" ማለት ይቃጣሀል ግን ለፈጣሪ ስራውን የሚሰራባት ቀን ናትና ለብዙ የትላንት የድካም ቀናቶችህ በዚች አንዲት እለት እጥፍ ድርብ አድርጎ ይክስሀል፤ በዝምታ የሆነውን ሁሉ ትቀበላለህ።

ይህ ቀን ግን እንደተለመዱት ቀናት አይሆንም።

ላደረከው ክፋት ምላሹ ዝምታ ሲሆን ልብህ እየደነደነ ይመጣል፤ የቀድሞ "ምን ይመጣብኝ ይሆን?" የሚለው ፍርሀትህ "ማን ምን ያመጣል?" ወደሚለው ድፍረት ይሸጋገራል ክፋትን በትንሽ ትንሹ ትለማመዳለህ። ለስራህ በጩኽት ይቀጣህ የነበረው ህሊናህ ልክ ምንም ያላደረክ ይመስል ዝም ይልሀል፤ እናም ልክ ካንተ በላይ ሰው ከምድር በላይ ገዢ የሌለ ይመስል ትታበያለህ። የተለመደውን በደል በምትፈፅምባት አንዲት ቀን ግን ፈጣሪ የስራህን ሁሉ ማብቂያ ያደርገዋል።
እንደ ተራራ የገዘፈው እንደ ሰናፍጭ ያልታየህን ቁልል ባልጠበከው ጊዜና ቦታ ይንደዋል፤ በራስህ የክፋት ካብ ፍራሽ ስር ምንምና ማንም ሆነህ ትቀራለህ፤ ይህ ቀን እንደተለመዱት ቀናት አይሆንም።

የፈጣሪ አንዲት እለት አንተ በጠበከው ጊዜና ቦታ አትመጣም የተለየ ፅድቅ ወይ የተለየ ክፋት ባልሰራህባት በአንዷ ቀን ግን የስራህ ሁሉ ማጣፊያ ይሆናል።

ፈጣሪም ሰውም ያላየህ ሲመስልህ ልብህን ከቶ አይክፋው በመልካም ጎዳናህ ለይ ሆነህ በዝምታ አምላክህን ጠብቀው።

ፈጣሪም ሰውም ያላየህ ሲመስልህ በክፋት ጎዳናህ ለይ በማን አለብኝነት እንዳሻህ አትረማመድ አይደለም ቆሞ መሄድ አጎንብሶ እንኳን ምህረት ማግኘት  ለታደሉት ብቻ ይሆን ይሆናል።
ለክፋትህም ልክ አበጅለት ምክንያቱም ይህ ቀን እንደተለመዱት ቀናት አይሆንም።

@wegoch
@wegoch
@wegoch

By mahlet